Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተጠያቂነት በሁሉም እርከኖች ይበልጥ እንዲረጋገጥ…

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተጠያቂነት በሁሉም እርከኖች ይበልጥ እንዲረጋገጥ…

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ግልፅነትና ተጠያቂነት የዴሞክራሲ መርሆዎች ናቸው። አንድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እነዚህን ጉዳዪች መቼም ቢሆን ቸል ሊላቸው የሚገቡ አይደሉም። በአገራችን ህገ መንግስት ላይም የመንግስት ስራዎች ግልፅነትና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል። በህገ መንግስቱ ላይ ፌዴራል መንገስትም የሁን የክልል መንግስታት ተቀንብበው የተሰጧቸው የራሳቸው የስልጣን እርከኖች አሏቸው።

በዚህ መሰረትም ፌዴራል መንግስቱ የራሱ የስልጣን ደረጃ አለው። በዚህ የስልጣን እርከኑ የሚያከናውናቸውን ማናቸውም ተግባራት በግልፅነትና በተጠያቂነት መተግበር ይኖርበታል። የፌዴራል መንግስቱ ማዕከላዊነትን የሚያረጋግጥበት ህገመንግስታዊ አሰራሮች አሉት። በእነዚህ የስልጣን እርከን መሰረት ተጠያቂ ይሆናል። ክልላዊ መንግስቶችም እንዲሁ በህገ መንገስቱ ተለይቶ የተሰጣቸው ስልጣን አላቸው። ራሳቸውን የቻሉ ናቸው። እነዚህ ራሳቸውን የቻሉ የስልጣን መዋቅሮች በሚያከናውኗቸው ማናቸውም ተግባራት ተጠያቂነትን በራሳቸው ማረጋገጥ መቻል ይኖርባቸዋል።

በእኔ እምነት የአንዱ ወገን ጥፋት የሌላው ሊሆን አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከተጠያቂነት የዴሞክራሲያዊ አሰራር ጋር ስለሚጣረስ የትኛውም አካል ተነስቶ ማንንም ተጠያቂ ሊያደረግ አይችልም። አስተሳሰቡም ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው።

በሌላ አገላለፅ በፌዴራል መንግስት የስልጣን እርከን ስር ለሚገኙ ክንዋኔዎች ተጠያቂው ፌዴራል መንግስቱ እንጂ የክልል መንግስታት ሊሆኑ አይችሉም። የክልል መንግስታትም በእነርሱ የስልጣን እርከን ስር የሚወድቁ ጉዳዩችን ተፈፃሚ ሲያደርጉ ለሚፈጠሩት አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ችግሮች የተጠያቂነቱን ድርሻ የሚወስዱት እነርሱው ናቸው—ፌዴራል መንግስቱ ሊሆን አይችልም። ይህም ሁሉም በየደረጃው ለሚያከናውነው ማንኛውም ተግባር ተጠያቂ እንደሚሆን የሚያስረዳ ነው።

ታዲያ ይህን የተጠያቂነት መንፈስ በሁሉም የስልጣን አርከኖች ውስጥ ገቢራዊ ማድረግ ይገባል። በዴሞክራያዊ ስርዓት ውስጥ ስልጣን የሚሰጠው ከተጠያቂነት ጋር እንጂ ለብቻው አይደለም። የስልጣን ምንጭና ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ መጠን “ማን ምን አከናወነ?” የሚለው ጥያቄ በባለቤቱ መነሳቱ አይቀርም። ስልጣንን ከህዝብ በውክልና ተቀብሎ “ከደሙ ንፁህ ነኝ” ማለት አይቻልም። ህዝብ “ለምን?” ሲል መጠየቁ አይቀርም። እናም ተጠያቂነት በሁሉም የስልጣን እርከኖች እንዲኖር በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ህዝብን አማክሮና አስወስኖ መስራት ቁልፍ ጉዳይ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት በተለይ በክልል መንግስታት ውስጥ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። ፌዴራል መንግስት በውስጡ ለሚፈጠሩ ችግሮች ክልሎችን ተጠያቂ እንደማያደርግ ሁሉ፤ ክልሎችም ለችግሮቻቸው ፌዴራል መንግስትን ተጠያቂ ሊያደርጉ አይችሉም።

እናም በየትኛውም እርከን ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ለምሳሌ ያህል መንግስት በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል። ተጠያቂነት ካለም አብሮ ይወስዳል። በፖለቲካዊም ይሁን በአስተዳደራዊ ጉዳዩች የሚጠየቁ ካሉም እንዲጠየቁ ይደረጋል። ይህ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው።

ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ አለበት። ይህም ሲሆን ዴሞክራሲ ያብባል። ዴሞክራሲው ሲያብብም የተጠያቂነት አሰራር በዚያው መልኩ እያደገ ይሄዳል። ዴሞክራሲ ሲጎለብት ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የተሞላበት እንዲሁም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል አሰራር መጠናከር አለበት።

የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው። በመሆኑም በሁሉም የስልጣን እርከኖች ውስጥ ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በብዛት ማሳተፍ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

በአንድ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ ተጠያቂነት ካልኖረ ህዝባዊ አመኔታን ማግኘት አይቻልም። በእያንዳንዱ የስልጣን እርከን ውስጥ (በፌዴራልም ይሁን በክልሎች) የመንግስት ስልጣንን የያዘ አካል በስልጣን እርከኑ ደርዝ ውስጥ የሚወድቁ ጉዳዩችን ማስተካከል ሳይችል ቀርቶ ዜጎች ለሞት፣ ለአካል መጉደልናና ለመፈናቀል ችግር ተጋልጠው ሲያበቁ፤ በዚያ የስልጣን እርከን ላይ ያለው ባለስልጣን መጠየቅ ካልቻለ ህዝባዊ አመኔታን ማግኘት አይቻልም። በየደረጃው ለችግሩ መፈጠር ተሳታፊ የሆነ አካል ሁሉ ተጠያቂ መሆን ያለበት ይመስለኛል። ይህ ካልሆነ ግን ህዝቡን ማስቀየም ይሆናል።

እርግጥ በዚህ ረገድ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎች የሚያስመሰግኑ ቢሆኑም፤ በክልል መንግስታት ዘንድም ተመሳሳይ እርምጃ መኖት አለበት። ይህ ሁኔታም ክልሎች ተጠያቂነትን በሁሉም የስልጣን እርከኖቻቸው ውስጥ ገቢራዊ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋልም። አሊያ ግን አንዱ በሌላኛው ላይ ጣቱን እየቀሰረ ተጠያቂነትን አንዲሁ በዋዛ ሊያልፈው አይገባም። አይችልምም። ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የደነገገውን ህገ የህግ የበላይነት መፃረር ስለሆነ ነው።

የህግ የበላይነት በሁሉም የስልጣን እርከኖች መከበር እንደሚኖርበት ጥያቄ አያሻውም። ሀገራችን የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ስለሚሆንባት ነው። ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል።

ከሁሉም በላይ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም።

ይህ የህግ የበላይነት በፌዴራል መንግስት ኢያም በተወሰኑ ክልሎች ውስጥ ብቻ የሚተገበር አይደለም። በሁሉም የፌዴራልና የክልል የስልጣን እርከኖች ውስጥ እውን መሆን አለበት። ያለ የህግ የበላይነት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አይቻልም። ተጠያቂነት ከሌለ የህግ የበላይነት እውን አይሆንም። ታዲያ ተጠያቂነትን በሁሉም እርከኖች ለማረጋገጥ በቅድሚያ በተግባራቂነቱ ላይ በጎ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በንቃት ማሳተፍና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካል ሚናውን ማሳደግ አለበት። ስልጣንን ይዞ ተጠያቂነትን አለመቀበል አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ባለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ቦታ የሌለው መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy