Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ታዳሽ ኃይልን የማልማት ጥረቶቻችን

0 271

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ታዳሽ ኃይልን የማልማት ጥረቶቻችን

                                                      ዘአማን በላይ

ኢትዮጵያ የምትከተው አረንጓዴ የልማት ስትራቴጂ በተለይም ታዳሽ ኃይልን ተጠቅማ በዕቅድ የያዘቻቸውን የልማት ስራዎች ለማከናወን የምታደርጋቸው ጥረቶች ውጤት እያስገኙ ናቸው። እነዚህ ጥረቶች በአፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም እየተደገፉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ግንባታ የሚውል 101 ነጥብ 46 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በብድርና በስጦታ ማቅረቡን  በድረ ገፁ ላይ ይፋ ማድረጉን ማንሳት ይቻላል። ከዚህ ውስጥ 86 ነጥብ 26 ሚሊየን ዶላሩ  እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ለተጠናውና የአዲስ አበባ የኃይል ማከፋፈያና ማሰራጫ ማስተር ፕላን ማስፈፀሚያ በብድር መልክ የቀረበ ሲሆን፤ 15 ነጥብ 20 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ለታዳሽ ሃይል ስራዎች ማስኬጃ በስጦታ የቀረበ ነው።

 

ይህ የባንኩ ብድርና ስጦታ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን ለመቀነስና ኃይልን በጥራት ለማቅረብ የሚያስችል ነው። የኃይል ማስፋፊያና ማሰራጫ ትራንስፎርመሮችን ዳግም ለማደስና በአዲስ መልክ ለመገንባት የሚያካትት ነው። ይህ ድጋፍም የአዲስ አበባን ኤሌክትሪክ መስመሮች ከማሻሻል ባሻገር የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲያችንን ለማገዝ የታለመ መሆኑ ግልፅ ነው።

 

ርግጥ ድጋፉ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመንደፍ ለታዳሽ ሃይል ትኩረት የሰጠች ሀገር ነች። የኃይል ልማት ፖሊሲው ከነባሩ ወይም ባህላዊ መንገንድን ተከትሎ ከሚደረገው የሃይል ማመንጨት ስራ ቀስ በቀስ ዘመናዊ የሃይል አጠቃቀም መከተልንና መሸጋገርን ማዕከል ያደረገ ነው።

 

አስተማማኝ የሃይል አቅርቦትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም የማዳረስና ለኢኮኖሚውም ዕድገት በቂ ሃይል የማቅረብ ሃሳብንም የያዘ ነው።  ፖሊሲው ለሀገር ውስጥ የሃይል ምንጭ ቅድሚያ በመስጠት ራስን መቻልን ያልማል። እንዲሁም ንፁህ ሃይልን ቆጥቦ በብቃት በመጠቀም የአካባቢ የአየር ሁኔታ ጤናማነትን በማስቀጠል የበኩሉን ሚና ለመጫወት ያለመ ነው።

 

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባልተራዘመ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ ራዕይ አላት። የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ በተከታታይ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ያላት የኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር ሆኖ እንደምትቀጥልም አየተነበዩ ነው፤ ሁሌም በየዓመቱ።

 

ይህን ስኬታማ ለማድረግ የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ልማቱ መሰረት ማድረግና የኤክስፖርት ደረጃን ለማሳደግ ታስቦም እየተሰራ ነው። ውጤትም እየተገኘ ነው። ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ራዕይዋን እውን ማድረግ የሚቻለውም ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ፈተና ሆኖ የተጋረጠውን የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት መዋጋትና ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ሲቻል መሆኑ ከግንዛቤ እንዲገባ ተደርጎ ስራው በመከናወን ላይ ይገኛል።

 

የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ሃብት እጥረት ነዳጅን በማስገባት በሚወጣ የውጭ ምንዛሬ ምክንያት የሚመጣ የተፈጥሮ ክስተት ነው። ይህ ክስተት በተለይ ልማታቸውን በተፈጥሮ ዝናብ ላይ ጥገኛ ያደረጉ ሀገሮችን የሚጎዳ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

 

በዚህ ስትራቴጂ የሚወሰዱ ርምጃዎች ሁሉ ለኢንቨስትመንት አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጡና የኢኮኖሚ ዕድገትን በቀጥታ ከሚያፋጥኑ ከተጨማሪ እሴቶች ጋር የስራ ፈጠራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስትራቴጂው የዓለም የሙቀት መጠንን በመቀነስ ረገድ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ሃላፊነቷን እንድትወጣ የሚያስችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የስራ ዕድልን ይፈጥራል።   

 

ርግጥ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ኢትዮጵያ በቀጣዩቹ ዓመታት 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል። ታዲያ ይህን ግብ ለመድረስ በሁለትዮሽ ግንኙነት አማካኝነት ከሚካሄዱ የዲፕሎማሲ ስራዎች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንዲሁም የግሉ ሴክተር ከሚጫወተው ሚና ጋር ተገናዝቦ ገቢራዊ እየሆነ ነው። እንዲሁም ሀገሪቱና አህጉሪቱ ለአለም አየር ንብረት ለሚያደረግት የታዳሽ ሃይል ስራዎች በጎ አስተዋጽኦ ማካካሻ የገንዘብ ድጋፎች ታሳቢ ሆነው ይቀርባሉ።

 

ርግጥ እዚህ ላይ ‘ለኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይል ለምን ያስፈልጋታል?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ይህም የአረንጓዴን ልማት ስትራቴጂ ፋይዳ የሚያመላክተን ይሆናል።  በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት ሀገራት ውስጥ ቻይናን እና ህንድን ብቻ ብንወስድ፤ እያንዳንዳቸው ከዚህ በፊት የዓለም ፍጆታን በሞኖፖል ከያዘው ክፍል በእጥፍ የሚበልጥ ህዝብ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሀገሮች በፍጥነት እያደጉ በሄዱ ቁጥር የተፈጥሮ ሃብት ምርቶች ፍላጎታቸው በዚያው ፍጥነት አድጓል።

 

በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተኪ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ማፍራት የሚቻል ቢሆንም፤ የተፈጥሮ ሃብትን ሙሉ በሙሉ መተካትና ህዝቦች ያላቸውን ፍላጎት በፍጥነት መቀነስ ግን አይቻልም። እናም አዳዲስ የኢኮኖሚ ማዕከሎች እየተፈጠሩ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ የተፈጥሮ ሃብት ምርቶች በተለይም የማዕድናትና የግብርና ምርቶች ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

ይህም የተፈጥሮ ሃብት ተፈላጊነቱ እየጨመረ እንጂ እያነሰ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታም የተፈጥሮ ሃብት እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም። የዓለም የተፈጥሮ ሚዛን ክፉኛ ሊናጋም ይችላል። እናም የተፈጥሮ ሃብትን በከፍተኛ መጠን ለመቆጠብ የሚያስችሉ እንደ የታዳሽ ሃየል ምንጮችን መፍጠር የግድ ይላል።

 

ታዳሽ ሃይልን መጠቀም በአየር ጠባይ ለውጥ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው።  ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ የሚከተሉት የዕድገት አቅጣጫ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኢነርጂ አላቂ ከሆኑት የካርቦን ኬሚካሎች በማመንጨት ላይ የተመሰረተ ነው። እነዚህ የሃይል አማራጮች አላቂ ከመሆናቸውም በላይ የሚለቁት ካርቦንዳይአክሳይድ መጠን አየር ላይ እየተከማቸ የመሬትን ሙቀት ይጨምራል። ይህም አሁን ባለው ልኬት መሰረት የካርቦን መጠኑ የዓለምን ሙቀት ቢያንስ በአማካይ ሁለት ዲግሪ ሴንቲግሪድ እንዲጨምር ያደርገዋል ተብሎ ይገመታል። በዚህ ሳቢያም በሰሜንና በደቡብ ዋልታዎች የተከማቸው ከፍተኛ ቦረዶ ኮረብታዎች ይቀልጣሉ። ይህም መላው ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገሮችን የአየር ንብረት በመለወጥ ለድርቅ ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው።

 

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ አህጉር ምንም እንኳን በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት ሀገራት ጋር እኩል ካርቦንዳኦክሳይድ በመልቀቅ በአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ሚና ያላት ባይሆንም፤ በሚደርሰው የአየር ንብረት ብክለት ግን ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ እየሆነች ነው።

በተለይም የአየር ንብረቱን ለመቀጣጠርና ሚዛናዊ ለማድረግ የሚጠቅሙትን ደኖች በመጨፍጨፍ ለተለያዩ ሃይል መጠቀሚያነት እንዲውሉ ማድረግ አህጉሪቱን በድርቅ አደጋ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት ነው።

 

በሀገራችን በየጊዜው የሚከሰተው የድርቅ አደጋ የዚህ እውነታ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። እናም ኢትዮጵያ ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይና ከስኳር ተረፈ ምርቶች እንዲሁም ከጂኦተርማል ታዳሽ የሃይል ምንጮች ሃይልን በማመንጨት የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር የወሰነችው ከዚህ በመነሳት ነው።

 

እዚህ ላይ የታዳሽ ሃይል አጠቃቀማችንን ለማሳየት አንድ ሰሞነኛ ምሳሌ ላንሳ። ሰሞኑን በርከታ መገናኛ ብዙሃን በአፍሪካ የመጀመሪያው የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ እንዲሁም የኃይል ማመንጫ በአዲስ አበባ ቆሼ ወይም ረጲ ተገንብቶ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ የሚገልጽ ዘገባዎች አስነብበውናል። ይህ የረጲ የኃይል ማመንጫ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በቆሼ የተከመረውን የአዲስ አበባ ቆሻሻ ወደ ኃይል በመቀየር ለከተማዋ የ30 በመቶ ቤቶችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደሚሸፍን የሚጠበቅ ነው።

 

ፕሮጀክቱ የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህም ኢትዮጵያ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ታዳሽ የኃይል ምንጭን በመጠቀም የአየር ብክለትን ለመከላከል የዘረጋችው ስትራቴጂ አካል ሆኗል። በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዋ ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች። ከብክለት የነፃ አካባቢን በመፍጠር ረገድ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ፓሊሲ አፍሪካዊ ብሎም ዓለም አቀፍ ኃላፊነቷን በግንባር ቀደምትነት እየተወጣች ያለች ሀገር እንድትሆንም አድርጓታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy