አርሶ አደርና በሬን፣ ወደ አርሶ አደርና ማሽን
ብ. ነጋሽ
ያለንበት ወቅት የመኸር ምርት መሰብሰቢያ ወቅት ነው። አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ ሥራ በሚከናወንበት ክረምት የተዘሩ ሰብሎች ከህዳር እስከ ጥር ባሉት ወራት ተሰብስበው ይገባሉ። እናም በመላ አገሪቱ አርሶ አደሩ ምርቱን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል። በ2009 ዓ.ም የክረምት እርሻ 12 ነጥብ 7 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኗል። አሁን በመሰብሰብ ላይ ያለው ይህ በክረምት የታረሰ ሰብል ነው። ከዚህ የሰብል እርሻ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ባለው የመስመር እርሻ የለማ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ከዘንድሮ የመኸር ምርት በአጠቃላይ 345 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይጠበቃል። በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ ስምንት በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከፍተኛ መጠን ያለው እርሻ ምርታማነትን በማሳደግ ትልቅ ድርሻ ባለው የመስመር እርሻ የለማ መሆኑ፣ በርካታ አርሶ አደሮች የብጥስጣሽ እርሻን ለመቋቋም ኩታ ገጠም ማሣዎችን በጋራ ማልማታቸው፣ በበርካታ አካባቢዎች ምርታማነትን በእጅጉ የሚቀንሱ አሲዳማ መሬቶች በኖራ በመታከማቸው፣ የማዳበሪያ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ በማሳየቱ በሁሉም አርሶ አደር ሊባል በሚችል ደረጃ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉ፣ ከተሻሻለ ዘር ጋር ያለው ትውውቅም እያደገ መምጣቱ በዓመቱ የታሰበው 345 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ሊሰበሰብ እንደሚችል ያመለክታል። ይህ ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው 293 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲወዳደር ጉልህ ብልጫ አለው። የዘንድሮ ተጨባጭ የምርት ውጤቱ ምን እንደሚመስል ከወራት በኋላ የሚታወቅ ይሆናል።
አርሶ አደሩ በማሣ ላይ ሥራው ምርታማነቱን ማረጋገጥ መቻሉ በራሱ የሚፈለገውን ምርት ለመሰብሰቡ ዋስትና አይደለም። ባህላዊው የምርት አሰባሰብ – ከአጨዳ ጎተራ እስከ ማስገባት ባለው ሂደት በርካታ ምርት ይባክናል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስካሁን ባለው ባህላዊ የምርት አሰባሰብ ዘዴ 30 በመቶ ያህል የሚሆነው ምርት ይባክናል። በያዝነው ዓመት የሚጠበቀውን 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የመሰብሰብ ተግባር እንዲሳካ የምርት አሰባሰብ ላይ ያለውም አሠራር ወደዘመናዊነት መለወጥ አለበት።
በዚህ ረገድ በያዝነው የመኸር ምርት ስብሰባ የተሻለ ሁኔታ ታይቷል። ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለባቸውና የመሬቱ አቀማመጥ አመቺ በሆነባቸው አካባቢዎች በተለይ የስንዴ ምርት በኮምባይነር የሚሰበሰብበት ሁኔታ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። በኮምባይነር ምርት መሰብሰብ በማይቻልባቸውና ከቴከኖሎጂው ጋር ባልተዋወቁ አካባቢዎችም ቢሆን የተመጣጣኝ ቴክኖሎጂ መውቂያዎችን መጠቀም በስፋት ይስተዋላል። ከዚህ በተጨማሪ በአነስተኛ ማሣ ላይ በተለይ የስንዴ ምርትን ማጨድ የሚያስችል አነስተኛ ማሽን በመተዋወቅ ላይ ነው። በአንድ ቀን አራት ሄክታር ድረስ ማጨድ የሚችለው ይህ በመተዋወቅ ላይ ያለ አነስተኛ ማሽነሪ ለአንድ ቀን ውሎ አንድ ሊትር ነዳጅ እንደሚጠቀም በባለሞያ ተገልጿል። ይህ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ መዋል ሲጀምር አሁን ከፍተኛ የምርት መሰብሰቢያ ሜካናይዜሽን መጠቀም አለመቻል የፈጠረውን ክፍተት መሙላት ይቻላል። ቴክኖሎጂው ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ሊፈጥር የሚችልበት ሁኔታም አለ። ወጣቶች ተደራጅተው ይህን ማሽን በመግዛት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ የአጨዳ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት እድል አለ። ከአርሶ አደሮች የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ ሄክታር መሬትን በተቀጣሪ ሠራተኛ ለማሳጨድ ከስድስት መቶ እሰከ ዘጠኝ መቶ ብር ወጪ ይጠይቃል።
ከዚህ በተጨማሪ እስከ ቅርብ ዓመታት ምርቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ተወስኖ የቆየውን የጤፍ ሰብል መሰብሰብ የሚያስችል ማሽነሪ ሥራ ላይ የማዋል ጉዳይ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል። እስካሁን የጤፍ ሰብልን የሚወቃ አነስተኛ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ውሏል። ምን ያህል የጤፍ አልሚ አርሶ አደሮች ከዚህ ተመጣጣኝ ቴክኖሎጂ ጋር እንደተዋወቁ የሚያመለክት መረጃ ግን የለም። በአገሪቱ ቀዳሚ የፍጆታ ሰብል፣ ዋጋውም ከፍተኛ የሆነውና አርሶ አደሩም ለማልማት የሚመርጠው የጤፍ ሰብልን ምርታማነት ለማሳደግ ከምርጥ ዘርና ከአስተራረስ ሥልት ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ የተሻሻለ ቴክሎጂን ሥራ ላይ መዋል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግና ገበያውን ከማረጋጋት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
የግብርና ዘርፍ ምርታማነት ማደግ ለኢትዮጵያ የአጠቃላይ ኢኮኖሚ ማደግ አለማደግ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ኢትዮጵያ የአርሶና አርብቶ አደር አገር ነች። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማራ ነው። አሁን ባለንበት ወቅት የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 36 ነጥብ 3 በመቶ ገደማ ድርሻ አለው። የኢንዱስትሪው ዘርፍ 25 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ ሲኖረው የአገልግሎት ዘርፉ 39 ነጥብ 3 በመቶ ነው። ባለፉት አንድ ተኩል አሥርት ዓመታት ኢኮኖሚው ተከታታይ እድገት ሲያስመዘግብ በዚህ ውስጥ ግብርና ትልቁን ድርሻ ይዞ ቆይቷል። በቅርቡ የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ የበላይነት እስከያዘበት ጊዜ ድረስ የግብርናው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ቀዳሚ ነበር። የግብርናው ዘርፍ በአገሪቱ የወጪ ንግድ ውስጥ ያለው ድርሻ አሁንም በጉልህ ከፍተኛ ነው። ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም ከብት የመሳሰሉት የግብርና ምርቶች 80 በመቶ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ይሸፍናሉ። የግብርና ዘርፍ የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ የሚያደርገው ከላይ የተገለጹት እውነታዎች ናቸው። የግብርናው ዘርፍ እድገት የአገሪቱን ዜጎች የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድም ምትክ የሌለው ነው። ምርታማነትን በማሻሻል ገቢያቸውን በማሳደግ ዜጎችን ከድህነት በማውጣት ኑሯቸውን ለማሻሻል ከ80 በመቶ በላይ ህዝብ ለተሰማራበት ግብርና ትኩረት መስጠት ምትክ አማራጭ የለውም። የግብርናውን ዘርፍ ችላ ብሎ የህዝቡን ኑሮ ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የማይታሰብ ነው።
መንግሥት ይህን ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ገጠርና ግብርና ላይ ያተኮረ የልማት ፖሊሲ ነድፎ ተግባራዊ አድርጓል። የዚህ ፖሊሲ ተግባራዊነት የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ገቢ ማሻሻል አስችሏል። የአርሶ አደሩም ኑሮ በዚሁ በገቢው እድገት ልክ መሻሻል አሳይቷል። ኑሯቸውን ወደተሻለ ደረጃ ከማሸጋጋር አልፈው ወደኢንቨስተር ባለሃብትነት የተሸጋገሩ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ምንም ያልነበራቸው አርሶ አደሮችንም መፍጠር ተችሏል። ይህ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ አጀንዳ በመሆኑ በሌላ ጽሁፍ ለመመልከት ትቼው በአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ሚና ወደመመልከት ልመለስ።
ከላይ እንደተጠቀሰው የግብርናው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ አሁንም ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የግብርናው ዘርፍ እድገት ወሣኝ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ በአጠቃላይ አገራዊ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆን አገራዊ የካፒታል ክምችት በመፍጠር የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግና ወደኢንዱስትሪ መር ለማሸጋጋር የማይተካ ሚና አለው። እናም የግብርናው ዘርፍ ልማት አሁንም የትኩረት መሠረት መሆን ይገባዋል።
የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ልማት ፈተና የእርሻና የምርት አሰባሰብ በቴክኖሎጂ የታገዘ አለመሆን ብቻ አይደለም። ግብርናው በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆኑም ሌላው ፈተና ነው። በእቅድና በፖሊሲ በቁጥጥር ሥር ሊውል የማይችለው የአየር መዛባት የሚያስከትለው ድርቅ ደግሞ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን ግብርና ክፉኛ እየጎዳው ነው። በመሆኑም የእርሻ ሥራ ወቅት ተከል ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚከናወንና ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ እንዲሆን የመስኖ እርሻን ማስፋፋት አማራጭ የለውም። የመስኖ እርሻን ለማስፋፋት ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በዚህ ዘርፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተጨባጭ መሻሻሎችን ማሳየት ተችሏል። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2009 በጀት ዓመት በአገሪቱ በመስኖ ከለማው 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል። በዚህም ሰባት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነው የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ሃብት ማከማቸት የጀመሩም አሉ።
ዘንድሮም የመኸር ወቅት የሰብል ስብሰባ እየተጠናቀቀ መምጣቱን ተከትሎ ሰባት ሚሊየን ያህል አርሶ አደሮች ለመስኖ ሥራ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል። አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው የሚገኝ ውኃን በመጠቀም ወደ መስኖ ልማት ሥራዎች ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ዘንድሮ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት፣ ከ469 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የተለያዩ የአትክልትና ልዩ ልዩ የግብርና ምርቶችን ለማልማት ዝግጅት ተደርጓል።
ከተሻሻለ የእርሻ ሥልት፣ ግብዓቶች አጠቃቀም እንዲሁም ከሜካናይዝድ የምርት ስብሰባ ጀምሮ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ወሣኝ ድርሻ ያለውን የግብርና ዘርፍ ልማት ለማፋጠን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው። የግብርናውን ዘርፍ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ማሳደግ ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ ለከርሞ ከዘንድሮ የተሻለ የማምረት አቅም እንዲኖረው ማድረግ የሚፈልግ መሆኑም ሊታሰብበት ይገባል። ይህ ደግሞ በዋናነት አርሶ አደሩ የልፋቱን ያህል ተጠቃሚ የሚሆንበትን የገበያ ሥርዓት መዘርጋትን የሚጠይቅ ነው። በአጠቃላይ የበሬና የአርሶ አደርን ቁርኝት ወደ ማሽንና አርሶ አደር ቁርኝት ለመቀየር ብሎም በመስኖ ልማት ግብርናን የዓመት ሙሉ ሥራ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።