Artcles

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም እያነሣ  የሚጥላት አይደለችም!

By Admin

December 18, 2017

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም እያነሣ  የሚጥላት አይደለችም!

አባ መላኩ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች ተፈቃቅረውና ተከባብረው እንዲሁም ተቻችለው  የሚኖሩባት አገር ናት። ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለቀጠናው አገራት ዘላቂ  ሰላም የሚተጋ  ጠንካራ መንግስት ያላት  አገር ናት።  አንዳንድ ቅን አስተሳሰብ ያላቸው ወይም የዋህ  ዜጎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በሚስተዋሉ  የትምክህትና ጥበት ሃይሎች አካሄድ አገር የምትፈርስ ህዝብ እርስ በርሱ  የሚጫረስ መስሏቸው ስጋት ተስምቷቸዋል። ይህ አስተሳሰብ ክፋት አለው ብዬ አላስብም። ስጋቱም ምክንያታዊ አይደለም ብዬ መከራከር አልፈልግም። ይሁንና ኢትዮጵያ   ማንም  ተነስቶ ዕለቱን የሚያፈርሳት፣ የተውገረገረች  አገር እንዳልሆነች ግን በዕርግጠኝነት መናገር  ይቻላል። ህብረተሰባችን ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር ያለው ሃይማኖተኛ በርካታ የጋራ እሴቶች  ያሉት ህዝብ ነው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ  በህዝቦች ደምና አጥንት የተገነባች ህገመንግስታዊ አገር ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናስተውላቸው  ምክንያታቸው በርካታ የሆኑ  ችግሮች  አሉ። መንግስትም በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት  ችግሮች መኖራቸውን ተቀብሎ ለችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ የሚያደርገው ጥረት እንዳለ እንመለከታለን።  የአገራችንን ችግሮች ጠለቅ ብለን ብንመረምራቸው የበርካታዎቹ ችግሮች  ምንጫቸው የግል ጥቅም ፍለጋ (ኪራይ ሰብሳቢነት) ነው።  የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ከሆኑ ነገሮች መካካል ዋንኞቹ  የጥበትና ትምክህት አስተሳሰብና ተግባር ነው።

ጠባቦችና ትምክህተኞች  የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ስኬት አይፈልጉም። የእነዚህ ሃይሎች መደበቂያ ሃይማኖትና ብሄር ነው።  ለእነዚህ የጥፋት  ሃይሎች  የህዝቦች አብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት አይታያቸውም።  የጥበትና ትምክህት  ሃይሎች  ዓላማቸውን ለማሳካት  ሁሌም  ነውጥና ሁከትን  ይመርጣሉ። ነውጥና ሁከት መፍጠርና በተለይ በብሄሮች መካከል የሚደረግ ግጭት የጥፋት ሃይሎች ዋንኛ ስትራቴጂ ነው። አሁን ላይ ይህ ሃይል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው በከፍተኛ ትምህርት ላይ ነው።  ዩኒቨርሲቲዎች  ከትምህርት ተቋምነት ወደ  ነውጥና ሁከት እንዲያመሩ ወላጆች ልጆቻቸውን  ከትምህርት ገበታቸው ላይ  ነጥለው እንዲወስዱ የተለያዩ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ላይ ናቸው።

የጥበትና ትምክህት  ሃይሉ የጽንፈኛው የዳያስፖራ  ሚዲያዎችንና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን  በመጠቀም  አገር እንዳበቃላት  አድርገው የተለያዩ መረጃዎችን በመንዛት ላይ ናቸው። አሁን ላይ የጥበትና ትምክህት ሃይሉ  ግንባር ፈጥረው አገር የሚያፈርስ እጅግ መርዛማ መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቦችን ዕርስ በርስ  ለማጋጨት ተግተው በመስራት ላይ ናቸው።  ነውጠኛ ሃይሎች  ድብቅ አጀንዳቸውን ለማሳካት ትኩረት አድርገው እየሰሩ ያሉት ደግሞ  ወጣቱ ላይ ነው።  የበሬ ወለደ ታሪክ በማቀነባበር ወጣቱን  ስሜታዊ የሚያደርጉና    ለጥፋትና በቀል የሚያነሳሱ መረጃዎችን  በማሰራጨት አገር ልትፈርስ እንደሆነ በማስመሰል ህብረተሰቡ ላይ ስጋት ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ አይነት ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ለማንም የሚበጅ አይደለም። የመልካም አስተዳደር ችግሮች  በተላይ ወጣቶችን በተመለከተ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት  ሰላም ሲረጋገጥ እንጂ በአመጻና ነውጥ አይደለም።

የነውጥ ሃይሎች  የጥፋት ተልኳቸውን ትኩረት አድረገው እየሰሩ ያሉት  የብሄር  ግጭቶች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ ማድረግ ላይ  ነው። ግጭቶች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ  ከማድረግ ጎን ለጎን በመልካም አስተዳደር በማጓደል በህዝብ  ተገምግመው ከሃላፊነታቸው የተሰናበቱ  ግለሰቦችን በማስተባበር በመንግስት ላይ ዘመቻ መክፈት  እንደአንድ ዘዴ እየተጠቀመበት ነው።  እነዚህ የጥፋት ሃይሎች  በዚህ አያበቁም በመልካም አስተዳደር ችግሮች የተማረሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያየ ዘዴ  በመንግስት ላይ   ማነሳሳት ነው።  መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን አምኖ  ከህብረተሰቡ ጋር  መፍትሄዎችን በመስጠት ላይ ነው።     

መልካም አስተዳደር ማስፈን የዕለት ተግባር  አይደለም። ሁለም ችግሮች ዕለቱን አይፈቱም።  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ  መንግስት  የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። ይህ የመንግስት ጥረት ውጤታማ የሚሆነው በህዝብ ተሳትፎ  ሲታገዝ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይገባል።  በየትኛውም መስክ ለጥፋት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት አንዱ የመንግስት ተግባር መሆን ይገባል። የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና  ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል  ያስፈልጋል። ህዝቡ የነውጥና የሁከት  ጋሻጃግሬዎች  እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም እነዚህን አካላት ለህግ አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል።

መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩትን ጉድለቶች ለማስተካከልና  የህዝብን ፍላጎትን ለማሟላት  የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። እስካሁንም መልካምናም ተጨባጭ   ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው። ይሁንና አንዳንድ አካላት  ለምን  ሁሉም ነገር በአንዴ አልተስተካከለም ወይም አልተፈጸመም  በማለት ህብረተሰቡን ለነውጥና ለሁከት የሚያደርጉትን ሩጫ ማጋለጥ ተገቢ ነው። መንግስት ካቢኔን እንደገና እስከማዋቀር፣ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የሚገኙ ህግ የተላለፉ አስፈጻሚዎችና ፍጻሚዎችን ህግ ፊት የማቅረብ  እርምጃዎች ወስዷል። በመወሰድ ላይም ይገኛል።  ይሁንና አሁንም በርካታ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል።  ሁሉም ነገር ዕለቱን መፍትሄ ያገኛል ማለትም አይደለም።  ይሁንና በሂደት ነገሮች በመስተካከል ላይ ናቸው።  

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ የመንግስት ሚና ወሳኝ ቢሆንም  ካለህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ የታሰበው ዓላማ ሊሳካ አይችልም። ለመልካም አስተዳደር  መረጋገጥ ቁልፉ ጉዳይ አሰራር መዘርጋት ነው።  አንዳንድ   አካላት  የመንግስት ሹማምንቶችን ከኃላፊነት ቦታቸው በማንሳት ወይም በማሰር መልካም አስተዳደርን የሚረጋገጥ መስሏቸው ከራሳቸው ፍላጎት በመነሳት እከሌ ከሃላፊነት ካለወረደ፤ እከሌ ካልታሰረ ወዘተ በማለት  መንግስት  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያደርገውን ትግል ለማኮሰስ የተለያዩ  ውዥንብሮችን  በመንዛት ላይ ናቸው።  በእርግጥ ጥፋተኛ መጠየቅ ይኖርበታል፤ ነገር ግን ተጨባጭ ማስረጃ  ባለተገኘበት ሁኔታ  ማንንም  ከህግ ፊት ማቅረብ ደግሞ የግለሰቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጋፋት ነው። ህገመንግስታዊ አካሄድም አይሆንም።  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁልፉ ነገር በማንኛውም ተቋም ውስጥ የአሰራር ስርዓት  መፍጠር፣ ተጠያቂነትን ማንገስ፣ ህብረተሰቡም አገልግሎት ለማግኘት የሚጠበቅበትን  መብትና   ግዴታ ጠንቅቆ  ተገንዝቦ መብቱን ማስከበር እንዲሁም ግዴታውን እንዲወጣ ተገቢውን ድጋፍ  ማድረግ  እንጂ ፈጻሚን በየጊዜው በመቀያየር የተፈለገውን ውጤት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም።   

በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ። አንዳንድ ግለሰቦች  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ  ሁሉንም ችግሮች ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ለማስተሳሰር የሚያደርጉት ጥረት ሊወገዝ ይገባል።  ለአገራችን የሚበጃት  ሁሉንም  ችግሮች  በየፈርጁ ብንመለከታቸውና   በጋራ ሆነን መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ  በነውጥና ሁከት መፍትሄ እናመጣለን ማለት  ለአገራችንም ለህዝባችንም የሚበጃት አይሆንም። ስሜታዊነት ህዝብ ያጋጫል፣ አገርንም ያፈርሳል።  ስሜታዊነት  ምክንያታዊ እንዳንሆን  ያደርጋል። በአገራችን የሚስተዋሉ ሁሉም ችግሮች የመልካም አስተዳደር ችግሮች አይደሉም። በመንግስት የአቅም እጦት መንገድ ያልተዘረጋላቸው ወይም ውሃና ኤሌክትሪክ  ያልቀረበላቸው  አካባቢዎች  የመልካም አስተዳደር ችግር ተደርጎ መወሰድ የለበትም።  

ለአገራችን የሚበጃት ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መሆን መቻል ይኖርብናል።  በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የፊት ለፊት ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ መድረኮችን በማድረግ ላይ ነው። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ቢሆንም፤ መነጋገርና መወያየት  የሚያስችል  ፖለቲካዊ ስርዓት  በመገንባት ላይ ነው።  ይህን መልካም ጅምር ልንጠቀምበት ይገባል። መስማማት ወይም አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ፤  ቁጭ ብሎ መነጋገር  መቻል  በራሱ የመጀመሪያውና ትልቁ መልካም  ነገር ነው።  

ባለፉት 27 ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 15 ዓመታት በአገራችን በርካታ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያጎለብቱና የሚያፋጥኑ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። እየተመዘገቡ ካሉ  ስኬቶች ህብረተሰቡ በየደረጃው  ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት  እየተደረገ ነው። ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል። ይሁንና መልካም አስተዳደር በማስፈን ረገድ ያልተፈቱና ህዝቡን እያማረሩ  ያሉ በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች  መኖራቸው  ገሃድ ነው። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እያንዳንዱ ዜጋ  ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ  የመንግስት ጥረት ብቻውን ውጤታማ ሊሆን አይችልም።