Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲስ አበባን ውብ ማድረግን ያለመ ዘመቻ

0 712

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲስ አበባን ውብ ማድረግን ያለመ ዘመቻ

                                                                                        ይልቃል ፍርዱ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ፤ እናንተስ? የሚለውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳታፊነት የተጀመረው አዲስ አበባን ጽዱና ውብ የማድረግ ዘመቻ ከእንግዲህ በኋላ በወር አንድ ግዜ በእቅድ ውስጥ ተካቶ በቋሚ ፕሮግራምነት ተይዞ መቀጠል የሚገባው ታላቅ ተግባር ነው፡፡

አመታት እየተቆጠሩ በሄዱ ቁጥር ወደ ቋሚ ባሕልነት ስለሚቀየር የግድ ሕብረተሰቡ
በየወሩ እየወጣ በጋራ፤ የአካባቢውን ብሎም የከተማውን ውበት የሚያጠፉ ቆሻሻዎችን ያጸዳል፡፡ በአሁኑ ሰአት አዲስ አበባ የአፍሪካ አሕጉርና የአለም የዲፕሎማሲ ከተማ ለመሆን ብትበቃም ይህን ታላቅ ክብርና ደረጃ ይዛ የመጨረሻዋ በቆሻሻ የተሞላች ከተማ መሆንዋ ደግሞ እጅግ በጣም ሊያሳፍረን ይገባል፡፡

የዚህ ጉዳይ ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቆሻሻን መጸየፍና ማስወገድ ከቻለ በቀበሌ፤ በክፍለ ከተማ፤ በክልል ደረጃ ከተማዋ ጸዳች ማለት ነው፡፡ እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ እናንተስ? የሚለው መሪ ቃል ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡ የራስን ቤትና ግቢ ብሎም አካባቢን ንጹሕና ጽዱ የማድረግ በአጠቃላይ ሁሉንም የከተማዋን ክፍሎች  ንጹህ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ መልካም ጅምር በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ በጥሩ ምሳሌነቱ ተወስዶ ሊሰራበት ልምድና ባሕል ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

እንዲያውም በየወሩ በተመረጠ የሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀናት በአንዱ ቋሚ ሁኖ በዘመቻ መልክ ቢሰራበት ውጤታማ ይሆናል፡፡ ይህን ጉዳይ የሚያስተባብሩ የሚመሩ ሕብረተሰቡን ለጽዳት ዘመቻው ስራ በየወሩ እንዲሳተፍ የሚያደርጉ ቋሚ የኮሚቴ አባሎችን በየቀበሌው በመምረጥ እነዚህም ሕብረተሰቡን እንዲያነቁ እንዲያስታውሱ በየወሩም ለጽዳት ዘመቻው ኃላፊነትን እንዲወጣ በማድረግ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡

እንደምናየው አዲስ አበባ ከተማ በቆሻሻ ተሞልታለች፡፡ በዚህ ክርክር ውስጥ የሚገባ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ ለፍሳሽ ማስወገጃ ተብለው በየሰፈሩ በየመንደሩ የተሰሩት የውሀ መውረጃዎች በሚጣሉ የውሀ መያዣ ሀይላንዶችና በቆሻሻ ፌስታሎች ተሞልተዋል፡፡ አስከፊ የሆነው ሽታ በአካባቢው ለማለፍ ይሰነፍጣል፡፡ ክርፋቱ አፍንጫን ሰርሳሪ መጥፎ ሽታው፤ በተለይ የከረረ ጸሀይ ሲወጣ የሚፈጥረው ትነት ምን ያህል በጤና ላይ ችግር እያስከተለ እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ስለ እውነቱ እንነጋገር ከተባለ አዲስ አበባ ከመጠን በላይ ቆሽሻለች፡፡ የተላላፊና የወረርሽኝ በሽታዎች መቀፍቀፊያ ጎሬ ወደ መሆን እያዘገመች ነው፡፡ ቢቸግራቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እስቲ ምሳሌ ልሁን ብለው በጽዳት ዘመቻው መጥረጊያ ይዘው የተሰለፉት፤ ተግባራቸው እሰየውም ያስብላል፡፡

በተለያ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ወደ ትምሕርት ቤት የሚሄዱ ሕጻናት የአካባቢው ነዋሪዎች ለማንሳት ቢሞከር በየግዜው እየሞላ በሚጠራቀመው ቆሻሻና በሚያስከትለው መጥፎ ሽታ ምን ያህል በበሽታው እንደሚጠቁ ለመገመት አይከብድም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አዲስ አበባ ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር ቆሽሻለች፡፡ የሰፈሮቻችን ቦዮች ወንዞቻችን በሙሉ ከመጠን በላይ ከመቆሸሻቸውም በላይ በመርዝና በበሽታ አምጪ ተዋህስያን ተበክለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ስምና አዲስ አበባ አልተገናኝቶም፡፡

አብዛኛው ዜጋ ቆሻሻን በተመለከተ ከቤቱ አውጥቶ መጣሉን እንጂ  በራሱ ልጆችም ሆነ በሕብረተሰቡ ላይ ምን አይነት የከበደ የጤና ችግር ያስከትላል የሚለውን ለአፍታም አያስተውለውም፡፡ በአጭሩ ኃላፊነት አይሰማውም፡፡ ጭርሱንም ቆሻሻን ተላምዶ የሚኖር ነው የሚመስለው፡፡ ይህን በሰዎች ውስጥ ነፍስ ዘርቶ የተተከለን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ የሚያስችል ሰፊ ስራ እስካልተሰራ ድረስ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አይቻልም፡፡ አዲስ አበባም ቆሻሻን መለያዋ አድርጋ ትቀጥላለች ማለት ነው፡፡

ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርአያነት የተሳተፉበትና እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ እናንተስ? በሚለውን መሪ ቃል የታጀበ፤ ታላቅ ተነሳሽነትነ የፈጠረ፤  አካባቢንም ሆነ በአጠቃላይ ከተማዋን ጽዱ ሊያደርግ የሚችል ፕሮግራም የተከናወነው፤ በመሆኑም አጠንክርን ልንገፋበት የገባል፡፡ የተለያዩ ሀገራት ከተማቸውን በአጠቃላይ ጽዱና ለጤና ተስማሚ በማድረግ ረገድ የሚከተሏቸው ደንቦችና መሪያዎች አሉ፤ ያም ያስፈልገናል፡፡

ስልጡን በሚባሉትና ባደጉ ሀገራት ነዋሪ ዜጎችም ሆኑ የውጭ ሀገራት ዜጎች ቆሻሻን በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር የትም እንዳገኙት እንዲጥሉ አይፈቀድላቸውም፡፡ በየትኛውም የከተማዎቹ ሰፈሮች፤ መንገዶችና አውራ ጎዳናዎች፤ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፤ የአውቶቡስ መናሀሪያዎች፤ የባቡር ጣቢያዎች፤ የመስሪያ ቤትና የቢሮ አካባቢዎች ወዘተ የቆሻሻ መጣያ የተለያየ መጠን ያላቸው በርሜሎች አላቸው፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች ውጭ በምንም መልኩ ቆሻሻን መጣል አይቻልም፡፡ በስህተት የወደቀ ቆሻሻ ወረቀት ቢገኝ እንኳን ማንኛውም ሰው አንስቶ ወደ በርሜሎቹ ያስገባል፡፡ ቆሻሻ ያለቦታው መጣል ነውርና አሳፋሪም ነው፡፡

ለዚህ ነው አዲስ አበባ እንደ ስምዋ የምታምር አበባ መሆን ተስኖአት ከጥግ እስከ ጥግ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መሆን ደረጃ ላይ የደረሰችው። ይሄ ያሳፍራል፤ ያሳዝናልም፡፡ በእርግጥ በምርጥ ተምሳሌትነት በጽዳት አያያዛቸው የሚጠቀሱ ቦሌን የመሳሰሉ አንዳንድ አካባቢዎች አሉ፡፡ እነዚህ የተመረጡ ቦታዎች አብዛኛውን ዋናውን የከተማዋን ክፍል አይወክሉም፡፡

ገና በብዙ መልኩ መሰልጠን ዘመናዊ መሆን የቤታችንንና የአካባቢያችንን ንጽሕና ጽዱ አድርጎ የመኖር ልምዱና ባሕሉ ይጎለናል፡፡ ከተማችን በቆሻሻ አድፋለች፡፡ ተጥለቅልቃለች፡፡ ይህ ሊሰማን ይገባል።  

መቸም ምክንያትና ሰበብ ወዳድ ነንና በገዘፈ ሁኔታ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከመንቀሳቀስ  ይልቅ ራሳችንን ከተጠያቂነት ለማዳን የማናቀርበው የመከላከያ ሀሳብ አይኖርም፡፡ ምንም ተባለ ምን ኃላፊነቱ፤ ተጠያቂዎቹ ነዋሪዎችዋ  እኛና እኛ ብቻ ነን፡፡

ቆሻሻው ሰፈሩን መንደሩን አካባቢውን የሚበክለው ከየቤታችን እየወጣ እየተጣለ  ነው፡፡ ይህንን በስርአቱ በተለየ ቦታ ማስወገድ ካልቻልን ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት አዲስ አበባም ልክ እንደ ሕንድዋ ዋና ከተማ ኒውዴልሂ መንገዶችዋ በቆሻሻ ተሞልተው ሕዝቡ መተላለፊያ ያጣል፡፡ ከዚህ በላይ አሳሳቢና አስከፊ ነገር የለም፡፡ ችግሩን ለማስወገድ አሁንም መፍትሄው ያለው በእጃችን ነው፡፡ እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ እናንተስ የሚለው ነው፡፡ ሁሉም አካባቢውን ሲያጸዳ ከተማዋ ትጸዳለች፡፡

የአለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ቀዳሚ ተምሳሌት የሆነች ምድር፤ በአለም የሰው ዘር የመጀመሪያው መገኛ የሆነች፤ በፓን አፍሪካ ንቅናቄ ቀዳሚ ስፍራ ያላት ሀገር፤ ለአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች የክፉ ቀን መጠጊያና ተስፋ የነበረች ምድር፤ የአፍሪካ አንድነት በኋላም የአፍሪካ ሕብረት መስራችና ዋና ጽህፈት ቤት ዛሬ ደግሞ ከኒውዮርክና ቤልጂየም ቀጥላ ሶስተኛዋ የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከተማ ለመሆን የበቃችው የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ በጣም የጸዳችና የአማረች ከተማ እንድትሆን ነዋሪዎችዋ ከተማዋን በማጽዳት ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዲስ አበባ አህጉራዊና አለም አቀፍ መዲናም ነች፡፡ የጽዳትዋ ደረጃና ለጤንነት ተስማሚነትዋ ይሄን ሁሉ ታላቅ ክብርና ስም በሚመጥን ደረጃ እይደለም የሚገኘው፡፡ ከፍተኛ የቆሻሻ ማከማቺያ ሆናለች፡፡ በዚህም የሀገሪቱ ክብርና ስም ተዋርዶአል፡፡ የዚህን ጉዳይ ሸክም በመንግሰት ላይ መጣሉና ማማረሩ ብቻውን ትርጉም የለውም፡፡ ለራሱ ለልጆቹ ለሕብረተሰቡ ጤንነት ሲል አሳሳቢነቱን ሊያጤነው የሚገባው ራሱ ሕብረተሰቡ ነው፡፡

የመኖሪያ ቤት ሽንትቤትን ቦይ ቀዶ በቱቦ አድርጎ ወደ ወንዝ የሚለቅ ወንጀለኛን ከራሱ በስተቀር ስለሕዝብ ስለሀገር የማያስብ ሰው የተሸከመች  ከተማም ጭምር ነች አዲስ አበባ፡፡ ያ ሽንት ቤት ከግቢው ተለቆ ወደ ወንዝ ሲገባ የወንዙ ውሀ በመጀመሪያ ደረጃ ይበከላል፡፡ በወንዙ ውስጥ ያሉ እጽዋት ነፍሳት የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል፡፡ ወንዙ ወራጅና ሂያጅ በመሆኑ አቋርጦ በሚጓዝበት ቦታ ሁሉ በሽታን እያካፈለ በሽታንም ተሸክሞ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡

ወንዙን በሄደበት ቦታ የሚጋራው ሕብረተሰብ ውሀ ለማግኘት የማይችለው በተበከለው የወንዝ ውሀ ልብሱን ገላውን ልጆቹን ያጥባል፡፡ እንሰሳት በተለምዶ ወንዝ ወርደው የተበከለውን መርዛማ በሽታ ተሸካሚ ውሀ ይጠጣሉ፡፡ ምናልባትም በድሮው እምነት የሚኖሩ ወንዙን በሩቅ ቦታ በአቅራቢያቸው ሲያልፍ የሚያገኙትም ቀድተው  ወደቤት ወስደው ለመጠጥ ውሀ ለእቃ ማጠቢያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

ወደ ወንዙ የሚጣሉት ፕላስቲኮች ፌስታልና ሀይላንዶች ደግሞ ወንዙን እስከ ወዲያኛው ይበክሉታል፡፡ የሰው ልጅ በስርአቱና በአግባቡ ሊከላከለው ሊያስወግደው ቦታም ሊያበጅለት የራሱን የቤተሰቡን የልጆቹን ጤንነት ለመጠበቅ እየቻለ በግዴለሽነትና በዝርክርክነት በሚፈጥረው ችግር አካባቢውን አልፎም በሩቅ ያሉ ቦታዎችን በመርዝ ይበክላል፤ ያቆሽሻል፡፡

ከከተማ ፋብሪካዎች የሚወጡት ፍሳሾችም የዛኑ ያህል ለሰው ልጅና ለእንሰሳት  ጤንነት አደገኛ የሆኑ የኬሚካል መርዞችን ተሸክመው ወደ ወንዞች ይቀላቀላሉ፡፡ በመሰረቱ ሕዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ፋብሪካዎች አይገነቡም፡፡ ከፋብሪካው ስራቸውን ጨርሰው የሚወገዱት ኬሚካሎች በቱቦ ተደርገው የሚለቀቁት ወደወንዞች መሆኑ የተጋረጠብንን አደጋ አሳሳቢና የከፋ ያደርገዋል፡፡ ስልጣኔና እድገት ማለት በቆሻሻ ክምር መከበብ ማለት አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ለአካባቢው የአየር ንብረት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለሕብረተሰቡም ጤንነትና ሕይወት አደጋ የማያስከትሉ ሁኔታዎችን ጠብቆ ተከላክሎ መስራት ማለት ነው፡፡ ፈረንጆቹ “ኢንቫይሮመንት ፍሬንድሊ” ይሉታል፡፡

ችግሩ ግዙፍና የትየለሌ ነውና ወደ መፍትሄው ማተኮሩ ይጠቅማል፡፡ በከተማው አስተዳደር በሕዝብ ተሳትፎ የታገዘ አዲስ የቆሻሻ ማስወገጃ  ዘዴ መፈለግ፤ መቀየስም አለበት፡፡ በተለይ የሽንት ቤት ቆሻሻዎችን በቱቦ እያገናኙ ወደወንዝ የሚለቁትን በዚህም ሕብረተሰቡን ለተስቦና ለተላላፊ በሽታዎች የሚያጋልጡትን በተመለከተ በሕዝብ ጤንነትና በወንዞቻችን ላይ የሚፈጸም ከባድ የግድያ ወንጀል ስለሆነ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ መክበድ አለበት፤ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ኃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎች ስለሆኑ ማለት ነው፡፡

በመላው ሀገሪቱ ሕብረተሰቡን አስተባብሮ በከተሞች ውስጥ በየመንደሩ በየሰፈሩ ቀበሌዎችን በቀጠና ከፍፍሎ የቆሻሻ ማከማቻ በርሜሎችን በሕዝብ መዋጮም ቢሆን በስፋት ማሰራት ማንም ሰው በሕግ ከተፈቀደለት ቦታ ውጪ ቆሻሻ ጥሎ ቢገኝ ተጠያቂ እንደሚሆን የማስተማርና ማሳወቅ ስራ ዛሬ ቢጀመር ቀጣዩ ትውልድ አብሮት፤ ባሕሉ አድርጎም ይወስደዋል፡፡

ባጠቃላይ፣ የሰፈሩን የአካባቢውን ብሎም በብሔራዊ ደረጃ ንጹሕና ለጤንንት ለኑሮ የተመቹ ከተሞችና አካባቢዎች እንዲኖሩን ያደርጋል፡፡ ጽዳትን መጠበቅ የዘመናዊነትና የስልጣኔ ምልክት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ጽዳትን መጠበቅ ጥቅሙ ለማንም ሳይሆን በዋነኛነት ለነዋሪዎች ሕዝብ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy