Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚናውን ይረከባል

0 386

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚናውን ይረከባል

ወንድይራድ ኃብተየስ

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግብርናውና ኢንዱስትሪው ተመጋጋቢ ሚና እንዲኖራቸው ተደርጎ ተቀርጿል። በዕቅድ ዘመኑ ኢንዱስትሪው ከግብርናው የመሪነት ሚናውን እንዲረከብ በመንግሥት በኩል በርካታ ጥረቶች እየተከናወኑ ነው። አንዱስትሪው ይህን ሚናውን እንዲወጣ የልማት ዕቅዱ ከወዲሁ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።

በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚያስብል ደረጃ እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተስፋ ሰጪ ነው። በመላ አገሪቱ የሚገነቡት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተስፋፉ መምጣታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ይህም አገሪቱ ለኢንቨስትመንት መስፋፋትና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥና ለዘላቂ ዕድገት መሠረት የሚጥል ነው።

መንግሥት ፓርኮቹን የሚገነባው የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ነው። ፓርኮቹ አስፈላጊው የመሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው የሚገነቡ በመሆናቸው ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።

በመልማት ላይ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ሂደት ተከትለው የሚገነቡ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት ነፃ ናቸው። በምርት ወቅት ተረፈ ምርታቸውን እንደገና መጠቀም በሚያስችል ሁኔታ የተገነቡ በመሆናቸው ደግሞ የሃብት ብክነትን ማስወገድ ይችላሉ። ይህም ፓርኮቹ በምርትም ይሁን በተረፈ ምርት ውጤታማ መሆን የሚያስችሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይም የማምረቻ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚና ትልቅ ድርሻ አለው። በአሁኑ ወቅት የዘርፉ ምርቶች ጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ከ1ዐ በመቶ አይበልጥም። በዕቅዱ መሠረት በ2012 ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ይህንን ድርሻም ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግና በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ ተቀምጧል።

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡ አመላካች የሚሆነው በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የሰው ኃይል ሽግሽግ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛና በከፍተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የተሰማራውና ከ350 ሺህ የማይበልጠውን የሰው ኃይል በቀጣዩቹ አሥር ዓመታት በአራት እጥፍ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቧል። በዚህም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እድል ይፈጠራል። የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ልማታዊ ፋይዳዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ መንግሥት በብርቱ እየተረባረበ ይገኛል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም አገር በምጣኔ ሀብት፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የሥራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በአገሪቱ የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ሥራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል። ልማቱ ለመሠረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የላቀ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ አገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ሥራዎችን በሂደት በአገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በአገር በቀል ተቋማት አማካይነት እንዲከናወኑ መሠረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል።

በመላ አገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይላቸዋል። በዘመናዊ አሠራር ውስጥ የሚታወቀውን የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ አሠራርንም ይከተላል። በማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እየተገነቡ ያሉት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ መሠረትም መንግሥት በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በራሱ ወጪ እየገነባቸው የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን የነደፈውን ዕቅድ ለማሳካት ጥረት እያደረገ ነው።

በዚህም የልማት ዕቅዱን ግብ ለማሳካት በግል ባለሃብቱ ከሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች ባሻገር በመንግሥት ሙሉ ወጪ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በመላ አገሪቱ በመገንባት ላይ  ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል በዋነኛነት የሐዋሣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዋነኛ ማሣያ ይሆናል። በሐዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ 18 ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች በፓርኩ ከትመው ሥራ ጀምረዋል። ምርትም ወደውጭ መላክ ጀምረዋል። ከዚህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች።

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በልማቱ የተነሱ 186 አባዎራዎች ከክልሉ መንግሥትና ሐዋሣ ከተማ መስተዳድር ጋር በመሆን ምትክ የመስጠት ሥራ ተከናውኗል። በልማቱ ለተነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተማ አስተዳደሩ ወደ 200 የሚጠጉ ቤቶችን ገንብቶ አስረክቧል።  በሐዋሣ ከተማ የሚገኙ ሰፊ ቦታ ያላቸውና ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦችም መንግ
መንግሥት ባቀረበው የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ ሆነው ቤት የመገንባት ሥራውን ጀምረዋል።

እነዚህ ተግባራት የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር ለልማት የሚነሱ ዜጎች ተመጣጣኝና ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ተገቢው ምትክና ካሣ በመንግሥት በኩል ተፈፃሚ እየሆነላቸው መሆኑን ነው። ይህ ሁኔታም ዜጎች ለልማት ተነሺ ቢሆኑም፣ ከሚካሄደው ልማት በየደረጃው ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ነው። የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከግብርናው የመሪነት ሚናውን እንዲረከብ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። ይህም ወደፊት የኢንዱስትሪው የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ መደላድል እየፈጠረ ነው። መንግሥት በዚህ ረገድ በተለይም በመቀሌና በኮምቦልቻ የተሰናዳው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ጥሩ ማሣያዎች ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ።

አሁን ባለው ቁመና ኢንዱስትሪውና ግብርናው ተመጋጋቢ እየሆኑ መጥተዋል። ይህም በአንድ በኩል ግብርናው ምርቶቹን በተገቢው ሁኔታ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚሆኑበት ደረጃ ውጠታማ ይሆናል። በሌላ በኩልም ኢንዱስትሪው ከግብርናው በሚያገኘው ግብዓት እየታገዘ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል። ይህም ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን የሚያደርጋት ይሆናል። በመሆኑም አሁን ባለው ዕቅድ መሠረት እየተፈጠረ ያለው የኢንዱስትሪ እመርታ በቀጣይ ከግብርናው የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ አሁንም የበለጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy