ለደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ዳግም ተፈጻሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲተባበሩ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ ጥሪ አቀረበ።
በደቡብ ሱዳን ሰላም ድርድር ላይ ለመምከር ደርጅቱ በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ የአባል አገራቱ መሪዎች ጉባኤ ያካሂዳል።
በዛሬው ዕለትም ከሌሎች አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ አጋር አካላት በተገኙበት ቅድመ ጉባኤ ስብሰባ በአፍሪካ ሕብረት አካሂዷል።
በጎርጎሬሳዊያኑ 2011 ሉዓላዊ አገርነቷን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን ለአራት አመት ያክል በአላባራ የእርስ በርስ ጦርነት ወሰጥ ትገኛለች።
የእርስ በርስ ጦርነቱን ለማርገብ በኢጋድ መሪነት በ2015 የሰላም ስምምነት ተደርሶ ነበር።
ይሁንና በተቃናቃኞች ችግር የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ባለመደረጉ ባለፈው ሰኔ ወር የሰላም ስምምነቱን ዳግም ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ በኢጋድ በመተላለፉ ተቀናቃኞችን ዳግም ለማደራደር ለወራት ሲሰራ ቆይቷል።
የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳሉት በ2015 የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ዳግም ገቢራዊነትም የኢጋድ አባል አገራት ሚኒስትሮች ምክር ቤት አሳታፊና ተከታታይነት ያለው ምክክር መድረክ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
ከነገ ጀምሮ ለአራት ቀናት ለሚደረገው የመሪዎች ጉባኤም የምክክሩ ውጤት ለደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖችና አጋር ድርጅቶች መሰራጨቱን ጠቁመዋል።
የዳግም ሰላም ስምምነቱ ደቡብ ሱዳን በወቅቱ ባጋጠማት ቀውስና እርስ በርስ ጦርነት ወጥታ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንባት የታመነበት ነው ብለዋል።
ይህ የሚሆነው ግን ሁሉም ተቀናቃኝ ወገኖች ለሰላም ድርድሩ ተፈጻሚነት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሲኖራቸው ነው ብለዋል።
ሰለሆነም ለስደት፣ርሀብና እርዛት የተጋለጡ ሰላም ፈላጊ ደቡብ ሱዳናዊያንን ምላሽ ለመስጠት ለሰላም ድርድሩ ተፈጻሚነት ሁሉም ወገኖች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ለደቡብ ሱዳናዊያን ሰላምና ማህበራዊ ደህንነት ኢትዮጵያና ኢጋድም ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ለሰላም ድርድሩ ዕውንነት ከሁሉም ወገኖች አወንታዊ ምላሽ እንዳለ የጠቆሙት በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ መልክተኛ አምባሳደር እስሜኤል ዌይስ፤ ተቀናቃኝ ወገኖች ከሁሉም በላይ አገራዊ ጥቅም ሊያስቀድሙ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በደቡብ ሱዳን የተፈለገውን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሁሉም ወገኖች ለዳግም የሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነትም ትብብርና ቀናኢ መፍትሄ አካል ሊሆኑ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የሰላም ስምምነቱን የሚከታተለው የክትትልና ግምገማ ጥምር ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የቀድሞ የቦትስዋና መሪ ፌስተስ ሞጌ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ተኩስ ማስቆም፣ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረግና የሰላም ስምምነቱን ማስፈጸም ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ቁልፍ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊተባበር አንደሚገባና ተቀናቃኞችም ወደ ጠረምቤዛ መጥተው እርስ በርሳቸው ልዩነታቸውን በማቻቻል ድርድሩን መተግበር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በዛሬው ቅድመ ጉባኤ የአውሮፓ ሕብረት፣የአፍሪካ ህብረት፣ተመድ አና ሌሎች ድርጅቶች ከኢጋድ ጎን በመቆም ለተጀመረው ሰላም ድርድር ስኬት ከጎን እንደሚቆሙ አቋማቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ፣ ስዊድንና እንግሊዝን ያቀፈው ትሮካም በሰጠው መግለጫ በአሁኑ ስብሰባ ተቀናቀኞቹ ከመስማማት ውጪ ሌላ አማራጭ ማስቀመጥ አንደሌለባቸው የሦስትዮሽ ጥምረቱ አሳስቧል።
ቻይናም በተመሳሳይ ድርድሩ ስኬታማ እንዲሆን ጠይቃ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከኢጋድ ጋር አንደምትሰራ አስታውቃለች።