Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከብሄር ተኮር ጥላቻ እንውጣ

0 342

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከብሄር ተኮር ጥላቻ እንውጣ

                                                                             ይልቃል ፍርዱ

በሀገራችን ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተከሰተ ያለው ሁከትና ብሄር ላየ ያተኮረ ግጭት፤ ይህንንም ተከትሎ የሚስተዋለው አመጽ፣ ንብረት ማውደምና የሰው ሕይወት መጥፋትን የመሳሰሉ ቀውሶች መፈጠራቸው መንግስትንም ሕዝብንም ከልብ ያሳዘነ ድርጊት ሆኖአል፡፡

ለዚህ ከመነሻው ጀምሮ የዚህ አይነቱ ግጭት እንዲነሳ ሆን ብለው በመስራት እልቂትና ደም መፋሰስ እንዲከሰት ሲጥሩ የነበሩ አንዳንድ አካላት የተጫወቱት ሚና ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ለጉዳዩ መባባስና መልኩን ቀይሮ መከሰት የተጫወቱት የዘረኝነት ሚና፤ የረጩት የከፋ የጥላቻ መርዝ ሰውን በሰውነቱ፤ በዜግነቱ ከማየትና ከመመልከት፤ ለሰውኛ መብቱ ከመቆምና ከመከራከር ይልቅ የግለሰቦችን የግል አለመግባባትና ግጭቶች ሁሉ ወደ ጎሳና ብሄር እየለወጡ የተሳሳተ ትርጉም በማስያዝ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዲወጡ ለማድረግ ይህ ቀረው የማይባል ጥረት አድርገዋል፡፡

ከአብሮነትና ከተለመደው ተከባብሮ የመኖር ኢትዮጵያዊነት ውጪ ሙሉ በሙሉ ባፈነገጠ መልኩ ለአንድ ዘር ወይንም ጎሳ ከእኛ በላይ ተቆርቋሪ የለም በሚል፤ የሌላውን ብሔር ብሔረሰብ በማጥላላትና በማንቋሸሽ ስሜታዊ ሁኖ እንዲነና ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ የበቀልና የኃይል እርምጃ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ረገድ በየሶሻል ሚዲያው የተጫወቱት ሚና ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነው፡፡

እኛ የተለየን ነን ብለው ከሰው በላይ ራሳቸውን የተለዩ አድርገው የማየት ልክፍት የተጠናወታቸው ሕሙማን ናቸው ዛሬ ላይ በሰፊው ለተከሰተው ችግር ዋነኞቹ ተዋናዮች፡፡ እነዚህ ወገኖች ከኃይማኖታዊ እሳቤም ውጭ የሆኑ፤ እግዚአብሄር የሰውን ልጅ በአምሳሉ ፈጠረ ከሚለውም ውጭ የቆሙ፤ ምናልባት እግዚአብሄር እኛን ብቻ ፈጠረ እንጂ ሌላውን የሰው ልጅ አልፈጠረም ለማለት የሚዳዳቸው ደናቆሮዎች ናቸው፡፡ ከሰውም ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም  ጋር ሳይቀር የተጣሉ ናቸው፡፡

ተው አደጋው ለሁሉም ይተርፋል፤ የሚበጀው በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር ነው ተብለው ከድርጊታው እንዲቆጠቡ ቢነገራቸውም የሚሰሙ አልሆኑም፡፡ እንዲያውም ይህንኑ ነውረኛና ዘረኛ ስራቸውን እንደ ጀግንንት ቆጥረው በይፋ ድፍን ሕዝብ እስከ መዝለፍ መሳደብ የእኛ ዘር የተለየ ነው እስከማለት የደረሱበ፤ ከጣሪያ በላይ የገዘፈ ጩሀት የሚያሰሙበት በአምሳያዎቻቸው አይዞአችሁ የሚባሉበት ሁኔታ መከሰቱን ሁሉ ተመልከተናል፡፡ ቢያስቡ ኖሮ ሕዝብ ይከበራል እንጂ አይሰደብም፤ አይንቋሸሽም ነበር።

ሰው የሆነ ሰው የተፈጠረበት ጎሳም ሆነ ብሄር ሲነካ፣ ሲሰደብ፣ ሲዘለፍ፣ ሲዋረድ፣ ለችግር ሲዳረግ፣ በፍጹም አሜን ብሎ ሊቀበል ሊንበረከክ አይችልም፡፡ እነዚህ በዘርና በጎሳ ፖለቲካ የተጠመዱ የግጭት ሱሰሾች ይሄንን ቀላሉን እውነት እንኳን ሊረዱና ሊገነዘቡ አይፈቅዱም፡፡ ይህ ከመሰረቱ የተናጋና የተበላሸ የዘረኝነት ልክፍት ደረጃውን አሳድጎ ዛሬ ሀገሪቱንና ሰላሟን እስከማናጋት ደርሶአል፡፡

አንድ ሰው ሲበደል ግፍ ሲፈጸምበት ሰው በመሆኑ ብቻ ልንቆምለት ለመብቱም ልንከራከርለት ይገባል፡፡ ሁሉም የሰው ዘር በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለው ብሔራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ መርሕ ተገቢና ትክክለኛም ነው፡፡ ከእከሌ ጎሳ ከእከሌ ዘር ስለተፈጠረ ስለተወለደ የምንጠብቀው፤ ከሌላ ዘርና ጎሳ በመወለዱ በመፈጠሩ የምንጠላው የምናጠቃው ከሆነ ለሀገርም ለሕዝብም አብሮነት፤ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አደጋን ያስከትላል፡፡ አሁን የተከሰተው አካሄድም ይሄው ነው፡፡ ፈጥነን ተረባርበን ልንመክተው ካልቻልን በስተቀር፡፡

ዘረኝነትና ጎጠኝነት እጅግ የተሳሳተ፤ ከሰውኛነት ተፈጥሮ በእጅጉ የራቀ ምናልባትም ወደ እንስሳነት በጣም የቀረበ አስተሳሰብና አካሄድ ነው፡፡ እንስሳት ናቸው ሁሉም በዝርያቸው ብቻ የሚቧደኑት፡፡ አምበሳ ከአምበሳ፤ ነብሩ ከነብር፤ ዝንጀሮው ከዝንጀሮ ወዘተ ሌላ እንስሳ ወይም አራዊት ቢቀርባቸው ለጥቃት የመጣ አድርገው ስለሚወስዱት ከመበላላትኝ ከመገዳደል ውጪ ሌላ የሚፈጥሩት ነገር የለም፡፡ ሰው ደግሞ ከእንስሳት በላይ የሚያስተውልበት አእምሮ የተሰጠው ፍጡር ነው፡፡ መገዳደል አንዱ ሌላውን ማሳደድ የሰለጠነ የማመዛዘን ባሕርይ የሌለው የሰው ልጅ ባሕርይ እንዴት መሆን እንደሚችል ለማሰብ ይከብዳል፡፡ የአንድ ሀገር ልጆች ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ባልነበረ ግዜ የወለደው የካንሰር በሽታ ተለክፈው እርስ በእርስ እንደ ጠላት ሲተያዩ፣ ሲናቆሩና ሲጠፋፉ ማየት በእጅጉ ዘግናኝ ብቻ ሳይሆን አሳዛኝም ነው፡፡ ለሕዝብ አብሮነት ለሀገር ሰላምም አይበጅም፡፡

በሕዝብ ስም የሚነግዱ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጩ ወንጀለኞች የመጨረሻው ግባቸው እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭት ተፈጥሮ ሀገር ሰላምዋ ተናግቶ ሕዝቡ እንዲተላለቅ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የኖረ የነግብጽ የነኤርትራ ቀዳሚ አላማና ኢትዮጵያን እንበታትናል ብለው ሲሰሩበት የኖሩት ሴራ ነው፡፡

የግብጽ መንግስት ከሰሞኑ ማናፋት የጀመረው በብዙ ሚሊዮን ዶላር መንዝሮ ገንዘቡ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ካደረገ በኋላ በሕዝቡም ሆነ በተማሪው ውስጥ የማይበርድ የጎሳና የዘር ግጭት በመቀስቀስ፣ ሁኔታውን በማባባስ ሀገሪትዋ ሰላምና መረጋጋትዋ ደፍርሶ የብጥብጥና የሁከት ማእከል እንድትሆን በተደራጀ ሁኔታ የሰራው ስራ ውጤት ነው፡፡ በዚህም የተሰሩትና የሚሰሩት ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲወድሙ፣  የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ኢትዮጵያ ዝንተ አለም በድሕነት እየማቀቀች ጭርሱን ተበታትና እንድትጠፋ አቅዶ ሲሰራበት የቆየ ሲሆን ዛሬ ላይ በሚታዩት የሰላም መደፍረሶች በተከሰቱ ብጥብጦች ተሳክቶልኛል ብሎ አስቦአል፤ ቢያንስ በነሱ አስተሳሰብ፡፡

ተግባሩ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የታቀደ ታላቅ ሴራ ነው፡፡ በእኛ ውስጥ ስለታዩት ችግሮች አስቀደምን እንጂ የግብጽ ሴራ መቼም አባርቶ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያላሴረችበት አንድም ጊዜ ግዜ የለም፡፡ ይሁን እንጂ አንድም ጊዜ ሲሳካላት ታይቶ አይታወቅም። የሰሞኑ ወታደራዊ ዛቻም ከድንፋታ አይዘልም፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆነና የአለቃ ገብረሀና ማዘንጊያ “እዛም ቤት እሳት አለ” አባባል ለግብጽ ወቅታዊ ሁኔታ የሚመጥን ነው፡፡ “መስታወት ቤት ያለ ሰው ድንጋይ ለመወርወር የመጀመሪያው አይሆንም” የሚለውም ለግብጽ ይሰራል፡፡

የእኛን ሕዳሴ ግደብ አጠፋለሁ ስትል በእጅዋ ያለውንና የምትንሰፈሰፍበትን የአስዋን ግድብና የናስር ሰው ሰራሽ ኃይቅ ወድሞ እንዳይፈራርስ ማሰብም አለባት፡፡ ምናልባት ሳኡዲ አረቢያ የመንን እንዳወደመቻት ኢትዮጵያን እንደዛ አደርጋለሁ ብላ አስባ ከሆነም መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ለሁሉም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ላይ ከተከሰቱት ግጭቶችና ሁከቶች ጀርባ የራሳችን የውስጥ ችግር ጎልቶ ቢታይም ይሄንን በማቀጣጠል ረገድ የግብጽና የኤርትራ ስውር እጆች በየማእዘኑ፤ ከጀርባ እንዳሉ በፍጹም መጠራጠር አይቻልም፡፡

ይህንን ምስጢራዊ ሴራ ለረዥም ዘመን ግብጾች ውስጥ ለውስጥ ሲሰሩት ኖረዋል፡፡ ግብጾች በጥንት ዘመን የአባይን ውሀ ከምንጩ ለመቆጣጠር አስበው በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ሠራዊት አዝምተው ተዋርደው፤ በጦር ሜዳ ተገድለውና ተማርከው እግሬ አውጪኝ ብለው ሸሽተው ሄደዋል፡፡

ዛሬም በተጨባጭ በውስጥ ያለውና መፈታት ያለበት ሀገራዊ ችግር በውስጥ የሚፈታ ቢሆንም ይሄንን እንደ ማቀጣጠያ ነዳጅ በመጠቀም የራሳችንን ዜጎች በውስጥ በማሰለፍ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ወኪሎችን በመመልመል የእርስ በእርስ የጎሳ ግጭት እንዲነሳ በተማሪዎች መካከል ግጭትና መጠፋፋት እንዲከሰት የሶሻል ሚዲያ ሠራዊት በማሰማራት ሰፊ ስራ እየሰራች ያለቸው ግብጽ ከኤርትራ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

ይሄንን የኖረና ግዜን ጠብቆ እየተከወነ ያለ ሀገር አጥፊ ሴራ ኢትዮጵያውያን በቅጡ ተረድተን ልንመክተው ካልቻልን ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ሀገራችንን አሳልፈን ሰጥተናል ማለት ነው፡፡ ይህን ቀድሞ አውቆ መከላከል ሀገርንና ሰላምዋን መጠበቅ ጠላቶቻችን በዘረጉት ወጥመድ ተጠልፈን ሀገራችንን ለውደቀት ከመዳረግ መቆጠብ ይገባናል፡፡

የዘርና የጎሳ ፖለቲካ በሽታን ማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ በየትኛውም ማእዘን ሰርቶም ሆነ ተምሮ ንብረት አፍርቶ ወልዶ ከብዶ ተዘዋውሮ የመስራት፤ የመኖር መብቱ እንደቀድሞው ሁሉ በፍቅር በመተሳሰብ በቤተሰባዊነት እንዲቀጥል ማድረግ መቻል አለብን፡፡ እርስ በእርስ በመናቆር፣ ሀገራችንን በማጥፋት ለግብጽና ለሻእቢያ ሴራ ሲሳይ መሆን የለብንም፡፡

አንድ ሰው ጥፋት  አጥፍቶ ቢገኝ መጠየቅ ያለበት በግለሰብነቱ ራሱ በፈጸመው ድርጊት እንጂ በጎሳው ወይምን በዘሩ መሆን የለበትም፡፡ ይህ በየትኛውም አለም ሕግ የጸደቀና የሚሰራበትም ነው፡፡ ሕዝብ ከሕዝብ አይጋጭም፡፡ አይጠላላም፡፡ መነሻ ምክንያት የሚሆኑት ሁልግዜም በተሳሳተ መንገድ የሚራመዱ ግለሰቦች ናቸው፡፡ የግለሰቦች ስሕተትና ጥፋት እንደ ሕዝብ ጥፋት ሊታይ፤ ሊወሰድ የሚችልበት የሕግ መሰረትም የለም፡፡

ሰው ከእንስሳት ተለይቶ የማሰብና የማመዛዘን ባሕርይ ያለው ፍጡር ነው፡፡ መጠፋፋት፣ መበላላት፣ መገዳደል፣ ጎራ ለይቶ መፋጀት በተለይ የአውሬዎች አይነተኛ ባሕርይ ቢሆንም ምክንያታዊነት በሌለበት፣ ማስተዋልና ሚዛናዊነት በጠፋበት በጅምላ በስሜት መነዳት በሚነግስበት ወቅት ሰውም ልክ በሩዋንዳ እንደተፈጠረው የሁቱና የቱሲ ጎሳዎች ትርጉም በሌለው ሁኔታ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንደተላለቀበት የዘር ፍጅት አይነት ከለየላቸው የዱር አውሬዎች በላይ ሲፈጥር አይተናል፡፡

ከዚያ ሁሉ ሰቅጣጭ እልቂት በኋላ እንደገና ሀገሪቱ አንድ ብላ አቧራ አራግፋ ተነሳች፡፡ እንደገና ሕይወት ቀጠለ፡፡ ዛሬ ላይ ለምን ያ ሁሉ ሆኖ በፍቅር መኖር እያቻልን መቻቻል ተስኖን ነበር ብለው ቢጸጸቱም ያለቀውን ሕዝብ፣ የወደመውን ንብረት ሊመልሱት ግን አልቻሉም፡፡ የውጭ ኃይሎችም ያ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ፈጥነው በመድረስ ሊገቱት አልቻሉም፡፡ እንዲውም ዛሬ ላይ የነበራቸውን ሚና የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

ይህ አይነቱ  አስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ በሀገሩ ላይ እንዲከሰት የሚፈልግ ማንም አይኖርም፡፡ በዚህ የከፋ ተግባር የተጠመዱትን ሕዝብን ከሕዝብ ማናቆር፣ ማጋጨትና ማባላት የሚፈልጉትን ከወዲሁ ሳይረፍድ ማስታገስ ተገቢ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የተፈጠረው ሁከትና ተቃውሞ መነሻም ከዚሁ አይነት የብሄር ግጭት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በጎሳው በዘሩ ምክንያት ለጥቃት መዳረግና መሞት የለበትም፡፡ ይሄንን ያደረጉትን መንግስት ተከታትሎ ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማስፈን መቻል ይጠበቅበታል፡፡ በአደባባይ ለፍርድ መቅረብም አለባቸው፡፡ ሌላው ሊማር የሚችለው በዚህ መልክ ብቻ ነው፡፡

ተማሪዎቻችን የነገ የሀገሪቱ ተረካቢዎችና መሪዎች ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በጎሳና በዘር መደራጀቱም መቆም አለበት፤ ሲጠቅም አላየንም፡፡ ፍቅርን ሲገድል እርስ በእርስ ሲያባላ እንጂ ሕብረትን ሲያመጣ፣ አብሮነትን ሲያጎለብት አልተመለከትንም፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ በተጨባጭ ከታዩና ከደረሱ ውድቀቶች በመነሳት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ግድ ይለዋል፡፡

የትምህርት ተቋማት እውቀት የሚቀሰምባቸው አብሮ መኖር መቻቻል መተዋወቅ ማሕበራዊ ሕይወትን በጋራ መካፈል የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች በጋራ አንድ ማእድ የሚቆርሱበት እንጂ እጅግ ኋላቀር በሆነ የጎሳ ፖለቲካ መነሻነት የሚባሉበት መድረክ ከቶውንም ሊሆን አይገባውም፡፡ በ20ኛው ክፍል ዘመን የሰው ልጅ ከምድር አልፎ ሕዋ ላይ ለመኖር እየታገለ ባለበት፣ ምጡቅ ቴክኒዮሎጂ በሰፈነበት ዘመን የዘርና የጎሳ ፖለቲከን ማቀንቀንን ቀዳሚ አጀንዳ ማድረጋችን ምን ያህል ከአለም ወደኋላ የቀረን መሆናችንን ያሳያል፡፡

ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ክቡር ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ከእከሌ ጎሳ ልወለድ ብሎ ማመልከቻ አቅርቦ የተወለደ በአለም ላይ የለም፡፡ ከየትኛው ዘር ጎሳ ይወለድ ሰው ሁሉ በእኩልነት ሰብአዊ መብቱ ሊከበርለት፤ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ይህ የሞተ፣ ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ሀገርንና ትውልድን ይገድላል፡፡ በመሆኑም “ሳይቃጠል በቅጠል” ሊሆን ይገባልና ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy