Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአጋጣሚነት ወደመደበኛነት እየተለወጡ የመጡት ግጭቶች መንስኤ ምን ይሆን?

0 773

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአጋጣሚነት ወደመደበኛነት እየተለወጡ የመጡት ግጭቶች መንስኤ ምን ይሆን?

ኢብሳ ነመራ

የሃይማኖትና የብሄር ብዝሃነት ያላት ኢትዮጵያ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ምሳሌ ሆና ቆይታለች። በኢትዮጵያ ታሪክ ብሄርንም ይሁን ሃይማኖትን መነሻ ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት አጋጥሞ አያውቅም። ብዝሃነትን ጨፍልቆ አንድ ብሄራዊ ማንነትና ሃይማኖት ያለው ኢትዮጵያዊነትን የመመስረት ስትራቴጂ ይከተሉ የነበሩ የአሃዳዊ መንግስት ሥርአቶች በነበሩበት ወቅት እንኳን አንዱ ብሄር በሌላው ላይ አልተቆጣም፣ አልተነሳምም። በርካታ ብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄዎች የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ በነበረበት እስከ 1983 ዓ/ም ድረስ በነበሩ ዓመታት፣ የነጻነት ንቅናቄዎቹ እንወክለዋለን ከሚሉት ውጭ የሆኑ ማህበረሰቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረው አያውቁም። ወይም ጥቃት እንዲሰነዘር ህዝብን በህዝብ ላይ አነሳስተው አያውቁም። ከማንነት ባሻገር ለሰዎች መብትና ነጻነት መከበር ነበር የሚታገሉት። በትጥቅ ትግልም ሆነ በሌላ መንገድ ለመብትና ነጻነት ሲካሄዱ የነበሩ ትግሎች ህብረ ብሄራዊ ባህሪ የነበራቸው፣ የተለያየ ብሄርና ሃይማኖት አባላት በአንድ ግንባር ተሰልፈው የተዋደቁበት ሁኔታም ነበር። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የአመለካከትና የሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊት ፌደራላዊት ኢትዮጵያን መገንባት ያስቻለው መሰረት የተጣለው በእነዚህ ትግሎች የተገኘ ድል ነው።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው በህገመንግስት ተረጋግጦ ብሄራዊ መብታቸውና ነጻነታቸውን ማጣጣም ከጀመሩ በኋላ፤ በመሃከላቸው እኩልነትና መከባበር መኖሩን ተገንዝበው በሃገራቸው በማንነታቸው ተሸማቀው ከመኖር ተላቀው አንገታቸውን ቀና ካደረጉ  በኋላ ግጭቶች መታየት ጀምረዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩበት መልከዓምድራዊ ወሰን ውስጥ በቋንቋቸው እየሰሩ፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያስተማሩ፣ ባህላቸውን እያስተዋወቁና እያጎለበቱ፣ እውነተኛ ታሪካቸውን እያጠኑና እየተንከባከቡ የመኖር መብታቸው ተረጋግጦ የጋራ ጉዳያቸውን ደግሞ ሁሉም በተወከሉበት የፌደራል መንግስት በሚያስተዳድሩበት ሥርአት የእርስ በርስ ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚያደርግ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ የለም። በፌደራላዊ ሥርአቱ የሚነሱ ግጭቶች ከነባራዊ ሁኔታና ከመርኸ አኳያ ሲታዩ ከሚጠበቀው ተቃራኒና መሆን ያልነበረባቸው ናቸው።

መሆን ያልነበራቸው ቢሆኑም የሆኑበትን አጋጣሚ ግን ተመልክተናል። የብሄር መልክ ያለው ግጭት እንዲያውም ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ የመጣበት ሁኔታ ነው የሚታየው። ይህ  ከነባራዊ ሁኔታና ከመርኸ ያፈነገጠው ግጭት ውጪያዊ መንስኤ ወይም ገፊ ኃይል ያለው መሆኑን ያመለከታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ እይታ እንዲኖረን በሃገራችን ባለፉ ሦስት ወራት ገደማ የነበረውን ሁኔታ በቻ መለስ ብለን እንመልከት። አነሳሱ ቀደም ያለ ቢሆንም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ከያዝነው ዓመት መግቢያ ጀምሮ በኦሮሞዎችና በሱማሌ ተወላጆች መሃከል ግጭቶች የሚካሄዱበት ሁኔታ አለ። በሁለቱም ወገን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል። የሞቱና የቆሰሉም አሉ። ግጭቱ አሁንም አላባራም። ሰሞኑን በምስራቅ ሃረርጌ ጨለንቆ እንዲሁም በምእራብ ሃረርጌ ዳሩ ለቡ እና ሃዊ ጉዲና ወረዳዎች ለበርካታ ኦሮሞዎችና ሱማሌዎች ሞት ምክንያት የሆነ አስከፊና አሳዛኝ ግጭት ተቀስቅሷል። ይህ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልና በኦሮሚያ አወሳኝ አካባቢዎች ያጋጠመ ሁከት ራሱን የቻለ ሰፊ አጀንዳ ስለሆነ ዝርዝሩን በሌላ ጽሁፍ የምመለስበት ይሆናል። ይሁን እንጂ ለዘመናት በሰላም አበረው ይኖሩ በነበሩ ብሄሮች መሃከል የተፈጠረ ግጭት መሆኑ ሊያዝ ይገባል።

ከዚህ ከግዙፉ ግጭት በተጨማሪ ባለፉ ሶስት ወራት የብሄር ገጽታ ያላቸው በርካታ ጥቃቅን ግጭቶች እዚህም እዚያም አጋጥመዋል። በኦሮሚያ ቡኖ ቤዴሌ ዞን ሶስት ወረዳዎች በኦሮሞና በአማራ ተወላጆች መሃከል ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ግጭት አጋጥሟል። በዚሁ ሰሞን በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የኢሬቻ በአል ላይ ሁለት ግለሰቦች ላይ ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል። በኦሮሚያ ምእራብ አርሲ ዞን ባቱ (ዝዋይ) ከተማ አካባቢ የሁለት ግለሰቦችን ግጭት መነሻ ያደረገ በኦሮሞዎችና በወላይታ ተወላጆች መሃከል ጎራ የለየ የቡድን ግጭት አጋጥሟል። በዚሁ በምእራብ አርሲ ዞን አርሲ ነጌሌ ከተማ የመጠጥ ግሮሰሪ ውስጥ በግሮሰሪው ባለቤትና ደንበኛ መሃከል  የተፈጠረና ለአንድ ገላጋይ ህይወት ህልፈት ምክንያት የሆነ ግጭት፣ በማግስቱ ጠዋት የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ግጭት የሚመስል ባህሪ ይዞ እንደነበረ ይታወሳል። በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በእንድ የአካባቢው ተወላጅ ሴት ላይ የመኪና አደጋ መድረሱን ተከትሎ ከሌላ አካባቢ የመጡ ኢትዮጵያውያን ላይ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል።

እነዚህ ብቻ አይደሉም። በህዳር ወር ማብቂያ ላይ በአማራ ክለላዊ መንግስት ሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ ከተማ፣ በመቀሌና ወልዲያ ከተማ የእግር ኳስ ቡድኖች መሃከል ሊካሄድ የነበረን ግጥሚያ መነሻ በማድረግ ጫወታው ከመጀመሩ ከሰአታት አስቀድሞ የወልዲያ ከተማ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ ወጣቶች በቀሰቀሱት ትንኩሳ ብሄርን መሰረት ያደረገ ግጭት ተቀስቅሶ ለሁለት ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። ይህን ተከትሎ በትግራይ ክልል አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብሄርን መሰረት ባደረገ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ነጆ ካምፓስ በተቀሰቀሰ ብሄርን መሰረት ያደረገ ግጭት ሁለት ተማሪዎች ተገድለዋል።

እነዚህ ወትሮ በሃገሪቱ ከነበረው ሁኔታ በተለየ በተከታታይ ያጋጠሙ የአብዛኞቹ ግጭቶች መነሻቸ ከብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው ናቸው። አብዛኞቹ ጊዜያዊ የግለሰቦች ጸብን፣ የእግር ኳስ ደጋፊነትን እንዲሁም የአጋጣሚ አደጋን መነሻ ያደረጉ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም የብሄር ገጽታ ይዘዋል ወይም እንዲይዙ ለማድረግ ተሞክሯል። ይህ ሁኔታ ከላይ የጠቀስኳቸውን በተለያየ ስፍራ በተለያየ መነሻ ምክንያት ያጋጠሙ ግጭቶች ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል። የተለያየ መነሻ ኖሯቸው ተመሳሳይ መልክ እንዲይዙ መደረጉ ግጭቶቹን የቃኛቸው አካል አንድ ወይም ተዛማጅነት ያላቸው መሆናቸውን ያመለክታል።

ይህን ሁኔታ ሰፋ አድርገን ስንመለከተው ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውንም ግጭት አመቺ ሆኖ ከተገኘ የቡድን – የብሄር ወይም የሃይማኖት ገጽታ በመስጠት ለማዛመትና ሃገሪቱን ለማተራመስ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ስልት መኖሩን ያመለክታል። ከዚህ ስልት ጀርባ ደግሞ ስልቱን የነደፉና የሚያስፈጽሙ አካላት አሉ።

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያን በእርስ በርስ ግጭት በማተራመስ ዳግም ሃገር መሆን በማትችልበት ሁኔታ የማፈራረስ ስትራቴጂ የሚከተሉ አካላት መሆናቸውን መገመት ብዙም ምርምር የሚጠይቅ አይደለም። ከእነዚህ የሃገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ጋር የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ነን ብለው በአሜሪካና በኤርትራ የመሸጉ ቡድኖችም ተሰልፈዋል። እንዲያውም ዋነኞቹ የስትራቴጂው አስፈጻሚዎች እነዚህ አካላት ናቸው። እነዚህ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ሃገሪቱን የማተራመስ የጠላት ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች የሚጠቀሙባቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ጥቃቅን ግጭቶችን ተቀጣጣይ ወደሆኑ የብሄር ግጭትነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ዘሐበሻ፣ መረጃ ዶት ኮም፣ ዲጄ ኢትዮጵያ . . . የመሳሰሉ የኤርትራ መንግስት የሚመራቸውና እነግንቦት 7 የሚጠቀሙባቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥላቻ በመቀስቀስ፣ ግጭቶች የብሄር መልክ እንዲይዙና እንዲስፋፉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርኛ መወጣታቸውን ልብ ይሏል።

ለዚህ አስረጂነት አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ተማሪ ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ግጭት መቀስቀዩን ተከትሎ፣ ዘሃበሻ የተባለው የፌስ ቡክ ገጽ በግጭቱ ሰባት የአማራ፣ ሰባት የኦሮሞ፣ አንድ የደቡብ ብሄሮች ተወላጆች የሞቱ አስመስሎ በድምሩ የ15 ሰዎችን ስም ዝርዝር አስፍሮ ነበር። እውነታው ግንን ፍጹም ከዚህ የተለየ ነበር። በግጭቱ የሞተው አንድ ተማሪ ብቻ ነው። የአንድ ተማሪ መሞት ዋጋ አይሰጠውም እያልኩ እንዳልሆነ ግን ልብ በሉ። የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን በእርስ በርስ ግጭት የማጥፋት ስትራቴጂ አስፈጻሚ የሆኑ ቡድኖች የሚጠቀሙበት ዘሐበሻ የተሰኘው ድረ ገጽና የፌስ ቡክ ገጽ ይህን አይን ያወጣ ወሸት ያሰፈረው የተሳሳተ መረጃ ደርሶት አይደለም። አስቦና አልሞ፣ የሚያስከትለውን ውጤት አውቆና ፈልጎ ነው ሃሰተኛውን መረጃ ያሰራጨው። ዓላማውም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ለማነሳሳት፣ ከተቻለም ይህን ግጭት ወደተቀረው ህብረተሰብ በማዛመት ሃገሪቱን ለማተራመስ ነው። ዘሐበሻና ቢጤዎቹ ከላይ ከጠቀስኳቸው የግለሰብ ጸብን ወይም ሌላ ምክንያትን መነሻ በማድረግ የተቀሰቀሱ ግጭቶችን አስመልክቶ ያሰራጫቸውን መረጃዎች በሙሉ ብትመለከቱ ይህን እውነታ በግልጽ መረዳት ትችላላችሁ።

እርግጥ ነው የክልል መንግስታትም ሆኖ የፌደራል መንግስት ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ በቂ የፖለቲካ ስራ ያልሰሩበት ሁኔታ አለ። ግጭቶች ካጋጠሙ በኋላም እንዳይባባሱና በሌላ ስፍራ ተመሳሳይ ግጭት እንዳይፈጠር ለማድረግ በቂ የፖለቲካ ስራ ያልተከናወነበት ሁኔታም ተስተውሏል። ፈጣን የህግ እርምጃዎች አለመወሰዳቸው፣ የግጭቶችን ተጽእኖ ለመቀነስና በአጠቃላይ በግጭቶቹ ዙሪያ የሚሰሩ የኮሚዩኒሽን ስራዎች የሚወሰዱ ግጭት ቀስቃሽ ሁኔታዎችን ያመቻቹበትን ሁኔታም ታዝበናል።

ያም ሆነ ይህ፤ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ  የተለመዱ እየሆነ መምጣት፣ ማንኛውም አይነት መነሻ ያለው ግጭት የብሄር መልክ የሚይይዝበት ሁኔታ መደጋገም ድንገተኛ ክስተት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሆን ተብሎ ሃገሪቱን ለማተራመስ በወጠኑ አካላት የሚሰራና የሚመራ ነው። በመሰረቱ ፌደራላዊ ሥርአቱ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እኩልነትና መከባባበርን በማስፈን የእርስ በርስ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የግጭት ምክንያቶች ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን የሚያስወግድ ነው። ፌደራላዊ ሥርአቱ በፍጹም የግጭት ምክንያት ሊሆን አይችልም። ፌደራላዊ ሥርአቱ በክልሎች ወይም በብሄሮች መሃከል አለመግባበቶች ቢያጋጥሙ እንኳን ወደግጭት ወይም የሃይል መፍትሄ ሳይገባ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ህገመንንግስታዊ የመፍትሄ ድንጋጌዎች አሉት።

እርግጥ ነው፣ ከዚህ ህገመንግስታዊ ሥርአት አፈጻጸም መጓተት ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ማድረግ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ መፈጠሩ አይካድም። ይሁን እንጂ ግጭቱን የሚመሩት ቡድኖች የግጭቱን መንስኤ ፌደራላዊ ስርአቱ አስመስለው በማቅረብ ለሌላ ሰፊ ግጭት እየተዘጋጁም መሆኑንም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊገነዘብ ይገባል። በአጠቃላይ በሃገሪቱ እያጋጠሙ የሚገኙት የብሄር መልክ ያላቸው ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ ረገድ የመንግስት የህገመንግስት አፈጻጻምና ያለመግባባቶች የተያዙበት መንገድ ክፍተት መፍጠራቸው ባይካድም በዋናነት የሚመሩትና እንዲዛመቱ የሚደረጉት ግን በኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው መሆኑን ማስታወስ ቢያንስ ሊሆን እንደሚችል መገመት ብልህነት ነው።   

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy