Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከዩኒቨርሲቲዎች ምክንያታዊነትን ወይስ ሁከትን?  

0 407

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከዩኒቨርሲቲዎች ምክንያታዊነትን ወይስ ሁከትን?  

 

ዮናስ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ ለጋ ወጣቶች ከአራቱም ማዕዘናት የሚገናኙባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከማንም እና ከምንም በላይ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ. ተቻችለውባቸው የመማር ማስተማር መርሐ-ግብር የሚከናወ ንባቸው ስፍራዎች ናቸው። ያም ሆኖ ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተወሰኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የፀጥታ መጓደልና ትምህርት መቋረጥ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። ከተማሪዎቹ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እና ለተመራቂ ተማሪዎች ይሰጣል በተባለው የመውጫ ፈተና ላይ አለመግባባት መኖሩ የችግሩ መነሻ እንደሆነ ቢነገርም ይህንኑ ሊያንጸባርቁ የማይችሉ አጀንዳዎች ተነስተው በተማሪዎች መካከል አለመግባባቱን አክረውት የነበረ መሆኑም ይታወቃል።

ከላይ በተመለከተው አግባብ ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት መገብያ፣ የመወያያ፣ የመከራከሪያና የተለያዩ ድምፆች ማስተጋቢያ መሆን አለባቸው። ልዩነቶች የሚከበሩባቸውና በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶችም የሚንፀባረቁባቸው ሊሆኑም ይገባል። እነዚህ ተቋማት የሥልጣኔ ጮራ መሆን ሲገባቸው የግጭት መናኸሪያ ሲሆኑ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነትም አደጋ ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱን ያፀናው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ 23 ዓመታት ተቆጥረዋል፤ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ፌዴራላዊት አገር ለመገንባትም አስችሏል። ከብሔር ብሔረሰቦች ብዝኃነት ጀምሮ ልዩነት ውበት እንደሆነ መግባባት ላይ ከተደረሰ አመታት ተቆጥረዋል። በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ያለውንም ልዩነት መቀበል ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቀላሉ ስራ መሆን ሲገባው፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በስፋት የሚያራግቡ ወጣቶች እየበረከቱ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በብሔርተኞች እየተነዳ ጥፋት የሚፈጽም ወጣት በስፋት እየተስተዋለ ነው። ከኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጫ የጋራ እሴቶች መካከል አንዱና ዋናው በመፈቃቀድና በመተሳሰብ አብሮ መኖር፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በጋብቻ በመተሳሰር ትልቅ አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸም ሆኖ ሳለ፣ ከዚህ በተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች በዩኒቨርሲቲዎቻችን እየተስተዋሉ ነው። በእርግጥ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የትምህርት አካባቢ ሁኔታ ለመፍጠር ተማሪዎች ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ተቋማቱ በፍጥነት ምላሽ መስጠት አለባቸው። በተቋማቱ የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ተማሪዎች ጥያቄዎቻቸውን ሰላማዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ለሚነሱ ጥያቄዎችም ተቋማቱም ሆኑ ሌሎች የመንግስት አካላት ፈጣን ምላሽ መስጠት አለባቸው። ዘላቂ የሆነ መፍትሄ የሚገኘው በዚህ አግባብ ብቻ ነው።

በኦሮሚያና ሱማሌ አዋሳኝ ክልሎች ‘በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ [ወገኖች] በዘላቂነት መቋቋም አለባቸው’ የሚሉት በተማሪዎቹ የተነሱ ጥያቄዎች መሆናቸውንም ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል። ስለሆነም ይህን መፍታት የሚገባው አካል በፍጥነት መልስ መስጠት መቻል አለበት። ይሁን እንጂ እንደዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ መቅረብ የነበረባቸው መሆኑ አያከራክርም። ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ ቢቀርቡ ኖሮ በመንግስትና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳትም ሆነ የሰው ህይወት መጥፋትም አይከሰትም ነበር።

አሁን ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራር አባላት ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራን እና አስተዳደሮች ጋር ባደረጉት ውይይት በመታገዝ ወደ መማር ማስተማሩ ሂደት እየተመለሱ ስለመሆናቸው ከትምህርት ሚኒስትር የወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው። የትምህርት ተቋማቱ የልማትና የሰላም ፍሬዎች ሆነው እንዲቀጥሉ፣ ተቋማቱ ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብና የተቋማቱ አስተዳደር ተማሪዎቹን ከአደጋ ለመጠበቅ ተከታታይ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በተደጋጋሚ ሲነገር እንደሚሰማው ሰላምን የማስጠበቅ ስራ የሁሉም ኃላፊነት ነው። ተማሪዎቹም ሰላምን ከሚያሳጡና አደጋን ከሚያባብሱ ጉዳዮች ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። ወጣቶች ትምህርታቸውን ለመከታተል ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የነገ አገር ተረካቢዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙ ለጋ ወጣቶች በብሔር ጎራ ለይተው እርስ በርስ ሲጠቃቁ ማየት ያስነውራል። ይህ ትውልድ ወዴት እየሄደ ነው? ከማለት በመውጣት ይህንን አደገኛና አሳፋሪ ተግባር ማስቆም የመንግሥትም ሆነ የዜጎች ኃላፊነት ነው። ወላጆች ልጆቻችንን ምን እያስተማርን ነው በማለት ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል። መንግሥት  ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ብሔራዊ የመወያያ መድረኮችን በስፋት ከመፍጠር ባሻገር የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት። ከወላጆቻቸው ጉያ ወጥተው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ለጋ ወጣቶች የግጭቶች ሰለባ እንዳይሆኑ እራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል። በአሁኑ ጊዜ አንዱ ዋነኛ ችግር ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያው መረጃ ከመለዋወጥ ባለፈ በርካታ ምሥጉን ተግባራት የሚከናወኑበት መሆን ሲገባው፣ በአሁኗ ኢትዮጵያ ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነት ማራመጃ እየሆነ ለጋ ወጣቶች እየተመረዙ ነው። ኃላፊነት የማይሰማቸው ጽንፈኛ ብሔርተኞች እያንዳንዷን ነጠብጣብ እየተከታተሉ የወጣቶችን አዕምሮ ሰቅዘው በመያዝ፣ የአንዱ ብሔር ወጣት በሌላው ላይ እንዲነሳ እየቀሰቀሱበት ነው። ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ግጥሞችን፣ መነባንቦችን፣ ሐሰተኛ ወሬዎችን፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የውሸት ምሥሎችን በመፈብረክ ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁባቸው ጨዋነትና አስተዋይነት ያፈነገጡ የእርኩሰት ድርጊቶችን እየፈጸሙበትም ነው። እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች  በወንጀል እንደሚያስጠይቁ ተማሪዎች ሊገነዘቡ ይገባል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከግጭት ጠብ የሚል አንዳች ነገር እንደሌለም ሊረዱ ይገባል።

ከዚያ ውጭ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ከተማሪ አደረጃጀቶች ጋር መስራት ያስፈልጋል። ዩኒቨርሲቲዎች ከተማሪዎች ህብረት እና የሰላም ፎረም ጋር በመተባበር ተማሪዎች የሚያነሷቸውን አስተዳደራዊና ለደባል አጀንዳ ተጋላጭ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ጥያቄዎችን በመለየት ደረጃ በደረጃ መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በየጊዜው በሚካሄዱ መድረኮች መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሰላም ዙሪያ በባለቤትነት እንዲሰራ ለማስቻልም ጥረት  ማድረግ ያስፈልጋል። ተማሪዎች ደግሞ ከየትኛውም መሰረታዊ ፍላጎቶች በላይ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል። የሀገሪቱን ሰላም አስጠብቆ ለማስቀጠል መንግስት የግጭትና ሁከት መንስኤዎችን ከምንጫቸው ማስወገድ  የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር ሆና በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ አንድነትና የቀደመ እሴቶቿን ይዛ እንድተቅጥል ተማሪዎችም የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል። በእርግጥ አሁን ሁሉም በሚባል ደረጃ ባደረጉት ውይይት ወደመማር ማስተማሩ ስራ ገብተዋል። የመማር ማሰተማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎል እና ዘላቂ ስለሆነ መፍትሄ ደግሞ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል።  

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የሰላም ፎረም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይስተጓጎል ተማሪዎች ምክንያታዊ አመለካከት እንዲኖራቸውና ችግሮችን ከግጭት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድ እንዲያዳብሩ እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል። ስራውም በተማሪዎች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር በየወቅቱ ተማሪዎች ሃገራዊ ኃላፊነት ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ ነው።

የጊቢው አመራሮች ከተማሪዎች ጋር በቅርበት እንዲወያዩ በመደረጉ የሚፈጠሩ ችግሮችና አለመግባባቶች የሚቀረፉት በእንጭጩ  ነው። ተማሪዎች በመቻቻልና በመከባበር ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆም እንዲችሉ በሰላም ዕሴት ግንባታ ላይ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጣቸው መሆኑንም ነው መረጃዎቹ ጨምረው የሚገልጹት። በማደሪያና በምግብ አዳራሽ አካባቢ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በኮሚቴው መፍትሄ ስለሚበጅላቸው የመማር ማስተማር ስራው ሁሌም ሰላማዊ ነው።

  ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲቀላቀሉ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ሀገርና ህዝብ ከእነርሱ የሚጠብቀውን አስፍቶ ማሰብና መረዳት አለባቸውና፤ በፎረሙ አማካኝነት የተለያዩ በራሪ ጽሁፎች ተዘጋጅተው ግንዛቤ የማሳደግ ስራም እየተሰራ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎች ተማሪዎችን ላልተገባ ተግባር በመዳረግ የመማር ማስተማሩን ስራ እንዳይረብሽ በሰላም ክበቡ አማካይነት መረጃዎችን የማጣራትና እውነታውን እንዲያውቁም እየተደረገ ነው። አግባብነት የሌለው መረጃ የተማሪዎችን ስነ-ልቦና እንዳይጎዳም በየሳምንቱ እየተገናኙ በግልጽ እንዲወያዩ እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ተሞክሮ የሚሆን መልካም ተግባር ነው።

  ከዚያ ውጭ ኩሩውና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በአገር ፍቅር ስሜቱ፣ እርስ በርስ ተከባብሮና ተዋዶ በመኖሩ፣ ያለውን ተሳስቦ በመካፈሉና ለእንግዳ ባለው ልዩ አክብሮትና መስተንግዶ መሆኑን ተማሪዎች ጠንቅቀው ሊረዱ ይገባል፡፡ ሰላማዊ መሆን የሚገባውን የፖለቲካ ትግል ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመሩ ኃይሎች ጽንፈኛ አቋም በመያዝ ወጣቶችን መጠቀሚያ እያደረጉ መሆኑንም ሊያጤኑ ይገባል። ይህንን አሳዛኝ ድርጊትና ተግባር በአስቸኳይ የማስቆም ሙሉ ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የተማሪዎችም መሆኑን መተማመን ይገባል። ሌላው ትልቁ ተግባር በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸውን መብቶችና ነፃነቶች ማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በተግባር ማረጋገጥ ከመንግስት የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር ይሆናል።

  ባጭሩ፣ ከዩኒቨርሲቲዎቻችን ምክንያታዊነትን እንጂ ጠብ ጫሪነትን አንጠብቅምና ተማሪዎቻችን ይህን ልብ ሊሉት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy