Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወደ ውስጥ የሚያይ መግለጫ

0 465

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወደ ውስጥ የሚያይ መግለጫ

                                                   ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እያካሄደ ስላለው ግምገማ መግለጫ አውጥቷል። ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ችግሮችን ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ ራሱን ወደ ውስጥ በመመልከት ያወጣው ይህ መግለጫ አስተማሪና የድርጅቱ ነባር የመተጋገል መንፈስ አሁንም መኖሩን የሚያመላክት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ኮሚቴው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የመንስኤያቸው አስኳል ጉዳይ የድርጅቱ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን አልካደም። ድርጅቱ ከስህተቱ ለመታረም ቁርጠኛ አቋምና ባህል ያለው በመሆኑ ሀገራችንን በቅርቡ የገጠሟትን ቀውሶች ለመፍታት አመቺ ጊዜ መፈጠረሩንና በአመራሩ መካከል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም መግለጫው ይገልፃል።

ርግጥ ኢህአዴግ እየተነሳና እወደቀ ዛሬ ላይ የደረሰ የህዝብ ድርጅት ነው። በመግለጫው ላይ ስለተነሱት አንኳር አውነታዎችን ከማስፈሬ በፊት ስለ ኢህአዴግ ጥቂት ለማለስ ፈቀድሁ። ኢህአዴግ እንዲህ ነበር።…

የድርጅቱ አመራርም ሆነ አባላት በየወቅቱ የሥራ አፈፃፀማቸው ይገመገማል፤ ፅናት፣ እምነትና የትግል ቁርጠኝነታቸው ይፈተሻል፤ ስነ ምግባርም ሌላው የመመዘኛ ነጥብ ይሆናል። ኃላፊነትን በቅጡ ሊከውኑ ያልቻሉ፤ የተሰጣቸውን የአመራርነት ሚናን በብቃት ያልተወጡ፤ ተሽለው ያልተገኙና በተግባርም ሚዛን ላይ ተቀምጠው በመሰፈሪያቸው ልክ መመዘን ያልቻሉ አመራሮች ከያዙት የኃላፊነት ደረጃም ተነስተው ዝቅ ብለው ይሰራሉ፤ ጫን ሲልም ከድርጅቱ እስከ መባረር ሊደርሱ ይችላሉ። ይህ አሰራር በኢህአዴግ ውስጥ  የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር የመተጋገል ሂደት ነው።

በዚህ የመተጋገል ሂደት ውስጥ ችግሮች ይጠራሉ። የተዛነፉ አቋሞችም ይስተካከላሉ። አላሰራና አላላውስ ያሉ ፈታኝ ጉዳዩች እልባት ያገኛሉ። ይህን ሃቅ በአስረጅ ለማስደገፍ አንባቢያንን የኋሊት 16 ዓመታትን ልወስዳችሁ ፈቀድሁ። ጊዜው ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት ነው—1994 ዓ.ም። በወቅቱ ህወሓት/ኢህአዴግ ለሁለት ተከፍሎ እንደነበር ድርሳናት ያወሳሉ። ኢህአዴግም እንደ ኢህአዴግ ውስጠ-ድርጅት ቁመናው ለፈተና ተጋልጦ ነበር።

ድርጅቱ ያሳተማቸው ንባበቦች እንደማያሳዩት፤ በወቅቱ “አንጃው” ተብሎ የተሰየመው የጥገኝነት አቀንቃኝ ቡድን በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤ 13 ለ15 በሆነ ድምፅ በመሸነፉ ሳቢያ ዴሞክራሲዊ መንገድን በመርገጥ አሻፈረኝ ብሎ ውይይቱን አቋርጦ ወጣ። ተሰብሳቢውም “የአንጃውን” አባላት “በሰማዕታት አጥንትና ስጋ ይዘናችኋል እባካችሁ ተቀመጡና ተወያዩ” ቢባሉም፤ እምቢኝ፣ አሻፈረኝ በማለት ውይይቱን ረግጠው ወጡ። በዚህም የድርጅቱን ህገ-ደንብ በግላጭ ጣሱ።

ሆኖም በድርጅቱ አሰራር መሰረት ውይይቱ “አንጃውን” አግዶ ባሉት አባላት እንዲቀጥል ተደረገ። የ“አንጃው” አንዳንድ አባላት በወቅቱ በኦህዴድና በደህዴን ውስጥ የነበራቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በሁለቱ ድርጅቶች ውስጥ ያልተገባ አካሄድን ለመከተል ሞከሩ። ደቡብና ኦሮሚያ በእኛ ስር ስለሆኑ ምን ያመጣሉ ሲሉም ታበዩ። እንዲያውም የ“አንጃው” የዝቅጠት አስተሳሰብ በብአዴን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመመታቱ ሳቢያ ጥቂት አምሳያዎቹን በመያዝ በፓርላማ ውስጥ የራሱን መንግስት ለመመስረት ተሯሯጠ።

ዳሩ ግን አብዛኛው ተወያይ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን በመደገፉ ምክንያት ይህ የ“አንጃው” ቀቢፀ-ተስፋ እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ኢህአዴግ እንደ ድርጅት የተጋረጠበትን የጥገኝነትና የዝቅጠት አደጋ በመፍታት በአዲስ መንገድ ላይ ተመመ። ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩ የበላይነትን በመያዙም ድርጅቱም ከብተና፣ ሀገራችንም የህዳሴዋን ጉዞ የምታሳልጥበት መንገድ ታያያዘችው።…ይህን ታሪክ የኋሊት በመሄድ ያነሳሁት ኢህአዴግ ምን ያህል ውስጡን በመፈተሽ ራሱን የማጥራት አቅም ያለው መሆኑን ለማሳየት ነው።

ዛሬ ደግሞ ከ16 ዓመታት በኋላ ድርጅቱ ፈተና ገጥሞት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ግምገማ ላይ ተቀምጧል። የችግሩ ምንጭ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየታየ ያለው ደም አፋሳሽ ግጭትና የህዝብን ጥያቄ በአግባበቡ ያለመመለስ ችግር ነው። ድርጅቱ በመግለጫው ላይ እንደገለፀው ኢሕአዴግ የኅብረተሰቡን ለውጥ የሚመራ ድርጅት ሲሆን፣ አስተማማኝ የለውጥ መሪ የሚሆነውም ራሱንም እየለወጠ መሆኑን በፅኑ ያምናል። ሁሌም ራሱን እየገመገመ ከነባራዊው ሁኔታ የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ለመያዝ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በመታየት ላይ የሚገኙት በዋነኛነት ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከሰላም ጋር የተያያዙ ችግሮች የማያዳግምና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት ቃል ገብቷል። እስካሁን በተደረጉት ግምገማዎችም የችግሮቹን ዓይነተኛ ባህሪዎችና ዋነኛ መንስዔዎች አስመልክቶ ዝርዝር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በአመራሩ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አኳኋን የአስተሳሰብ አንድነት እንደተፈጠረም ገልጿል። የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነት መሰረት በመሆኑም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰጡትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደ ወትሮው በላቀ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑንም አስምሮበታል።

በእኔ እምነት ድርጅቱ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ እያካሄደ ያለው ግምገማ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ምክንያቱም በግምገማው ላይ የሚታዩ ችግሮችን በተሟላ ደረጃ ለመፍታት ሁሉም አመራር ከመቼውም ጊዜ በላይ የጋራ መግባባት ላይ ከደረሰና ችግሩን የውስጣችን ነው ብሎ አምኖ ለመፍትሔው በቁርጠኝነት ከተነሳ እንዳለፉት ጊዜያት የማይፈታው ችግር ሊኖር ስለማይችል ነው።

ለዚህ ደግሞ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በፈጠረው ተስፋና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ፊቱ ላይ በደቀኑት ስጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ እንዳለ በትክክል መገንዘቡ ነው። የአንድን ችግር መንስኤ ማወቅ የችግሩን መፍትሔ ግማሽ ያህል የማወቅ ያህል ይቆጠራል እንደሚባለው፤ ድርጅቱ በችግሮቹ አስኳል ጉዳዩች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱ ለተፈጠረው ችግር ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው ይመስለኛል።

ይህም ሀገራችን የጀመረችውን ፈጣን ዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እስካሁን የመጣበትን ርቀት ለማሳካትም ሆነ ወደፊትም ለማስቀጠል በር የሚከፍት ነው። በድርጅቱ አራት ብሔራዊ አባል ድርጅቶች ውስጥ የነበረውና ያለው አኩሪ በመተጋገል ላይ የተመሠረተ አንድነት ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ይመስለኛል። ስለሆነም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድርጅቱ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረውን የእርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣበትን ሁኔታ ፈትቶ ለህዝቡ ማሳወቅ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። እንኳንስ ሀገርን የሚመራ የአንድ ድርጅት አባላት ቀርቶ የአንድ ኩባንያ ሰራተኞችም በርስ በርሳቸው የሚጠራሩ ከሆነ በተሰማሩበት ስራ ላይ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያስገኙ አይችሉም።

እናም በኢህአዴግ ታሪክ ውስጥ ያልነበረን ይህን ዓይነት የአስተሳሰብ መዛነፍ በፍጥነት በመቅረፍ ወደ ህዝቡ በአፋጣኝ መውረድ የሚገባ ይመስለኛል። ድርጅቱ ራሱን ወደ ውስጥ በመፈተሽ ያነሳቸው ጉዳዩች “ይበል!” የሚያሰኙት ቢሆኑም፤ የችግሮቹን መፍትሔዎች በአፋጣኝ በማበጀት ወደ ተጨባጭ ለውጥ መግባት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ድርጅቱ የያዘው ግምገማ መፍትሔዎችን በማስቀመጥና ነባሩን የመተጋገልና አመራሩንም በስራው ልክ መዝኖ ተጠያቂነትን ማስፈን ወሳኝ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy