Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘመን ተሻጋሪ ዕሴቶች

0 371

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዘመን ተሻጋሪ ዕሴቶች

አሉን!

አባ መላኩ

 

በቅርቡ  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ላይ  የተናገሩት ነገር ቀልቤን  ገዝቶታል። ኢትዮጵያዊነት ማንም ተነስቶ በፈለገው ጊዜ የሚያፈርሰው ወይም የሚንደው ነገር አይደለም፤  ኢትዮጵያዊያኖች በደምና አጥንት ትስስር ያላቸው ህዝቦች ናቸው፤ በአድዋ ጣሊያን ወረራ ወቅት ፣ በሶማሊያ ወረራ ወቅት በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ፣ አምባገነኑን  የደርግ መንግስት ለመጣል፣ በቅርቡ ደግሞ  በባድመ፣ ጾረና እናት አገራቸውን ከወራሪ ሃይል ለመከላከል ሲሉ ኢትዮጵያዊያኖች በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል።  ይህ ንግግር ኢትዮጵያዊነት በደምና በአጥንት የተገነባ ማንነት እንደሆነ ያረጋገግጣል።

 

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች  ባለፉት 26  ዓመታት በኢትዮጵያ  በህዝቦች  መካከል  ከአንድነት ይልቅ  ልዩነቶች  እንዲጎሉ  ወይም ልዩነቶች  ያለመጠን እንዲጎኑ በመደረጋቸው  አሁን ላይ በአገሪቱ  ለሚስተዋሉ ግጭቶች ምክንያት  ሆኗል  የሚል መከራከሪያ ነጥብ ሲያነሱ ይደመጣሉ። ለእኔ ይህ ውሃ የሚቋጥር ምክንያት ሆኖ አላገኘሁትም።  ምክንያቱም  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ማንነታቸውን ማወቃቸው፣ ቋንቋቸውን መጠቀማቸው፣ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው ለአገር አንድነት መላላት መነሻ ሊሆን አይችልም። ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ አንድነትን ማላላት አይደለም።   የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶች ህገ-መንግስታዊ  እውቅና  ማግኘት ለአገራችን ዘላቂ ሰላም   ማረጋገጥ እና  ልማት መፋጠን ምክንያት ሆኗል።   

 

ህገ-መንግስት የአገራችን የመጨረሻው ገዢ ህግ ነው።  ከዚህ ህግ ጋር  የሚጋጭ ማንኛውም ህግ  ተቀባይነት የለውም። እንደእኔ እንደኔ  ለአገራችን ሁከትና ቀውስ ቀዳሚው  ምክንያቱ በህገ-መንግስቱ  የተረጋገገጡ  የህዝቦች መብቶችን  አንዳንድ ሃይሎች ለግል መጠቀሚያነት ማዋላቸው እንዲሁም በህገመንግስቱ የተቀመጡ መብቶች በአግባብ ያለመረጋገጥ  ይመስለኛል።  በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ   የተሰገሰጉ የጥበትና የትምክህት ሃይሎች በተለይ ኪራይ ሰብሳቢዎች የህዝቦች  ህገ-መንግስታዊ መብቶች    እንዲሸረሸሩ  መልካም አስተዳደር  እንዳይኖር  በማድረጋቸው   ህዝቦች  መብታቸውን  በህጋዊ መንገድ  መጠየቅ  ሲጀምሩ ይህን የህዝቦች ትክክልኛ  ጥያቄ  ከለላ በማድረግ  ነውጠኞች አገራችንን ወደ ሁከትና ቀውስ ለማምራት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

 

የጥበት ሃይሎች  ይህ አካባቢ  የአንተ ብቻ ነው፤ ሌላውን አባረው ፣ ዝረፈው፣ ወዘተ በማለት  ሲቀሰቅሱ  ይደመጣሉ።   ኦሮሚያ ለኦሮሞ ብቻ፣ አማራ ክልል ለአማራ ብቻ፣ ትግራይ የትግራዮች ብቻ፣ ወዘተ  የሚባል ነገር  የለም። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ ክልል ወዘተ  ብሎ መለየት ያስፈለገው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን መጠቀምና ማሳደግ  እንዲያመቻቸው  ታስቦ ወሰን  ተበጀ  እንጂ በእነዚህ  አካባቢዎች ሌላው ኢትዮጵያዊ  የመኖር መብት  የለውም ማለት አይደለም። አሁን ላይ እየተመለከትን ያለነው ይህን መረን የወጣ አካሄድ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ  በፈለገው አካባቢ የመኖር የመንቀሳቀስና ንብረት የማፍራት መብቱ በህገመንግስቱ የተረጋገጠ ነው። ይህን መብት  መሸራረፍ አይቻልም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናስተውላቸው አንዳንድ አካሄዶች ህገመንግስታዊነት የጎደላቸው ናቸው።  

 

አዲሲቷ  ኢትዮጵያ የዘጠኝ ክልሎችና የሁለት ከተማ አስተዳደሮች  ድምር ውጤት ናት። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ሁኔታ በእነዚህ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመኖር፣ ሃብት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብት አለው። ህገ-መንግስታዊ፣ ጥበቃም ሆነ  ዋስትና አለው። የሚያሳዝነው  የጥበትና ትምክህት ሃይሎች  ኢ-ህገመንግስታዊ   ሆነው፣ ራሳቸውን  ከህግ በላይ አድርገው  አገር ሲያውኩና ሲያሳውኩ፣ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ህገመንግስቱን ሲጥሱ  አንዳንዶቻችን  በምናገባኝ ስሜት  እየተመለከትናቸው  ነው። ይህ ቅጥ ያጣ ነገር በወቅቱ  ሁላችንም  ተባብረን  ካላስተካከልነው  ነግ በእኔ እንደሆነ  ማወቅ ተገቢ  ነው።  አገር ሰላም የምትሆነው ዘጠኙ  ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሰላም ስትሆን ብቻ  ነው።  ምክንያቱም  የአገራችን ሰላም የእነዚህ  አካሎች  ድምር ውጤት ነው። የአንድ አካባቢ  ቀውስ ወይም ሁከት የሁሉም አካባቢዎች ችግር ነው።

  

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ-መንግስታቸውን ያጸደቁት በነፃ ፍላጎታቸው ነው።  በፍላጎታቸው ላጸደቁት ህገ-መንግስት ተግባራዊነት ሁሉም እኩል ሃላፊነት አለበት። በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት   የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠንካራ አንድነትና አብሮነት አስፈላጊ የሆነባቸው ሁለት መሰረታዊ ዓላማዎች  ተዘርዝረዋል።  በህገ-መንግስቱ መግቢያ  ላይ አንድ ጠንካራ የጋራ የኢኮኖሚያዊና  ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መፍጠር  የሚል  ሃሳብ  ሰፍሯል።  ይህ ሃሳብ ሁለት ነገሮችን  ያዘ ነው።   የመጀመሪያው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ስርዓታቸውን በማጎልበት  ዘላቂ ሰላማቸውን  ማረጋገጥ  የሚያስችል አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መገንባት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማታቸውን  በማፋጠን   የጋራ  ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ  መቻል ነው።  

 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ህብረብሄራዊነታቸው እንደተጠበቁ ሁሉ  በርካታ የሚያስተሳስሯቸው እሴቶችም አሏቸው።  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደምና አጥንታቸው  ያስከበሯትና  የገነቧት  የጋራ አገር አላቸው። አዲሲቷ  ኢትዮጵያ ታሪክ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ፣ ባህልና ብሄረሰባዊ ማንነት እሴቶች ድምርና የጋራ ትስስራቸው ውጤት ሆናለች።  በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መለያ የሆኑት ባህሎች፣ ወጎችና እሴቶች እኩል እውቅናና ጥበቃ አገኝተዋል።  ሁሉም  ባህላቸውን የማስፋፋትና የማዳበር እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብና የማዳበር እኩል መብት ተጎናጽፈዋል።  አዲሲቷ  ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ የታሪክ ድምር  እንድትሆን በርካታ መስዋዕትነት እንደተከፈለ ሁሉ  አሁን ላይ ደግሞ  የጋራ እሴቶቻቸውንም  ለማጠናከር የሚያስችሉ   ስራዎች   መሰራት ይኖርበታል። የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።  

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በአገራችን አንዳንድ ግድፈቶችን  እየተመለከትን ነው።  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመጠቀም መብት ህገመንግስታዊ  ዋስትና እንዳለው  ሁሉ   የጋራ አንድነታቸውን  የሚገልጹበትን  የፌዴራል የስራ ቋንቋ  ማወቅ ግዴታ  ነው ባይባልም እንዲያውቁ ማበረታታት ተገቢ ነው።   ይህ ብቻ አይደለም  የክልል መንግስታት   ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች   አገራዊ አንድነታቸውን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ይኖርባቸዋል። ለአብነት  አንዱ  የሌላን ባህልና ወግ እንዲሀም  ቋንቋ ማወቅና መማር  እንዲችል  ሁኔታዎች  መመቻቸት ይኖርባቸዋል።   የክልል መንግስታት  በክልላቸው  ለሚታዩ ልማቶች እንደሚወደሱ ሁሉ ለሚከሰት  ቀውስም   መፍትሄ በማፈላለግ ረገድም ሚናቸው የጎላ ሊሆን ይገባል።  

 

የጥበትና  የትምክህት ሃሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ  የሚለውን ህገመንግስታዊ መብት በመቆልመም  ለራሳቸው እኩይ ዓላማ ማሳኪያነት  እየተጠቀሙበት ነው።     ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመለከትን  ያለነው ነገር በተለምዶ መጤ ተብለው የተለዩትን የህብረተሰብ  ክፍል  መግደል፣ መዝረፍ፣ ማፈናቀል ከወንጀል የማይቆጠርበት ሁኔታዎች እየተመለከትን ነው።  ይህን እኩይ ተግገባር የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ አካላት ውስጥ አንዳንድ  የመንግስት አመራር አካላት ጭምር  ተሳታፊ  እየሆኑ  እንደሆነ የአደባባይ  ሚስጢር   ሆኗል። እነዚህ ሃይሎች ለማንም የሚበጁ አይደሉም።  አገር የሚያፈርሱና ህዝብን የሚያጫርሱ  በመሆናቸው ለህግ  እንዲቀርቡ  የማድረግ  ጥረት  የመንግስት ስራ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ጸጥታን  በማረጋገጥ  ረገድ ስኬት የሚመዘገበው  የመንግስት ጥረት በህዝብ ተሳትፎ  ሲታጀብ  ብቻ በመሆኑ  ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ  ከመንግስት ጎን በመሰለፍ  ለሰላማችን  እንቅፋት የሆኑትን የጥበትና ትምክህት ሃይሎችን አስተሳሰብና ተግባርን  ማጋለጥ ይኖርብናል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy