Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር…

0 338

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር…

                                                         ታዬ ከበደ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በዘለቄታው እንዲቆሙና በህዝቡ መካከል መተማመን እንዲሰፍን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አቅጣጫ መስቀመጣቸው ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በግጭቶቹ ውስጥ እጃቸው ያለባቸው አካላት ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው እንዲሁም ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው ሲኖሩ በቆዩ ህዝቦች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር እንደሚኖርበት ግልፅ አድርገዋል።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ውስጥ የህግ የበላይነት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ተጠያቂነትም እንዲሁ። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተጠያቂነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድንና ድርጅት በሚያከናውናቸው ስራዎች ተጠያቂ ካልሆነ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አይቻልም። ስለሆነም ለተጠያቂነት ቅድሚያ በመስጠት ህግ ለሁሉም ዜጎች እኩል መሆኑን ማሳየት ይገባል።

ዛሬ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ባለቤቶችና ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሚሆን ዕድገት በሁሉም መስኮች እያስመዘገቡ ነው። በዚህም የህዳሴያቸውን ጉዞ ቅርብ ለማድረግ ግስጋሴያቸውን ተያይዘውታል።

ሆኖም በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። የመንግስት አሰራሮች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንፈስ እውን መሆን አለበት። ይህ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሀገሪቱ ህዝቦች መንገስት እንደያከናውነው የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

እናም መንግስት ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም በመሆኑ በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል። የመንግስት የተጠያቂነት አሰራር የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው። በዴሞክራሲ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው።

ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ በህግ የበላይነት መሰረት ሊጠየቅ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያሉት ይህንኑ ነው። ይህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ይህንኑ ጉዳይ መተግበር ያስፈልጋል።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የህዝቦች አንድነት ማስጠበቂያ መሳሪያ ነው። በአሁኑ ወቅት በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል። የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋግጦላቸዋል፡፡

ርግጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ ነው። ይህን እውነታ የተገነዘበው ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የሀገሪቱ መንግሥትም ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ ነው።

የህገ-መንግስቱ ውጤትም ህዝቦች በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነው ማናቸውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ዕውን ማድረግ አስችሏል። ይህ ፍላጎታቸው እንደ መላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዓይነት መድረኮች ይንፀባረቃል። ይህን መሰሉ መድረክ ደግሞ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫ መሆኑን ከውድድሩ ተሳታፊዎች የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ስብጥር ለመገንዘብ አያዳግትም።   

እርግጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፡ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው፡፡ ይህ እውነታ በተሟላ ሁኔታ ሊገለፅ የሚችለው ልዩነትን በሚያቻችለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እናም ለሀገራችን ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል እንደሆነም አማራጭ የለውም።

ፌዴራላዊ ስርዓታችን በድቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አይደለም። ጠንካራና ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው። በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መፈቃቀድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሁም የህዝቦች አንድነት የሚገለፅበት ስርዓት ነው። ይህን የፌዴራሊዝም እሳቤን በየዓመቱ ከሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአብሮነት ማሳያ በዓል አንዱ መገለጫ ነው።

ዛሬ በሀገራችን ውስጥ የአናሳ ብሔሮች ማንነት በሁሉም መስኮች እንዲጎላና እንዲታወቅ እየተደረገ ነው። ርግጥም በሀገራችን በሁሉም መስኮች የአናሣ ማንነቶች ተሳትፎና ውክልና እያደገ መጥቷል።

ቁጥርን መነሻ ሳይደረግ ሁሉም ማንነቶች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና እንዲያገኙ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት እያንዳንዱ ማንነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ድምፁ እንዲሰማ እድል በመስጠት ከሌሎች ፌዴሬሽኖች የላቀ ርቀት የሄደ ነው ማለትም ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ በቁጥራቸው ማነስ ምክንያት በተወካዮች ምክር ቤት ሳይወከሉ ሊቀሩ ለሚችሉ አናሣ ማንነቶች እድል ለመስጠት በማሰብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሃያ  የማያንስ መቀመጫዎች ተጠብቆላቸዋል። የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎችም አናሣ ማንነቶች በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች እንዲወከሉ አድርገዋል።

ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ብዝኃነት የአብሮነትና የዕድገት ዕድል ሆኗል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ መኖር የሚችሉበትን ባህል እያዳበሩ መጥተዋል።

ታዲያ እዚህ ላይ አንድ እውነታን መገንዘብ ይገባል። እርሱም ፌዴራላዊ ስርዓቱ አልጋ በአልጋ ዕውን እየሆነ የመጣ ነው ማለት አይደለም። ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶች እንዲሁም በስርዓቱ ውስጥ የሚፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በአፈፃፀም ሂደቱ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ አሻራ ማሳረፋቸው አይቀርም።

ይሁንና እኛ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ራሱን በራሱ እያረመና እያስተካከለ የሚሄድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የሚገነባ እንዳልሆነ ሁሉ፤ እዚህ ሀገር ውስጥም የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው ነባራዊ ሃቅ ነው። እናም በሥርዓት አገነባቡ ሂደት ውስጥ ስንክሳሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ስንክሳሮች በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው።

በመሆኑም በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባሪያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሥርዓት መፍጠር ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል። ይህ የሆነው ደግሞ ጠንካራ የህዝብ ትስስር በመፈጠሩ ነው።

በመሆኑም ይህን ትስስር ለሚያላሉ ጉዳዩች ቀዳዳ መክፈት አያስፈልግም። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የሚያላላ ጉዳይ በሥርዓቱ ውስጥ ተቀባይነት ስለሌለው ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር የተጀመረውን ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy