Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠበት ዕለት

0 403

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠበት ዕለት

ኢብሳ ነመራ

በመጪው ዓርብ ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ/ም 12ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ ከተማ ይከበራል። በዚህ በዓል ምናልባት ከሦስት ሺህ የማያንሱ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዑካን ይገኛሉ። በዚህ የልዑካን ቡድን ውስጥ የባህል ልዑካን ዋነኞቹ ናቸው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከበሩ ህዝባዊ በዓላት በሙሉ በዓላማው ትልቅነትና በድምቀት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ቀን የሚያክል የለም።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተከበረው 8ኛ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላይ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተከበረው 9ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላይ የመሳተፍ እድል አግኝቼ ነበር። በእነዚህ ሁለት በአላት ላይ ለቀናት በአንድ መንደር በሚሰፍሩት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል የሚታየው የመተዋወቅ ፍላጎት፣ መደናነቅና ወንድማማችነት ልዩ ስሜት የሚያሳድር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በዓሉን ለማክበር ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጥቂት ቀናት በሚሰፍሩበት መንደር በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት ሊገነቧት ቃል ኪዳን የተግባቡባትን በልዩነት ውስጥ ያለ ጠንካራ አንድነት ያላትን ኢትዮጵያ በስሜት ህዋሳችን መረዳት በሚያስችል ሁኔታ ሞዴሏን ማግኘት ይቻላል።

በተለይ በ2006 ዓ/ም በጅግጅጋ ከተማ የተከበረው 8ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልኡካን የሰፈሩበት በኢትዮጵያ ሱማሌ የባህል ቤቶች ያሉበት መንደር ኢትዮጵያን እንደ አንድ መንደር መመልከትና ማዳመጥ ያስቻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የየብሄሮቹና ብሄረሰቦቹ ልዑካን ቡድኖች በመንደሩ ውስጥ በቆዩባቸው ሶስት ቀናት ምሽት በመንደሩ መሃከል ባሉ ክፍት ቦታዎች ላይ ሁሉም በየራሳቸውን ባህላዊ ጭፈራ መንደሩን በተለያየ የዳንስና የዜማ ህብር ልዩ ውበትና ድምቀት ይሰጡት ነበር። ህብረ ብሄራዊቷ ኢትዮጵያ እነደነዛ ምሽቶች ታምራለች።

ዘንድሮ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መዲና ሰመራ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከጅግጅጋው ጋር ተመሳሳይ ገጽታ የሚኖረው ይመስለኛል። ሰመራም ልክ እንደ ጅግጅጋው ሁሉ የአፋሮች ባህላዊ ጎጆዎች ችምችም ያሉበት መንደር አዘጋጅታ የኢትዮጵያ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችነና ህዝቦችን በዚህ አንድ መንደር ውስጥ ለማስተናገድ እየተጠባበቀች ነው። ይህች መንደር ለሶስት አራት ቀናት ኢትዮጵያ ትሆናለች።

እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ብትሆንም ይህ ህብረ ብሄራዊንት በዘውዳዊውና በወታደራዊው ደርግ የመንግስት ሥርአቶች እውቅና ተነፍጎት መቆየቱ ይታወሳል። ዘውዳዊው ሥርአት የሁሉንም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ማንነት ጨፍልቆ አንድ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊነት የመፍጠር ስትራቴጂ ነበር የሚከተለው። ደርግም ይህንኑ ሥትራቴጂ በተጠናከረ ሁኔታ አስቀጥሎ ነበር። ይህ ስትራቴጂ ተግባራዊ በሆነባቸው አንድ ክፍለ ዘመን ያህል ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ግብር በሚከፍሉበት ሃገር በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት መብት ተነፍገዋል። ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መሰረተ ትምህርት የማግኘት እድል ተነፍገዋል። ባህልና ወጋቸው እንደርካሽ ተቆጥሮ እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል። በእነዚህ እርምጃዎች በገዛ ሃገራቸው ላይ በማንነታቸው አፍረው አንገታቸውን እንዲደፉ ያደረገ ሁኔታ ተፈጥሯል። ማንነታቸውን ለመደበቅ በተለይ ወደከተማ ሲገቡ በቋንቋቸው የወጣላቸውን የመጠሪያ ስማቸውን ለመቀየር ይገደዱ የነበረበት ሁኔታ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ዘውዳዊው ሥርአት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ በወሰን ማስፋት ወረራ የተቆጣጠራቸው አካባቢ የነበሩ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የባለሃገርነት መብት ነፍጎ ነበር። ዘውዳዊው ሥርአት ሃገር የሚለው ህዝብን ሳይሆን መሬቱን በመሆኑ በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች የነበሩትን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የባለሃገርነት መብታቸውን ገፍፏል። ዘር ማንዘራቸው በኖረበት፣ አቅንቶ እያረሰ ሲተዳደር ዘመናትን ባስቆጠረበት መሬት ላይ የመሬት ባለቤትነት መብት ተነፍገዋል። ሰፍረው የሚኖሩበት መሬት ለመሳፍንቱ፣ መኳንነቱ፣ ለሥርአቱ ባለሟሎችና በየደረጃው ለነበሩ የመንግስት ተሿሚዎች ከነባለሃገሩ በርስትነትና ጉልት ተሰጠ። በገዛ መሬታቸው ላይ የባለርስትና ባለጉልት ገባር ጢሰኛ ለመሆን ተገደዱ። በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት ሆነች።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን መብትና ነጻነታቸውን የነፈገ እስር ቤት፣ ይሁን ብለው በጸጋ አልተቀበሉም። ታግለውታል። በመጀመሪያ ባልተደራጀና ግብታዊ በሆነ ሁኔታ በየአካባቢው ሹማምንት ላይ ያተኮረ ትግል ነበር የሚያካሂዱት። ይህ በየአካባቢው በልዩ አጋጣሚ ቀስቃሽነት በግብታዊነት ሲካሄድ የነበረ አመፅ አርሶ አደሩን ለጭፍጨፋና ለአደባባይ ግርፋት ከመዳረግ ያለፈ ውጤት ማስገኘት አልቻለም። ይሁን እንጂ የተደራጀና ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ የነጻነት የትጥቅ ትግል የተጸነሰው እዚህ ግብታዊ አመፅ ውስጥ ነበር። የቀዳማዊ ወያኔን፣ የባሌ አርሶ አደሮችን አመፅ ወዘተ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

ከ1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ነጻነታቸውን የማረጋገጥ ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ የተደራጀ የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀምረዋል። ዘውዳዊውን ሥርአት በተካው ወታደራዊ ደርግ የስልጣን ዘመን በብሄር ተደራጅተው የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ቡድኖች ከሃያ በላይ ነበሩ። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በየአቅጣጫው የከፈቱት የነጻነት የትጥቅ ትግል በመጨረሻ አሃዳዊውን የደርግ ስርአት ዳግም ሊቆም በማይችልበት ሁኔታ ፈንቅሎ አስወገደው።

አዲሲቱ ኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ሲያካሂዱ በነበሩት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተገነባች ሃገር ነች። የሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በሃይል ሳይሆን በፈቃዳቸው በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት አብረው ለመኖር ተስማምተው የመሰረቷት ሃገር ነች። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸውን ነጻ ሃገር ከመመስረት ይልቅ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተደዳሩ በእኩልነት የሚኖሩበትን ሃገር መመስረት መርጠዋል። ይህንን ምርጫቸውንም በህገመንግስት ቃል ኪዳን አስረዋል።

በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ እንደሰፈረው ከዚያ ቀደም በክፉም በደግም የተጋሩትን የጋራ እሴቶች መነሻ በማድረግ፣ ተዛብቶ የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነት በማስተካከል በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበር ለመመስረት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአዲሲቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 8 የህዝብ ሉዓላዊነት በሚል ርዕስ ስር፤

 

  • የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።
  • ይህ ህገመንግስት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው።

 

ይላል።

እንግዲህ፤ በጽሁፉ መግቢያ ላይ ያነሳሁት በየዓመቱ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያለፈ የቆሸሸና የተዛባ ታሪካቸውን አጽድተውና አስተካክለው፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆኑበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመስረት ቃል የተግባቡበት ህገመንግስት የጸደቀበትን ቀን መነሻ በማደረግ ነው የሚከበረው። ይህን ዕለት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መንደር የህብረ ብሄራዊቷን ኢትዮጵያ ሞዴል ፈጥረው የሚያከብሩት፣ አንድነትን የሚያጠናክር ዕለት ነው። ዕለቱ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠበት ዕለት በመሆኑ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy