Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ተግባሮች

0 261

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ተግባሮች

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

ባለንበት ወቅት የፌዴራል ስርዓቱን ሊያጎለብቱ የሚችሉ በርካታ ጉዳዩች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም ክንዋኔዎች ውስጥ በየክልሉ ህዝቦች መካከል በመፈጠር ላይ ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ተጠቃሽ ነው። በተለይ በመቐለ፣ በባህር ዳርና በጎንደር የተካሄዱት ህዝባዊ ኮንፈረንሶች የህዝቦችን የርስ በርስ ግንኙነትንና አንድነትን በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና ነበራቸው።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ የህዝቦች አንድነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ምክንያቱም ሀገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት በህዝቦች ተጋድሎ እውን የሆነና በእነርሱው ፈቃድ ብቻ ማናቸውም ጉዳዩች እልባት የሚሰጣቸው መሆኑ ነው። ፌዴራላዊ ስርዓቱ ባለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት የህገ መንግስቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ እንዲሆኑ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ማንም አይክድም፡፡

በአሁኑ ወቅት በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋግጦላቸዋል፡፡

ርግጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ ነው። ይህን እውነታ የተገነዘበው ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የሀገሪቱ መንግሥትም ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ ነው።

የህገ-መንግስቱ ውጤትም ህዝቦች በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነው ማናቸውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ዕውን ማድረግ አስችሏል። ይህ ፍላጎታቸው እንደ መላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዓይነት መድረኮች ይንፀባረቃል። ይህን መሰሉ መድረክ ደግሞ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫ መሆኑን ከውድድሩ ተሳታፊዎች የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ስብጥር ለመገንዘብ አያዳግትም።   

እርግጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፡ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው፡፡ ይህ እውነታ በተሟላ ሁኔታ ሊገለፅ የሚችለው ልዩነትን በሚያቻችለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እናም ለሀገራችን ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል እንደሆነም አማራጭ የለውም።

ፌዴራላዊ ስርዓታችን በድቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አይደለም። ጠንካራና ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው። በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መፈቃቀድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሁም የህዝቦች አንድነት የሚገለፅበት ስርዓት ነው። ይህን የፌዴራሊዝም እሳቤን በየዓመቱ ከሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአብሮነት ማሳያ በዓል አንዱ መገለጫ ነው።

ዛሬ በሀገራችን ውስጥ የአናሳ ብሔሮች ማንነት በሁሉም መስኮች እንዲጎላና እንዲታወቅ እየተደረገ ነው። እርግጥም በሀገራችን በሁሉም መስኮች የአናሣ ማንነቶች ተሳትፎና ውክልና እያደገ መጥቷል።

ቁጥርን መነሻ ሳይደረግ ሁሉም ማንነቶች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና እንዲያገኙ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት እያንዳንዱ ማንነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ድምፁ እንዲሰማ እድል በመስጠት ከሌሎች ፌዴሬሽኖች የላቀ ርቀት የሄደ ነው ማለትም ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በቁጥራቸው ማነስ ምክንያት በተወካዮች ምክር ቤት ሳይወከሉ ሊቀሩ ለሚችሉ አናሳ ማንነቶች እድል ለመስጠት በማሰብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሃያ  የማያንስ መቀመጫዎች ተጠብቆላቸዋል። የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎችም አናሣ ማንነቶች በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች እንዲወከሉ አድርገዋል።

ዛሬ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ መኖር የሚችሉበትን ባህል እያዳበሩ መጥተዋል። ታዲያ እዚህ ላይ አንድ እውነታን መገንዘብ ይገባል። እርሱም ፌዴራላዊ ስርዓቱ አልጋ በአልጋ ዕውን እየሆነ የመጣ ነው ማለት አይደለም። ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶች እንዲሁም በስርዓቱ ውስጥ የሚፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በአፈፃፀም ሂደቱ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ አሻራ ማሳረፋቸው አይቀርም።

ይሁንና እኛ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ራሱን በራሱ እያረመና እያስተካከለ የሚሄድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የሚገነባ እንዳልሆነ ሁሉ፤ እዚህ ሀገር ውስጥም የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው ነባራዊ ሃቅ ነው። እናም በሥርዓት አገነባቡ ሂደት ውስጥ ስንክሳሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ስንክሳሮች በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው።

በመሆኑም በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባሪያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሥርዓት መፍጠር ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል።  ስርዓቱ አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያደረገ ይመስለኛል።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት የታገለለትንና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቶ ዛሬም ሆነ ነገ በፅናት የሚያምንበትን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማይገሰሱ መብቶች ላይ ከቶም ቢሆን ድርድር የሚያውቅ አይመስለኝም። ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት ተግባር የዚህ እውነታ መገለጫዎች መሆናቸው አይካድም።

ስርዓቱ የህዝቦች መብት አስጠባቂነና በዝቦች መካከል ጠንካራ አንድነት የፈጠረ እንጂ በየትኛውም መስፈርት በህዝቦች መካካል መቃቃር እንዲፈጠር በር የሚከፍት አይደለም። ይህ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የትኛውም ብሔረሰብ ከየትኛውም ብሔረሰብ ጋር ምንም ዓይነት ቅራኔ የሌለው መሆኑን ስለሚያውቅ በራሱ ግፊት ህዝባዊ ኮንፈረንችን እያከናወነ ይገኛል። እነዚህ ኮንፈረንሶች የህዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ናቸው።

በመቐለ ከተማ በትግራይና በአማራ ህዝቦች፣ በባህር ዳር ከተማ የኦሮሚያና የአማራ ህዝቦች፣ በባህር ዳር ከተማ በትግራይና በአማራ ህዝቦች መካከል የተካሄዱት ምክክሮች እንዲሁም በቅርቡ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ህዝቦች መካከል ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምክክር የህዝቦችን አንድነት ይበልጥ የሚያፀኑ፣ የሚያስተሳስሩና በህገ መንግስቱ ላይ የተገለፁትን አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ራዕይን እውን የሚያደርጉ ናቸው። እናም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy