Artcles

                      የመማር ማስተማሩ ሂደት ቀጥሏል

By Admin

December 23, 2017

                      የመማር ማስተማሩ ሂደት ቀጥሏል

                                                                                          ይልቃል ፍርዱ

ዩኒቨርሲቲዎቻችን ታውከዋል፡፡ የሚጠበቅባቸውን የመማር ማስተማር ሂደት የሚስያተጓጉሉ፤ የሰላም አየሩን የሚያደፈርሱ፤ ተማሪዎችን ቤተሰብንም ሆነ ሕዝብን የሚያስጨንቁ ያልተለመዱ ክስተቶች እያየን ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ የጎሳና የዘር ግጭትን በማራገብ ስራ የተጠመዱ አንዳንድ የሚዲያ አክቲቪስቶች ስራዬ ብለው የሚያሰራጩት፣ የሚነዙት፣ የሕዝቡንም ሆነ የተማሪውን መንፈስ የሚያደፈርሱ፣ ቁጣን የሚቀሰቅሱ፣ ስሜትን የሚያናውጡ መልእክቶች ናቸው ችግሩን እያስፋፉት ያሉት፡፡

ወልዲያ በስፖርት ምክንያት የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የሰው ሕይወት መጥፋቱ ቀጥሎም አዲግራት የተከሰተው ግጭትና አደጋ በማሕበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የጎጥ ጎራ ለይቶ ሲጋጭ ከመክረሙም በላይ በፍጥነት መላው ሀገሪቱን ማዳረሱ በአብዛኛው ኦሮሚያና በአማራው ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መነሻነት ተቃውሞ እንዲስፋፋ አድርጎአል፡፡ ይህ አይነቱ ክስተት ለሀገሪቱ እንግዳ ደራሽ ነው፡፡ የጎሳና የዘር ፖለቲካን የሚያራግቡ ክፍሎች ከዚህ እጅግ ኋላቀር የአስተሳብ አረንቋ መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አመለካከትን በአመለካከት መታገል ሲቻል ወደ አካላዊ ጥቃትና ግድያ መሄድ ከሰውኛ አስተሳሰብ በእጅጉ ያፈነገጠ የአውሬነት ባሕርይ ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ሽንፈት ጭምርም  ነው፡፡ ለረዥም ዘመናት በፍቅር፣ በሕብረት፣ በደስታና በችግሩ ሁሉን አብሮ ተካፍሎ የኖረና ያሳለፈን በብዙ ታሪካዊ መሰረቶች ማሕበራዊ ድሮች የተሳሰረና ተዋልዶ ተጋብቶ በደምና በአጥንት ተቀላቅሎ፣ የልጅ ልጅ አይቶ የኖረን ሕዝብ ዛሬ ላይ ደርሶ “ና ተለያይ፤ በየወገንህም ሁን” ቢሉት፣ በዘርና በጎሳ ሊከፋፍሉት ቢሞክሩ መልሱ “አይሆንም፤ ልትለያዩን አትችሉም” የሚለው ስለመሆኑ የሚጠራጠር አይኖርም፡፡

ሰው በተወለደበት ዘርና ጎሳ መነሻነት የጥቃት ሰለባ መሆን የለበትም፡፡ አስተሳሰቡን የግድ ማውጣት እስካልተቻለ ድረስ አደጋው ለሀገርና ለሕዝብ ይተርፋል፡፡ በዚህ አይነት ድኩም አስተሳሰብ የተለከፉና በየትኛውም ጎራ ያሉ ሰዎች ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ መብቱ ሊከበር፤ ሊጠበቅ እንደሚገባ፤ የጎሳና የዘር ጥላቻ ለማንም እንደማይጠቅም ከጥፋትና ከውድመት በስተቀር ሌላ ምንም አይነት ትሩፋት እንደሌለው ከሌሎች ሀገራት አሰቃቂና ዘግናኝ ታሪክ ሊማሩ ይገባል፡፡

በእንዲህ አይነቱ የእርስ በእርስ ትርምስና ሁከት መጠፋፋት የበለጠ ደስተኞችና ተጠቃሚዎች የሚሆኑት የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙና ለዚህም የማባላት ስራ እንቅልፍ አጥተው ሲሰሩና ሴራ ሲጎነጉኑ የሚያድሩ ኃይሎች ብቻ ናቸው፡፡

የተማሪዎችን ሕጋዊ ጥያቄዎች ስርአት ባለው ሰላማዊ ሁኔታ በውይይት በጋራ ምክክር ተነጋግሮ መፍታት እየተቻለ ወደዚህ አይነቱ የጥፋት መንገድ መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ አንድም ተማሪ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ባለዩኒቨርሲቲ የሚማር ሊደበደብም ሆነ ሊገደል አይገባውም፡፡ ለሁሉም ኢትዮጰያ የጋራ ሀገራቸው ነች፡፡ ያለልዩነት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች ናቸው፡፡ ይሄን ግዜ ወለድ እጅግ አደገኛ በሽታ በጋራ ቆመው ሊከላከሉት ሊያስወግዱት ይገባል፡፡ ይህንን የወንጀል ድርጊት የፈጸሙትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጣ ገንፍሎ እንዲወጣ ያደረጉትን አጣርቶ ለሕግና ለፍትሕ ማቅረብ ለሕዝብም ማሳወቅ ከመንግስት የሚጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡

በመላው ሀገሪቱ ያሉ ተማሪዎችን ማንኛዉንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚችሉ፤ ነገር ግን ከሁከት ራሳቸዉን እንዲያርቁ ዩኒቨርሲቲዎች መጠየቃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል የዘገበ ሲሆን የጎንደር፤ ሐሮማያና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተውን አለመረጋጋት ከሐይማኖት አባቶች፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአስተዳደር አካላት፣ ሕብረተሰቡና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባደረጉት ጥረት ዩኒቨርሲቲዎች ወደነበሩበት ሰላም እየተመለሱ መሆናቸውን፤ ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የሚገባቸው መሆኑ ተገልጾአል፡፡

ተማሪዎች ጥያቄዎች ካሏቸዉ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ መብታቸው ነው፡፡ ከዚህ አልፈዉ ወደግርግር፣ ንብረትንና ሕይወትን ወደሚያሳጡ ድርጊቶች መግባትና መሳተፍ የለባቸውም፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደምሴ ደስታ ታህሳስ 2፣ 2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው አለመረጋጋት ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር አሁን ላይ ተማሪዎችን የማረጋጋት ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ወደቀደመ ሰላማዊ መረጋጋቱ እየተመለሰ መሆኑን፤ በሕክምና እና ጤና ሳይንስ ፋኩልቲዎች ትምህርት እንዳልተቋረጠና በሕይወትም ሆነ በንብረት ላይ አንዳችም ጉዳት እንዳልደረሰ ዳይሬክተሩ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሕዳር 19/ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው ትምሕርት 90 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች ወደ መደበኛ የትምህርት ገበታቸው በመመለሳቸው ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ መቀጠሉን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሸት ተሾመ  ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርቸው ይመለሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸውና የመማር-ማስተማር ሂደቱን በተያዘለት የትምህርት መርሐግብር ለማስኬድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን መነሻ በማድረግ በጅማ ዩኒቨርስቲ ተቋርጦ የነበረው መማር ማስተማር  አሁን ላይ በሰላማዊ መልኩ እንደቀጠለ የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ኤክስፐርት አቶ ኩሳ ያደታ ገልጸዋል፡፡ ትምሕርቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ከተማሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ለመተማመንና ለመግባባት ብለዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ከዩኒቨርስቲዎቹ እንዳይወጡና በመረጋጋት ትምህርታቸውን ለማስቀጠል እንዲቻል ምክር መለገስ እንደሚኖርባቸው ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡

በየዩኒቨርሲቲዎቹ እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የፌደራል መንግስት ከፀጥታ አካላት ከክልል መንግስታትና ከዩኒቨርሲቲ ቦርድ አመራሮች ጋር በመሆን እየተከናወነ ያለው ድጋፍ ጠናክሮ እንደሚቀጥል የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

ከተማሪዎች  ጋር የተለያዩ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን  የወልድያ ዩኒቨርስቲ  ያስታወቀ ሲሆን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ  በተማሪዎች  መካከል ተከስቶ የነበረውን  ግጭት  ለመፍታትና ወደ መደበኛ የትምህርት መርሀ ግብር እንዲመለሱ ለማድረግ ውይይት እየተካሄደ  እንደሚገኝ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረው ግጭት ትክክል እንዳልሆነ በተማሪዎች ውይይት ወቅት መተማማን  ላይ መደረሱን በተማሪዎች  መካከል ጤናማ የሆነ ግንኙነት  እንዲፈጠርና መፈራራት እንዳይኖር ለማድረግ የሚደረጉት ጥረቶች መቀጠላቸውን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው  ተማሪዎችን  ለማወያያት 300  የሚሆኑ የተማሪዎችን አደረጃጃት መጠቀሙን  የገለጹት ፕሮፌሰር ያለው ተማሪዎችን በማወያያት በኩል የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ፣ዲኖችና መምህራን የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና እያደረጉም እንደሚገኙ ያስረዱ ሲሆን፤ በዩኒቨርስቲው በዚህ ሳምንት ለተፈጠረው የሰላምና መረጋጋት ችግር መንስኤ የሆኑ ተማሪዎችም ተለይተው  አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነም ፕሮፌሰር ያለው ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በየራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ትምህርት ሚኒስቴርም የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል። ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በየተቋማቱ ያሉትን ተማሪዎች ለማረጋጋት፤ ችግሮችን በመፈተሽም መፍትሔ ለመስጠት ወደ 20 ዩኒቨርሲቲዎች መሰመራታቸውን የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል። የስራ ኃላፊዎቹ ከተማሪዎቹ እና ከሌሎች የትምህርት ማሕበረሰብ አባላት ጋር ሰፋ ያሉ ውይይቶችን እንዳከናውኑም አመልክተዋል።

ተማሪዎቹን አሁን ካሉበት ድባብ በማውጣት ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር  ሒደት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሳሙኤል፤ የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን በማካካሻ ትምህርት እንዲስተካከሉ እንደሚደረግ አብራርተዋል። ተማሪዎችን በማረጋጋት በኩል የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረገውን አስተዋጽኦም አድንቀዋል። የሕዝቦች መተሳሰብና መደጋገፍ ባሕልን ለማበላሸት የሚጥሩ አካላትን በመታገል ረገድ ሕብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር ሳሙኤል ጥሪ አስተላልፈዋል።

 ተቋማቱ ሙሉ ለሙሉ ተረጋግተው ወደ ነበረው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት  እንዲመለሱ የሁሉም ማሕበረሰብ የላቀ ተሳትፎና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። ሰሞኑን በዚሁ ግርግርና ሁከት ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች ሚኒስቴሩ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን ገልጾ ለተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን የተመኘ መሆኑን ገልፀዋል። መንግስት በትምህርት ተቋማቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና አካባቢው ማሕበረሰብ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ባለፉት ጥቂት ቀናት ለውጥ መምጣቱም ተገልጿል፡፡

ባጠቃላይ፣ በቅርብ ቀናት ውስጥ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንደሚመለስ የብዙዎች እምነት እየሆነ መጥቷል፤ ይህ ፀሀፊም ይህንኑ ይጋራል።