Artcles

የመገንጠል መብት ክፋቱ አይታየኝም

By Admin

December 31, 2017

የመገንጠል መብት ክፋቱ አይታየኝም

አባ መላኩ

አንዳንዶች የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 3 በመጥቀስ ህገመንግስቱ የአገሪቱን አንድነት ለአደጋ ያጋልጣል ሲሉ ይደመጣሉ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይህ አንቀጽ በህገመንግስት ሰፈረም አልሰፈረም መገንጠል የሚፈልግ አካል ካለ የሚያግደው አንዳችም ነገር አይኖርም። ለአብነት የካታሎናዊያን ከስፔን፣ ኪዩቤክ ከካናዳ እንዲሁም ስኮታላንዶችን ከእንግሊዝ ለመነጠል ጥያቄ ከማቅረብ አላገዳቸውም። እነዚህ አገራት የመገንጠል መብትን በህገመንግስታቸው ይፋ አላደረጉትም።  እንደእኔ እንደኔ ይህ አንቀጽ በህገመንግስታችን ተጠቀሰም አልተጠቀሰም  ተገፋሁ፣ ተጨቆንኩ የሚል ብሄር ወይም ብሄረሰብ ካለ ለመገንጠል  ጥያቄ  ማቅረቡ  አይቀርም። ይህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ዜጎች መብታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁበት የመረጃ ዘመን ነው።   የኢፌዴሪ  ሕገ-መንግስት  ከመግቢያው ጀምሮ ከመገንጠል ይልቅ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጸኑ  በርካታ አንቀጦችንና ሃሳቦችን  ያካተተ ሰነድ ነው።  ለአብነት  ሕገ-መንግሥታችን መግቢያ ላይ በሕዝቦች መካከል አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ  መፍጠር የሚል  ትልቅ ሃሳብ ሰፍሮ እናገኛለን። ይህ ሃረግ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ሃሳቦችን የያዘ ነው።  

 

ሕገ-መንግስታችን  ባለፉት 27 ዓመታት  በየዘርፉ በአገራችን ለተመዘገቡ ስኬቶቻችን  መሰረት መሆኑን ማንም ሊክደው አይችልም።  የፌዴራል ስርዓታችን  በራሱ የህገ-መንግስታችን አንዱ ውጤት ነው። በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን ዋንኛ ምክንያት አገራችን  የተገበረችው የፌዴራል ስርዓት  ነው። ይህ ስርዓት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፤ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ኃይማኖታቸውን በነጻነት እንዲተገብሩ፣  በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣   ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ወዘተ መልካም ሁኔታዎችን ፈጥሯል።   እነዚህን መብቶች በተግባር ያጣጣማቸው ህዝብ አጣቸዋለሁ ብሎ እንዳይሰጋ “የመገንጠል” መብት እንዳለው  ቢያረጋግጥ  ክፋቱ አይታየኝም።   እውነት እውነቱን  እንነጋገር ከተባለ ማንም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ዳግም ወደ ቀድሞው የአፈናና የጭቆና ስርዓት ለመመለስ አይፈልግም።

 

የአገራችን የፌዴራል ስርዓት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከማስጠበቁ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንም አረጋግጧል።  የፌዴራል ስርዓታችን ህዝቦች አካባቢያቸውን እንዲያለሙ መልካም ሁኔታን በማመቻቸት ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖርም አግዟል። ዛሬ ላይ በሁሉም የክልል ከተሞቻችን አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ትላልቅ ኢቨቶችን ማስተናገድ የሚያስችል  አቅም መፍጠር ችለዋል።  ከዚህ ቀደም እዚህ ግባ የሚባል መሰረተ ልማት  ያልነበራቸው አርብቶ አደር አካባቢዎች ዛሬ ላይ የትላልቅ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠር እንግዶች የሚታደሙባቸው እንደብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በዓላት  ያሉ ኩነቶች  በታዳጋ ክልሎቻችን  በተሳካ ሁኔታ በመከበር ላይ ናቸው።   አራት  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች  በዓላት  በጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ዘንድሮ ደግሞ  በሰመራ በስኬት  ተከብሯል።   እነዚህ  በዓላት  የተከበሩት   በቀድሞ ስርዓት  እዚህ ግባ  የሚባል  መሰረተ ልማት ባልነበራቸው  አካባቢዎች  መሆኑ የሚያመላክተው  ነገር አለ።  ባለፉት 26 ዓመታት  በአገራችን እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በመዕከል ወይም በተወሰነ አካባቢ የታጠረ  አለመሆኑን   ይህ  ጥሩ ማሳያ ነው።

 

እንደእኔ እንደእኔ በአገራችን  የኃይማኖት  እክራሪነት  ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደረገው አንዱና ቀዳሚው ነገር  ህገመንግስታችን  ለኃይማኖት የሰጠው ነጻነት ይመስለኛል።  ዛሬ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። በሃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ስርዓት ተረጋግጧል። በመሆኑም ሃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር መመስረት ተችሏል። ሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮታቸውን በነጻነት የሌሎችን መብቶች አክብረው ማስተማር ኃይማኖታቸውንም በሰላማዊ መንገድ ማስፋፋት  ይችላሉ።  ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ይህን የሃይማኖት ነጻነት የሚለውን መርህ በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ባለፉት 26 ዓመታት አንዳንድ ሃይሎች  የግል ፍላጎታቸውን በኃይማኖት  ከለላ  ለማሳካት   ቢሯሯጡም  በህብረተሰቡ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም።

በአገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም  ማስፈን በመቻሉ  መንግስት ሙሉ ትኩረቱን ወደልማትና ዕድገት እንዲያደርግ አግዞታል። በተለይ  ባለፉት 15 ዓመታት አገራችን ዓለምን ያስደመመ  ባለሁለት አሃዝ  ፈጣን  ዕድገት  ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ስኬት የሕገ-መንግስታችን  ቀጥተኛ  ውጤት ነው።  መንግስት ትላልቅና አሳታፊ የሆኑ ዕቅዶችን በመንደፍና ለተግባራዊነታቸው ጥረት በማድረጉ  በየዘርፉ  ተጨባጭ ለውጦችን  ተመዝግበዋል፤ አሁን ላይ የአገራችን  የድህነት መጠን ከግማሽ በላይ በመቀነስ ወደ  ከ22 በመቶ አካባቢ እንዲወርድ ሆኗል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ   ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ አገር አቋራጭ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የከተማ ቀላል የባቡር መስመር ዝርጋታ፣  ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎች (ከነእጥረታቸው)፣  የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም ሰፋፊ አገር አቋራጭ የመንገድ ግንባታ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታር ዝርጋታ ወዘተ በመካሄድ ላይ ናቸው።  መንግስት በርካታ  ቢሊዮን ዶላር ወጪዎችን በመሰረተ ልማት ማስፋፋት  ላይ በማዋሉ  ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  ኢንቨስትመንት በመሳብ ከቀዳሚዎቹ ተርታ  መሰለፍ ችላለች። በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ የሚውል ገንዘብ ነገ የሃብት ምንጭ እንደሚሆን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግስት  የእያንዳንዷ ሰላማዊ ደቂቃ  ለአገራችን ተጨማሪ የልማት ዕድል የምትፈጥር እንደሆነች  ይገልጻታል። ይሁንና  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ   በአንዳንድ  አካባቢዎች በተቀሰቀሱት ሁከቶች  የአገራችንን ልማትና ዕድገት እየጎዱት እንደሆኑ  መመልካት የሚከብድ አይደለም። የአገራችን ህዝቦች የልማት ፍላጎት ሰፊና ትልቅ ከመሆኑ ባሻገር ፈጣንም ነው። እንኳን ካለን ላይ አፍርሰንለት(አውድመንለት)፤  እንኳን ለልማት የሚለውን ጊዜና ገንዘብ  ለነውጥና ሁከት አውለነው ይቅርና በጀመርነው  ፍጥነት እየሮጥን እንኳን የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ማሳካት አልተቻለም። የአገራችንን ዕድገትና ልማት  የተሻለ የምናደርገው በሰላማችን ላይ መደራደር ስናቆም ብቻ ነው። ይህን ስል መንግስትን መቃወም ተገቢ አይደለም ማለቴ እንዳልሆነ ሊሰመርልኝ እፈልጋለሁ። ይሁንና ተቃውሞዎች ሁሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መካሄድ እንዳለባቸው ግን  አስረግጬ መናገር እፈልጋለሁ። ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የሚደረግ ተቋውሞ  ጤነኛ  አካሄድ  አይደለም። እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ  አካሄዶች  አገራችንን ወዳልተፈለገ  መንገድ  እንደሚያመሯት  ከሶሪያ፣ ሊቢያና የመን  መማር ይመበጀን ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ  ህገመንግስት  ጭቆና ዳግም እንዳይመለስ፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ለብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መብቶች  መረጋገጥ  ዋስትና  የሚሆን  አንቀጽን አካቷል። ይህን ህጋዊ መስመርን  የሚከተል ማንኛውም መገንጠል የሚፈልግ አካል በህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በአግባብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተቀምጧል። የዚህ አንቀጽ በህገመንግስቱ  መካተት የሚያመላክተው   ህገመንግስቱ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ነው። ምክንያቱም ማንም ህጋዊውን መስመር ተከትሎ መገንጠል የሚሻ አካል  ካለ  ግጭት ውስጥ  መግባት ሳያስፈልገው  ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ  የፈለገውን  ማሳካት እንደሚችል ነው።    

በኢፌዴሪ ህገመንግስት ዜጎች በአገራቸው ውስጥ  በየትኛውም  አካባቢ በነፃነት የመዘወዋወር፣  በፈለጉበት አካባቢ የመኖር፣ ሃብት የማፍራት ህገመንግስታዊ መብትና ዋስትና  እንዳላቸው  እንዲሁም  በፈለጉ ጊዜ ከአገር ወጥተው  በፈለጉ  ጊዜ ወደ አገር  ውስጥ የመመለስ መብታቸው የተረጋገጠ  ነው።  ይሁንና  ከቅርበ ጊዜ ወዲህ  እነዚህ መብቶች  በአግባብ  እየተተገበሩ አይደለም።  በአንዳንድ አካባቢዎች  በተከሰቱ  ሁከቶች  የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት በከንቱ ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፣ ንብረቶቻቸው ተቃጠለዋል አሊያም ተዘርፈዋል።  ለዚህ ቀውስ  በዋናነት ከፍተኛ አመራሩ  በተለይ የኢህአዴግ  ስራ አስፈፃሚና  የመንግስት  ከፍተኛ  የስራ ሃላፊዎች ሃላፊነት ይሁን እንጂ  በየደረጃው ያሉ  የድርጅትና የመንግስት  የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ህብረተሰቡም  የነበራቸው ሚና ቀላል የሚባል  አይደለም። የነውጥና ሁከት ጎዳናዎች ሰፊ ሂደታቸውም አጭርና  ቀላል ይሁን እንጂ ውጤታቸው  እጅግ አስከፊና ዘግናኝ ነው። ነውጥና ሁከት  በደቂቃዎች ውስጥ  የበርካታ ንጹሃን ህይወትን ቀምቶናል፣ የበርካታዎችን አካል አጉድሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትንም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።  ለዓመታት የገነባናቸውን  መሃበራዊ መገልገያዎች  እንዲሁም    የግለሰቦች በህይወት ዘመናቸው  ሁሉ ያፈሯቸውን ንብረቶች  በደቂቃዎች ውስጥ አጥተዋል።  መንግስት  የህግ  የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስጠበቅ  ግዴታው ነው።   የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የማይችል መንግስት መንግስት ሊሆን አይችልም። ህብረተሰቡም  ለአገራችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ  ከመንግስት ጎን መቆም ተቀዳሚው ተግባሩ ሊሆን ይገባል።