Artcles

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉና እመርታው

By Admin

December 07, 2017

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉና እመርታው

                                                          ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አኳያ የሚታዩ ናቸው። የዘርፉ እመርታ ለአገራችን የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነት እንዲሁም ለዜጎች ስራ ፈጠራ የሚሰጠውን ጥቅም ከፍተኛ ነው። በተለይም ኢንቨስትመንት በተስፋፋ ቁጥር የወጭ ንድግ ተወዳደሪነታችን እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ዘርፉ ጉልህ ሚና ያበረክታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

አሁንም ግን ከዕድገት ደረጃችን ጋር ተያይዞ ከሚኖረው የገበያ ጉድለት እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ ሊከሰትና ፈጣን ዕድገቱን ሊያስተጓጉል የሚችለው አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። አደጋውን ለማስቀረት አስቀድሞ የተለየና መፍትሔም የተቀመጠለት ጉዳይ ሆኗል።

የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትንና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ ችሏል።

ከዚህ ጎን ለጎንም መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።

መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል። እንደሚታወቀው ለዘላቂና ፈጣን ዕድገቱ ምቹ የሆነ የማክሮ ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል ያለው ሚዛን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን የፈጣን ዕድገቱ አንዱ ምንጭ ኢንቨስትመንት እንዲሆን ተተልሟል፡፡

በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎችና በሌሎች መስኮች የሚከናወኑ የግልና የመንግስት ኢንቨስትመንቶች ፈጣን ዕድገትን በማረጋገጥ በኩል የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።

በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የዘርፉ ምርቶች ጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ከ1ዐ በመቶ የማይበልጥ ነው።

ይሁን እንጂ በዕቅዱ መሰረት በ2012 ላይ ወደ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ይህ ድርሻም ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግና በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ ለማድረስ ግዙፍ ዕቅድ ተቀምጧል።

ሌላው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡ አመላካች የሚሆነው በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የሰው ሃይል ሽግሽግ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛና በከፍተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የተሰማራውና ከ350 ሺህ የማይበልጠውን የሰው ሃይል በቀጣዩቹ አስር ዓመታት በአራት እጥፍ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቧል።

ይህም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዩን ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ነው። እነዚህን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ልማታዊ ፋይዳዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ብርቱ ርብርብ እያደረገ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በአገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

እርግጥ ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል።

በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ስራው ተጠናቆ በአገልግሎት ላይ ለመዋል የተዘጋጀውና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ያሳድዋል ተብሎ የሚጠበቀው የኮምቦልቻው የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከለሌሎች የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ተመጋጋቢ በመሆን ጤናማ ውድድርን እንደሚያካሂድ ይታመናል። በሌሎች የአገራችን ክፍል የተገነቡትና የሚገነቡት ፓርኮችም ተመሳሳይ የውድድር መድረኮች ማሳያ ይሆናሉ።

በዚህ ጤናማ ውድድራቸውም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ያሳድጋሉ። በዚህም ህበረተሰቡም ይሁን የቀጠናው ህዝቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ተጠቃሚነታቸውም ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ ተጠቃሽ አገር እንድትሆን ያስችላታል። በዚህ መሰረትም መንግስት በአሁኑ ሰዓት በመላ አገሪቱ በራሱ ወጪ እየገነባቸው የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን የነደፈውን ዕቅድ ለመሳካት ጥረት እያደረገ ነው። ይሀም የወጭ ንግድን ከፍ በማድረግና ዜጎችን የስራ ዕድል ባለቤት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።