የሥርዓቱ ጥብቅነት መገለጫ
ታዬ ከበደ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጥልቀትና ጥብቅነት የህብረተሰቡ አንድነትና በጋራ ተቻችሎ ለመኖር ያለው ፍላጎት ጥብቅነት መገለጫ ነው። የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት ይዘውት የመጡትን ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴቶቻቸውን በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ይበልጥ አጎልብተዋል። በምንም መልኩ እንዲጠፉበት አይሻም።
የአገራችን ሀዝቦች ፍላጎት በአንድነት በፍቅር ውስጥ አብሮ መኖር ነው። አንድነታቸው የመነሳታቸው ዓይነተኛ ምክንያት አንደሆነ ያውቃሉ። እናም ለአንደነታቸው ያለው ግፊት ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ የትግራይና የአማራ ክልሎች እንዲስተካከሉ ያደረገው የህዝቦች ግፊት ነው።
እነዚህ ሁለት ወንድማማች ህዝቦች በየክልላቸው ግፊት በማድረጋቸው በክልሎቹ መካከል ያለው ሁኔታ ሊስተካከል ችሏል። ይህም ሁሉም ክልል ወደ ውስጥ ራሱን በመመልከት ለጥፋቱ ራሱን ተጠያቂ ማድረግ በማድረግ የሚከሰቱ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት ህዝቡ ያለውን ተነሳሽነት የሚያስገነዝብ ይመስለኛል። የአገራችን ህዝብ መቻቻልና ይቅር ባይነት እንጂ አንዱ ሌላውን በመበቀል የሚመጣ መፍትሔ እንደማይኖር ከህዝቦች አብሮ የመኖር ፍላጎት መማር ማወቅ ይቻላል።
የአገራችን ብሔርና ብሔረሰቦች አብረው የመኖር ፍላጎታቸው የጠነከረው ላለፉት 26 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን አጎልብተው በመገኘታቸው ነው። ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ህብረ ብሄራዊ ሆኖ መዋቀሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተመቸ ሆኗል። ይህም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ማንነቶችንና የጋራ እሴቶችን እያጎለበቱ እንዲመጡ አድርጓቸዋል። ታዲያ ሥርዓቱ ከተመሠረተ ወዲህ በተወሰኑ አካባቢዎች በጎሣዎች መካከልና በአንዳንድ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች መኖራቸው አይካድም። እነዚህ ግጭቶች ፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠራቸው አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም።
እንደሚታወቀው ሁሉ የሚከሰቱት ግጭቶች ግን አንዳንዶቹ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የጎሣ ግጭቶች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከልምድ ጉድለት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ይህንን ተንተርሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ሁከቶች ናቸው። ይህን ማንም አይክድም። ይሁን እንጂ የዜጎችን ሀብረ ብሔራዊ አንድነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ አይደሉም። ምክንያቱም አገራችን ውስጥ እየተገነባ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ስር በመስደድ ላይ በመሆኑ ነው። እርግጥ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ማንነት ተደፍቆ ሊመጣ አይችልም። ተከብሮ እንጂ። ባለፉት 26 ዓመታትም ሁሉም ማህበረሰብ በራሱ ቋንቋ የመናገር መብቱ የተጠበቀለት በዚሁ ፅንሰ ሃሳብ መነሻነት መሆኑ ግልፅ ነው።
የም ሆኖ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል። ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት የሚከተል ስለሆነ ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ በመሆኑ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን የሚያረጋግጥ ነው።
ፅንደ ሃሳቡ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው። ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎችና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስለሆነ ነው። ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ…አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።
ፅንሰ ሃሳቡ በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር የቻለ ነው። በመሆኑም አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል እሴት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። እንደ እውነቱ ከሆነ የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀሬ ነው።
በየቦታው አልፎ…አልፎ የሚታዩት ግጭቶች መነሻቸው ትምክህትና ጠባብነት እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነት የወለዳቸው ጉዳዩች ናቸው። ይሁን እንጂ፤ አመለካከቶቹ አልፎ አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹት አካላት አማካኝነት የሚከሰቱ በመሆናቸው እነዚህን ማነቆዎች ከሕዝቡ ጋር በመሆን ታግ ማሸነፍ ይቻላል።
ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅንሰ ሃሳብ እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን የሚገልፅ ነው። ስለሆነም ሃሳቡ ሁሉም ህዝብ የእኔ ብሔር ነው የሚል ጥቅል እሳቤን የሚቀበል ነው።
የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ዓይን ሲመለከትና አመለካኩን ሲያከብሩ በሌላ ጎኑም እርሱም መከበርን እንደሚያተርፍ ግልፅ ነው።
በዚህ መነሻ መሰረት አገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዕውን መሆንና ማበብ የታገለ ድርጅትና እንዲሁም እሳቤውን በመርህ በፅናት በማስፈፀም ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው። ብዙ ሕዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።
አገራችን ውስጥ የጠባብነት ምህዳርን ፈፅሞ መከርቸም የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል። በዴሞክራሲ ያበበን ብሔርተኝነት ጠባብነትን የሚዋጋ ዓይነተኛ መሳሪያ ነው። ጠባብነት በአካባቢ፣ በመንደርና በጎጥ እንዲሁም በቋንቋ ተመሳሳይነት በመከፋፈል ማናቸውንም ክንዋኔዎች ለመፈፀም የሚደረግ የቡድንተኝነት ስሜት ማራመጃ ነው።
አስተሳሰቡን የሚያራምድ የትኛውም አካል ከእርሱ ውጪ ስላለው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ምንም ዓይነት ደንታ የለውም። በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኘውን ማናቸውም እሴትን በራሱ ምህዳር ውስጥ አጥብቦ በማየት እየተረጎመ ችግሮችን ወደ ውጭ ለመግፋት ይሞክራል።
አገራችን አሁን በምትገኝበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ መቻቻልን መሰረት ማድረግ እንዲሁም አንዱ ሲያገኝ ሌላው በልማታዊ ውጤቱ መጠን የሚያገኝበት ሁኔታ አለ። በዚህ ረገድ የህዝቡ ግፊት ከፍተኛ ነው። የአገራችን ህዝብ ልዩነቶችን ለማጥበብ ያማንንም ይሁንታ የሚጠይቅ አይደለም። በራሱ ግፊት ሁሉንም ነገር የመከወን አቅም አለው። ይሀን የህዝቡ ፍላጎት ደግሞ ሁሉም ሊያከብረው ይገባል። ነገም ቢሆን ይህ ህዝብ ግፊቱና ፍላጎቱ ተቻችሎ፣ ተፈቃቅሮ በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ተከባብሮ በአንድነት መኖር እንጂ ለመናቆርና ለመለያየት የሚከፍተው አንዳችም በር ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። ይሁ ሁኔታም የሥርዓቱ ጥብቅነት መገለጫ መሆኑን መረዳት ይገባል—ሥርዓቱ የተገነባው በህዝብ ነውና።