Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም ዲፕሎማሲያችን ከፍታ

0 284

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም ዲፕሎማሲያችን ከፍታ

                                                      ዘአማን በላይ

ኢትዮጵያ በውስጧ ሰላም የፈጠረች ሀገር ናት። ከጎረቤቶቿ ጋርም ቢሆን ሰላማቸው እንዳይናጋ ከመጠበቅ አንፃር እየሰራቻቸው ያሉ በርካታ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ናቸው። ሀገራችን ከ26 ዓመታት በላይ የራሷን ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ማቆም የሚያስችል ቁመና ያላት ከመሆኗም በላይ፤ የአጎራባቾቿን ሰላምም መጠበቅ የምትችል ሀገር እንደሆነች አስመስክራለች። ይህ ሁኔታ የሰላም ዲፕሎማሲያችን ከፍታ አመላካች መሆኑ ግልፅ ነው።

ዛሬ የኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና እየጨመረ ሄዷል። ይህ የዲፕሎማሲ ድል በንጉሱ ዘመነ መንግስት ወቅት የነበረ ቢሆንም፤ ተቋማዊና በሰለጠነ መንገድ እየተመራ ይበልጥ ተቀባይነታችን እየጎላና እየደመቀ የመጣው በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ መሆን የጀመረችው በኢፌዴሪ መንግስት ነው።

ኢትዮጵያ አፍሪካን ብሎም ዓለምን በሚያስጨንቀው የሙቀት መጠን መጨመር የአፍሪካዊያን ልሳን ሆና ብቅ ያለችው በዚሁ መንግስት ነው። የመፍትሔው አካል ሆናም በቅድሚያ በራሷ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን በአርአያነት ያሳየችውም በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ይህ ሁሉ ተግባሯም በየጊዜው ተቀባይነቷ እንዲጎለብት አድርጓል።

በእኔ እምነት የኢፌዴሪ መንግስት በአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ይሁን በአፍሪካ ህብረት ያበረከታቸው አስተዋፅኦዎች በአሁኑ ወቅት ለተጎናፀፈው የዲፕሎማሲ ድል መሰረት ናቸው። እዚህም ላይ ጥቂት ምሳሌዎችን ማንሳት ይገባል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት ማድረግ የጀመሩት በአፍሪካ ህብረት ወቅት ነው። የሱዳንንና የወቅቱን የደቡብ ሱዳን አማፅያንን ችግር በኢጋድ በኩል ለመፍታትና ለቀውሱ እልባት ለመስጠት ኬንያ-ናይሮቢ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ውጤታማ የሆነበትን ድል አስመዝግቧል። ይህ የሀገራችን ጥረትና የተገኘው ውጤት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አድናቆት ሊያገኝ ችሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በየትኛውም ሀገር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት ሳይሆን፤ የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራችን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል። “ለምን?” ቢሉ፤ እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው።

ርግጥም እንኳንስ የድንበር አዋሳኞቻችን ቀርቶ የሩቅ ሀገራት ሰላም መሆንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ እሙን ነው። ይህም በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ሰላም እጅ ለእጅ ለማደግና በዚህም አፍሪካዊ ህዳሴን ማጎልበቱ አይቀሬ ነው።

ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ለተጫወተው የኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን  ጠንካራ እምነት የገለፁበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ይህም ሀገራችን የተጎናፀፈችው ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።

ደቡብ ሱዳን እንደ የራሷን ነፃ ሀገር ከመሰረተች ጀምሮም ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ይህም በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ጉዳዩች ላይ ያተኩራል።

በአሁኑ ወቅትም ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ሀገራችን ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም አንዱ የዲፕሎማሲ ከፍታችን ነው።

አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጉዜ ጀምሮም በውስጧ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግስት ከኢጋድ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል።

የመንግስታችን ከጐረቤት ሃገሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ይህን መነሻ ታሳቢ ባደረገ መልኩም መንግስታችን ለሰላም ካለው ጽኑ አቋም በመነሳት ለዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ጐረቤት ሀገር ሱዳን፣ በተለይ ደግሞ በቅርቡ ሰላሟ እየደፈረሰ ለምትገኘው ደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

ለዘመናት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ለህዝባቸው ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተው፣ የናፈቁትን ሰላምና ልማት ማጣጣም የጀመሩት የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ድርጅታቸው “ኤስ ፒ ኤል ኤ ”ዳግም ወደ እርስ በርሰ ጦርነት በመግባቱ ለከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት መዳረጋቸው ወቅታዊው ዕውነታ ነው።

ርግጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ወቅታዊ ችግር የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ መሳብ ቢችልም እልባት ከመስጠት አንፃር ግን የኢፌዴሪ መንግስትና ኢጋድን ያህል የተንቀሳቀሰ የለም ማለት ይቻላል።

ሁላችንም እንደምንገነዘበው የዓለማችን አዲስ ሀገር በሆነችው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ የአደጋው ተጋላጭ የሚያደርገው በዋነኝነት የሀገሪቱን ዜጎች መሆኑን እስካሁን ከደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መገንዘቡ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው። ያም ሆኖ ግን ዳፋው ለአካባቢው ሀገራት መትረፉ አይቀሬ ነው።

ኢጋድና የኢፌዴሪ መንግስት የደህንነት መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በማመን፣ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር የማስመስከር እንቅስቃሴያቸውን በመጀመር ግምባር ቀደም ሚናቸውን በመጫወት ላይ የሚገኙትም ለዚህ ነው።  

የዚህ ጥረት ማሳያ ሰሞኑን እዚህ መዲናችን ውስጥ በደቡብ ሱዳን ሰላም ላይ የሚመክር ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑ ነው። የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት 59ኛ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት፤ በደቡብ ሱዳን የተፈረመው የሰላም ስመምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመሆኑ በተፈጠረው ግጭትና በተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል ብለዋል። በሀገሪቱ እየተከሰተ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዲቆም ሁሉም ወገኖች እ.ኤ.አ በነሐሴ ወር 2015 የተፈረመው የሰላም ስመምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ቁርጠኛ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የሀገራችን ተሰሚነት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሆኑ ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ይህን የሰላም ፍላጎት እውን ያደርጉታል ብዬ አስባለሁ።

ያም ሆኖ ይህ የኢፌዴሪ መንግስት አቋም ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ሀገራችን ለቀጣናው ህዝቦች ሰላም መሆን ካላት ቀናዒ ፍላጎት የመነጨ ነው። በቀጣናው ውስጥ የአንድ ሀገር ህዝብ መጎዳት ዞሮ…ዞሮ ለሀገራችን የሚኖረው ዳፋ የሚታወቅ በመሆኑ ህዝቦች ሀገራቸው ውስጥ በሰላም እየኖሩ ለቀጣናው ልማት እመርታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያግዛል። በሂደትም ክፍለ አህጉራዊው የኢኮኖሚው ትስስር ይበልጥ እንዲዳብር ያደርጋል።

ይህም ሀገራችን የምትከተለውና የቀጣናው ሀገራት በምጣኔ ሃብት ተሳስረው ሁሉም ከሚገኘው እድገት ተቋዳሽ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። እያንዳንዱ ሀገር የተፈጥሮ ሃብተቱን በአግባቡ ካለማና በፍትሐዊነት መጠቀም ከቻለ በዚያው ልክ ለግጭትና ለቁርቋሶ ምንጭ የሆኑትን ውስጣዊ ተጋላጭነቱን ይቀንሳል። ቀጣናውም የሰላም መናኸሪያ ይሆናል።

ይህም እጅ ለእጅ ተያይዞ እንደ አንድ ቀጣና ለማደግና ዴሞክራሲም እንዲያብብ በር ይከፍታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናው ፋና ወጊ ሀገር በመሆኗ ልምዷን ለማካፈል ትችላለች። ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ስርዓት ሰላንም፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ከማረጋገጥ አኳያ ምን ያህል ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ እንደጠቀመ ለደቡብ ሱዳን ወንድሞቻችን ትምህርት የሚወስዱበት ይመስለኛል። የሀገራችን የዲፕሎማሲ ከፍታ ምክንያት መሆኑንም ይረዱታል ብዬ አስባለሁ። እናም ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከእነዚህ የሀገራችን ስኬቶች በመማር ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ለመፃዒ ባለ ተስፋ እድሎቻቸው ተግተው ሊያስቡ ይችላሉ እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy