Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀድሞው መተማመንና መደጋገፍ ያሻል

0 400

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቀድሞው መተማመንና መደጋገፍ ያሻል

 

አባ መላኩ

የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የድርጅቱ አንጋፋ ታጋዮች  ከታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ጥልቅ ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። ግምገማው ትኩረት  ያደረገው  ድርጅቱ  ከጥልቅ ታሃድሶ ወዲህ ያለውን አፈፃፀም  ላይ ነው። ከኢሕአዴግ ጠንካራ ጎኖች መካከል  ተጠቃሽ ነው የምላቸው  ድርጅቱን ችግር በገጠመው ጊዜ ሁሉ  አመራሩና አባሉ ችግሩን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ  ወደ ውስጥ የመመልከትና በጥልቀት የመገምገም  ባህል እንዲሁም ለችግሮች በጋራ መፍትሄ የመፈለግ አሰራሮች ናቸው። እንደእኔ እንደኔ ውድቀት  የሚጀመረው ችግሮችን በሌላ አካል ለማሳበብ ሲሞከር ይመስለኛል።  

 

ከሰሞኑ የኢህአዴግ መግለጫ ላይ እንደተመለከትነው ለችግሮች ዋንኛ ምንጭ አድርጎ  የወሰደው ከፍተኛ አመራሩን ነው። ይህ ትልቅ ሃላፊነት ነው።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢህአዴግ ውስጥ  መደነቃቀፎችን እያስተዋልን ነው። ድርጅቱም በመግለጫው ይህንኑ  አምኖ መፍትሄዎችን  በመፈለግ ላይ ነው።  ድርጅቱ ካለፈባቸው  ተሞክሮዎች  መረዳት እንደሚቻለው አሁን ላይ የገጠመውን መደነቃቀፎች  በድል እንደሚወጣ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይህን ያልኩበት አንዱ ምክንያት  ከፍተኛ አመራሩ ችግሩ የራሱ መሆኑን  መረዳት መቻሉ፤ ይህንንም ለህዝብ ሳይደብቅ መግለጹ ነው። “Good start half done” ፈረንጆች እንደሚሉት  ነው።  

 

ኢህአዴግን  ለስኬት  ያበቃው ሁሌም ራሱን እየገመገመ ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ራሱን ለማስተካካል የሚያደርገው ጥረት ነው።  ከነባራዊ  ሁኔታ ጋር ራስን  እያስተካከሉ  መጓዝ በራሱ ትልቅ  ችሎታን የሚጠይቅ ነው። በአገራችን ታሪክ ኢህአዴግ በመልካም ስነ-ምግሩ በጥሩ ዓረዓያነቱ በቀዳሚነት የሚፈረጅ ብቸኛ  የአገራችን ፓርት ነው ብል አብዛኛዎቻችንን የሚያስማማ እውነታ ነው።

 

በኢህአዴግ የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት፣ ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ ሁሌም የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት የነገሰበት ፓርቲ  ነው። ይህ አሰራሩም ብዙሃኑን ያማከለ፣ ከአንባገነናዊነት የፀዳና በግልፅነት ላይ የተመሰረተ አሰራርን የሚተገብር በመሆኑ በርካታዎችን ወደፓርቲው  አባልነት እንዲሳቡ ያደረገ ነገር ይመስለኛል። ይህ የድርጅቱ  መልካም  ባህሪያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ጥቅመኛ  አባላቱና አመራሩ መሸርሸር እየታየባቸው ነው። ድርጅቱም ሁኔታዎችን ገምግሞ ለማስተካከል ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

 

ኢህአዴግ ከምስረታው ጀምሮ  በጠንካራ የግምገማ ሂደት  ውስጥ  እያለፈ  የመጣ ድርጅት ነው።  የድርጅቱ   የግምገማ ባህል በአባላት መካከል ተጠያቂነ እንዲጎለብትና የህዝብ ተዓማኒነትን እንዲያተርፍ  አድርጎታል።  በርካታ የድርጅቱ የቀድሞ አባላት ለግል ጥቅምና ስብዕና  ደንታ የሌላቸው ለህዝብ ጥቅም  የቆሙ እንደሆኑ በተግባር አሳይተዋል።  ለዚህም ጥሩ ማረጋገጫ የሚሆነው አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በስኬት ጎዳና መጓዟ ነው።  

 

ኢህአዴግ ከምስረታው  ጀምሮ  ያስመዘገባቸውን  ዋና ዋና ስኬቶች  ለማንሳት ያህል  1983 ዓ. ም የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ኢትዮጵያን ከብተና መታደግ መቻሉ፣ 1994 ዓ. ም በከፍተኛ አመራሩ መካከል በተፈጠረው  የአመለካከት መከፋፈል የመስመር ማጥራት ስራ በማድረግ አገሪቱን በፈጣን ዕድገት  ምህዋር ውስጥ እንድትገባ ማድረጉ፣ በ1997 ዓ. ም የቅንጅት አካሄድን ተከትሎ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጠናከር ማድረጉ ናቸው።

 

ከላይ ካነሷኋቸው  እውነታዎች ባሻገር  የኢህአዴግ ጥንካሬ ነው ብዬ የማነሳው  ነገር የታላቁን መሪ ህልፈት ተከትሎ በድርጅቱ ውስጥ  የታየውን ነገር ነው።  2005 ዓ. ም ማገባደጃ ላይ የታላቁ መሪ ህልፈትን ተከትሎ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች   ኢህአዴግ  አበቃለት ፈረሰ  ሲሉ  ድርጅቱ  በስኬት ጎዳና  መጓዝ መቀጠሉ  እንዲሁም  ከ2008  ጀምሮ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች  የሚስተዋሉ  የመልካም አስተዳደር  ችግሮች ለመቅረፍ  ድርጅቱ ሁኔታዎችን  በጥሞና እየገመገመ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ላይ መሆኑ  ኢህአዴግ ራሱን ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ለማስተካከል እያደረገ ያለውን ጥረትና ብቃት የሚያሳዩ ናቸው።  

 

ድርጅቱ ሰሞኑን እያካሄደ ያለውን ግምገማ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው በከፍተኛ አመራሩ መካከል የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር  ተችሏል። በድርጅቱ መርህ መሰረት የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነት መሰረት በመሆኑ አሁን ላይ የተፈጠረው ስምምነት መልካም ጅምር የሚያስብል ነው። በአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ  ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮችና አባላት መካከልም ሁሌም   የሃሳብ ፍጭት  በጣም የተለመደ ክስተት ነው። በድርጅቱ መርህ መሰረትም  የሃሳብ ልዕልና የሚረጋገጠው በድምጽ ብልጫ  በመሆኑ  ዴሞክራሲያዊ  አሰራር የነገሰበት ፓርቲ  ነው።  

 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በድርጅቱ አመራሮች መካከል የርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣበት ሁኔታ መኖሩን የድርጅቱ  መግለጫ ያመላክታል።  ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰጡትን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣትና አሁን የተፈጠረውን ችግሮች ለመቅረፍ  የድርጅቱ የቀድሞው ጥንካሬ፣ የአመራሩና የአባላቱ ቀድሞው መተማመንና መደጋገፍ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። አንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ታማኝና ጠንካራ ከሚያደርገው ባህሪያት ቀዳሚው አባላቱ ለግል ስብዕና እና ጥቅም ከመሯሯጥ ይልቅ ለድርጅቱ ወይም ለፓርቲው ዓላማና መርሆ ተገዥ መሆን መቻል ነው።  

 

ከቅርብ ጌዜ ጀምሮ  አንዳንድ ነገሮች መልካቸውን  እየቀየሩ መምጣት መጀመራቸውን  ድርጅቱ ሳይደብቅ በመግለጫው ጠቁሟል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የድርጅት አባላት ወርቃማውን የድርጅቱን  መርሆዎች  እያጎደፉት ነው። በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የጥበትና የትምክህት  አመለካከቶችና ተግባራት በድርጅቱ ውስጥ እየገነገኑ ናቸው።  ቀድሞ የድርጅቱ አባላት በፈንጂ ላይ ለመረማመድ እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም ይባባሉ  የነበረው  አስተሳሰብ ዛሬ ላይ  በግለኝነት  እየተለወጡ  ናቸው።

ባለፉት 27 ዓመታት ለአገራችን ስኬቶች ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል ብል  ያጋነንኩ አይመስለኝም። በእያንዳንዱ የአገራችን ስኬቶች ውስጥ የኢህአዴግ አስተዋጽዖ ወሳኝና በጉልህ የሚስተዋሉ የአደባባይ እውነታ ነው። ከኢህአዴግ ቀዳሚ አገራዊ ስኬቶች  መካከል  ለእኔ  የጎሉት  ህገ-መንግስታዊ አገር መፍጠር መቻሉ፣ ብዝሃነትን  ማረጋገጥና አንድነት የማስጠበቅ ስኬቱ፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በማጎልበት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን መብት ማረጋገጥ መቻሉ፣ ለተከታታይ 15 ዓመታት ተከታታይና ባለሁለት አሃዝ ፈጣን ዕድገት ማረጋገጥና ፍትሃዊ ተጠቀሚነት ለማረጋገገጥ መጣር ተጠቃሾች ናቸው።  ማህበራዊ መገልገያዎችን በተለይ በጤናና ትምህርት  ማስፋፋት  አኳያ ተጨባጭ  ለውጦች ተመዝግገቧል።  ሌላው በኮንስትራክሽን ዘርፍ የታየው ዕድገትም አገሪቱን  ፈርሳ እንደገና የምትገነባ እስከመባል አድርሰዋታል።  

 

የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ በሂደትም የሚፈቱ ነገሮች ናቸው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች  የዴሞክራሲ ባህላችን እየዳበረ በሄደ ቁጥር ጠያቂ ህብረተሰብ  እየጎለበተ የሚሄድ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም መፈጠራቸው አይቀርም። የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት የሚቻለው በሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን በመቀራረብና በመነጋገር ብቻ ነው። በአገራችን የሰላማዊ ትግል ባህል ሊጎለብት ይገባል። በቀጣይ በየትኛውም መስፈርት በአገራችን በነውጥና በሁከት ወደ መንግስት ስልጣን መሰቀልም ሆነ በነውጥና ነውጥ ከስልጣን ማንንም ማውረደ  አይቻልም። እንሞክረው ብንልም ይህ አይነት አካሄድ  ለማንም የሚበጅ አይሆንም። በዚህ መንገድ የምትፈጠር አገርም ለማንም የማትበጅ እንደምትሆን ከሊቢያ፣ ሶሪያና የመን መረዳት ይቻላል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy