Artcles

የበቀል መዳረሻው የት ይሆን?  

By Admin

December 29, 2017

የበቀል መዳረሻው የት ይሆን?  

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተል ከጀመረት  27 ዓመታትን አስቆጠረች።  በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ የቀንዱ አካባቢ ሠላም ደሴት መሆኗን በተግባር አሳይታለች። አገራችን የተረጋጋች ሠላም የሰፈነባት ለመሆን የበቃችው የህዝቧቿ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት መከተል በመቻሏ ብቻ ነው። በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ለአብነት የብሄር፣ የኃይማኖት፣ የማንነት፣ የአስተሳብ የሚስተዋሉባት እንዲሁም በዓለም በነውጥ ቀጠናነቱ በሚታወቀው ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምሥራቅ አፍሪካ  ቀጠና የምትገኘው ኢትዮጵያ ስኬታማ  ለመሆን የበቃችው በፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓቷ ነው። ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩት አሃዳዊ ሥርዓቶች አገሪቱን ለምን ዳርገዋት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።   

 

እንደእኔ እንደኔ በ21ኛው ዘመን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ ራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ተግባር ይመስለኛል።  አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን የፌዴራል ሥርዓት ችግር እንዲገጥመው የሚደረጉ ሩጫዎች ለማንም የሚበጁ አይመስለኝም።  በኢትዮጵያ የህዝቦች  የሠላም፣ ልማትና  የዴሞክራሲ ጥያቄዎች  ምላሽ   ማግኘት  የጀመሩት  በዚህ የፌዴራል ሥርዓት ነው። ችግሮች መኖራቸው የሚካድ አይደለም፤ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ተነጋግረን ልናስተካክላቸው የምንችላቸው ናቸው። በነውጥ  የሚመጣ  ለውጥ  መዳረሻው አይታወቅም። በቀል የሠላምን መንገድ  እየዘጋ ነውጥና ሁከትን እያባባሰ ወደ ውድቀት ይመራል እንጂ መልካም ነገርን አያመጣም።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን  ዘላቂ ሠላም አስፍኖልናል፤  ልንለማ፣ ልናድግና ልንለወጥ እንደምንችል በተጨባጭ አሳይቶናል። ብዝሃነትን በአግባብና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ እንደሚሆነም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥሩ ምሣሌ ናት።  የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን  ተቀብሎ  ዴሞክራሲያዊ  በሆነ  ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የሥርዓቱ ዋልታና ማገር በመሆን በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነትን የሚያጠናክር የአንድነት ማሰሪያ ገመድ ነው። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ከተረጋገጠ አብሮነትን የሚጠላ አካል አይኖርም። እስካሁን ያለው አብሮነትም የስኬታችን ዋነኛ መነሻም መድረሻም ነው።  

 

መንግሥት ልዩነታችንን ሊያሰፉ ህዝብን ሊያራርቁ የሚሯሯጡ ኃይላትን ከህዝቡ ጋር በመተባበር ህግ ፊት ሊገትራቸው ይገባል። የህግ የበላይነት መቼም ለድርድር መቅረብ የለበትም።  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በቅርቡ እንደተናገሩት ግጭት የቀሰቀስ ወይም ግጭት እንዲባበስ ያደረጉ ማንኛውም አካላት ከህግ ተጠያቂነት አያመልጡም። ይህን ጉዳይ  በተግባር ማየት እንፈልጋለን። ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ  ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጠባቦችና ትምክህተኞች  የህልውናችን  መሠረት የሆነውን የፌዴራል ሥርዓታችንን ለመበተን የሚያደርጉትን መሯሯጥ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈን ልንዋጋቸው ይገባል። ይህ ነገር ከመፈክር አልፎ በተግባር ልንፈጽመውም ይገባል። ለህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ የነውጠኞችንና የሴረኞችን መሰሪ አካሄድ ሊያወግዝ ይገባል።  የጥፋት ኃይሎችን ለህግ በማቅረብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለድርድር እንደማይቀርብ ማረጋገጫ መሆን መቻል አለበት። ይህ ሲሆን ሌላውም ትምህርት ያገኛል፤ በቀጣይም ሌሎች  የጥፋት እጆችም ይሰበስባሉ።   

 

ጥቅመኞች ለህዝብና  አገር  ተቆርቋሪ  በመምሰል  አንዱን ብሄር ተጠቃህ፣ ተናቅህ፣ ወገኖችህ አለቁ ድርስላቸው ወዘተ በማለት በግጭቶች ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። በእውኑ እነዚህ ኃይሎች ለኅብረተሰቡ ተቆርቁረው ነውን? ይህን መመርመር ይገባል። አንዳንድ ሚዲያዎችም በዚህ ረገድ አካሄዳቸውን ቢያጤኑት መልካም ይመስለኛል።  የወቅቱን ነበራዊ ሁኔታዎች በቅጡ ካለመረዳት ይመስለኛል የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ስሜት ቆስቋሾች ሆነው ይታያሉ። የበቀል መንገድ  የትም አያደርስም። በበቀል አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና  ወድቀት ነው።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻል፣ መከባበርና አብሮ መኖርን ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነው። ህዝቦችን በማጋጨት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ለማንም አይበጅ። እወክለዋለሁ ለሚባለው ብሄርም  ቢሆን  በመደጋገፍና በመተሳሰብ  አብሮ በመኖር እንጂ  በመነቋቆር የሚያገኘው አንዳችም ትርፍ የለም። ባለፉት 27 ዓመታት ተቻችለንና ተከባብረን አብረን በመኖራችን በርካታ ነገሮችን አትርፈናል፤ ሰፊና አማላይ ገበያ፣ ጠንካራና አዳጊ ኢኮኖሚ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ መንግሥት፣ በሥነ ምግባር የታነፀ ህዝባዊ  የፀጥታ ኃይል ወዘተ።

 

በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በህዝቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም በፌዴራል ሥርዓታችን ጉድለት ሣቢያ የተከሰቱ ችግሮች እንዳልሆኑ ግን  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀ ውስብስብ ችግሯን መፍታት የቻለችው በዚህ የፌዴራል ሥርዓት ነው። አንዳንዶች እዚህና እዚያ የሚነሱ ትናንሽ ግጭቶችን እንደማሣያ በማቅረብ  ፌዴራል ሥርዓቱ  ድክመት አድርገው ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በተጨባጭ ያየነው ግን አገሪቱ በስኬት ጎዳና መጓዟን ነው።  ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች፣ የበርካታ ኃይማኖቶች፣ በርካታ አስተሳሰቦች፣ በርካታ ባህሎች ወዘተ  ያሉባት አገር በመሆኗ እነዚህን ልዩነቶች ሊያስተናግድ የሚችል የአስተዳደር ሥርዓት መከተል የግድ ይላታል፤ ይህ ሥርዓት ደግሞ ከነእጥረቱም ቢሆን  የፌዴራል ሥርዓት ብቻ ነው። እውነትም ይህ ሥርዓት የኢትዮጵያን ችግሮች አክሞ ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቱን በስኬት ጎዳን እንድትረማመድ  አድርጓታል።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን  የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች ከማረጋገጥ ባሻገር አገሪቱን በፈጣን  የምጣኔ ሀብት ለውጥ ምህዋር ውስጥ አስገብቷታል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ ተሰሚነት ባለፉት 27 ዓመታት እጅጉን  ተለውጧል፤ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም በመስፈኑ  በዓለም አቀፍ ደረጃ  የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው። ከባድ ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቢከሰትም በራስ አቅም መቋቋም ተችሏል።  ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ  በአፍሪካ ሆነ  በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን በተባበሩት መንግሥታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን መንግሥት ባከናወነው  ተግባር ነው።   ይህ የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬት አይደለምን? እነዚህን ትላልቅ  የፌዴራል ሥርዓታችን  ስኬቶች ወደ ጎን ተብለው  ለምን  ትናንሽ ነገሮችን ብቻ ለማጎን እንሽቀዳደማለን?

 

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ሠላም ዘላቂ እንዲሆን ከምታደርገው የሠላም ማስከበር ሥራ ባሻገር አገራት በምጣኔ ሀብት ጥቅም እንዲተሳሰሩ በርካታ ተግባራትን  በማከናወን ላይ ትገኛለች። ለአብነት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱ ነው።   በታዳጊ  አገር  አቅም ለመገንባት አይታሰብም የሚባለውን ይህን ፕሮጀክት አሁን ላይ  ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህስ የፌዴራል ሥርዓቱ እውን ከሆነ በኋላ የመጣ ስኬት አይደለምን? እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን  ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ሙገሳ ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ከ850 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች።  

አገሪቱ ከላይ ያነሳኋቸውን ስኬቶች  ማስመዝገብ የቻለችው ሕዝቦቿ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ በመኖራቸው ነው። አብሮ መኖር ያስቻለን ደግሞ ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ የስቻለን  የፌዴራል ሥርዓታችን ነው። በመሆኑም አንዳንድ ኃይሎች  በአገሪቱ  የሚስተዋሉ  የመልካም አስተዳደር ችግሮች  ሁሉ  የፌዴራል ሥርዓቱ እንከኖች አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።  አንዳንዶች ደግሞ ለህዝብና  አገር  ተቆርቋሪ  በመምሰል ትናንሽ ግጭቶችን በማጎን  እከሌ የተባለው ብሄር ሊያጠቃህ ነው፤ ተነስ፣ ለወገኖችህ  ድረስላቸው ወዘተ በማለት  በግጭቶች  ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። የሌለን ነገር እየፈጠሩ ብሄሮችን ማጋጨት ለማንም የማይበጅ የፖለቲካ አካሄድ ነው።  የበቀል መንገድ  የትም አያደርስም። በበቀል አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና  ወድቀት ነውና።