Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብሄር ብሄረሰቦች በዓልና ወቅታዊ ሁኔታ

0 342

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሄር ብሄረሰቦች በዓልና ወቅታዊ ሁኔታ

                                                           ታዬ ከበደ

በቅርቡ ለ12ኛ ጊዜ በተከበረው የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦች በዓል ላይ በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከወሰን ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ህይወት መመለሳቸው የማይቀር ጉዳይ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

እንደሚታወቀው ሁሉ ቀደም ሲል መንግስት ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሰው በሰላም የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው ሊከበሩ እንደሚገባ፣ እነዚህን መብቶቻቸውን የጣሱና የሚጥሱ አካላት የህግ ተጠያቂነት እንደሚሆኑ፣ የሁሉንም ዜጎች ህገ መንግስታዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት በዋነኛነት የክልል መስተዳድሮች እንደሆነ አቅጣጫ ማስቀመጡ አይዘነጋም።በዚህ አቅጣጫ መሰረትም በሁለቱም ክልል አመራሮች ባካሄዱት ምክክር ውጤት እየተገኘበት ነው።

እርግጥ የአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለግጭት ቦታ የሚሰጥ አይደለም። ችግሮችን የሚፈታበት የራሱ መንገድ አለው። የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ- መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው።

ይህ የአገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህም ይመስለኛል— ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችብን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

ያም ሆኖ ያለፉት ሥርዓቶች በህዝቦች መካከል የፈጠሩት የተዛባ ግንኙነቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት እጥረቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚታዮ ግጭቶች መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው አይካድም። እርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ይመስለኛል። እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በሥልጣኔ በገፉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ ነባራዊ ክሰተት ነው። በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚመላለሰው የሰው ልጅ ቀርቶ ህይወት የሌላቸው ግዑዛን ነገሮችም በተፈጥሮ እንቅስቃሴ ሳቢያ ሊጋጩ ይችላሉ።  

እርግጥ ከሰው ልጅ ግጭቶች አኳያ በዓለማችን ላይ የተፈጥሮ ሀብት እጥረት መኖሩ እንደ መንስዔ የሚታይ ነው። ሀገራችንም ከዚህ የተፈጥሮ ዕውነታ ልትርቅ አትችልም— እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባትና። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል። ዳሩ ግን ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ይህን ዕውን ለማድረግም ሥርዓቱ አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ እየሰራ ይገኛል።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያለፉ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማረም በሚያደርገው የእኩልነትና የፍትህ ተግባራት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። የተዛቡ የህዝቦች ግንኙነቶችን በማስተካከል በሚደረጉ የፍትህና የእኩልነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለፉትን ስርዓቶች በመናፈቅ አሊያም በዚያኛው ዓይነት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሀገራችን እንድትመራ የሚፈልጉ አካላት ግን ይህን ሁኔታ ሊገዳደሩት ይሞክራሉ—ምንም እንኳን ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ለዚህ የሚሆን መፈናፈኛ ባይሰጣቸውም።

እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ አላቸው። መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሐዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ በህገ መንግስቱ ገልፀዋል። ላለፉት 26 ዓመታት እያከናወኑት የመጡትም ይህን እውነታ ነው።

ምንም እንኳብ ያለፉት ስርዓቶች በህዝቦች መካከል የተዛቡ ግንኙነቶችን ፈጥረው ቢያልፉም፣ ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በእኩልነትና በፍትህ ዴሞክራሲያዊ መንገዶች እነዚህ ችግሮች እየተቀረፉ ነው። ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወቱና ፍትህንና እኩልነትን ከማጠናከር አኳያ የሄደባቸው መንገዶች አጥጋቢ ናቸው።

በአገራችን ውስጥ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ ሲያበቃ፤ በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ማህበረሰብ የድንበር ግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልሎች የድንበር አካባቢዎች የተከሰተ ግጭት ሀዝብን የሚወክል ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

ስለሆነም ችግሩ በመስተዳድሮቹና ህዝቡ የጋራ ጥረት እንዲሁም በሥርዓቱ መሰረት የህግ አግባብን ተመርኩዞ የሚፈታ ነው። ከላይ ለአብነት በቀረቡት ክልሎች መካከል የተካሄደው የድንበር ማካለል ችግሮችን እልባት የመስጠት ተግባር  ወደፊትም ከድንበር ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች ካሉ ስርዓቱ ባለው አሰራር መሰረት የሚፈታው መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታም ስርዓቱ ማናቸውንም ችግሮች በራሱ የአሰራር ስርዓት የመፍታት ብቃትና አቅም መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ህገ መንግስቱ እውን የሆነበት የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን እነዚህን ችግሮች የመፍታት አቅም አለው። የሚፈታውም በተግባር በሚገለጥ የህግ ማስከበር ስራ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የችግሩ ተዋንያን የሆኑ ሃይሎች ይጠየቃሉ በማለት የገለፁት ከዚህ አግባብ በመነሳት ነው።

ሆኖም አንዳንድ ሃይሎች ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ሁኔታውን ሊያዛቡት ይሞክራሉ። ግና መቼም ይሁን መቼ ህዝብን የገደለ፣ አካለ ጎዶሎ ያደረገና ያፈናቀለ ሃይል መጠየቁ አይቀርም። ይህን ማድረግ ሥርዓቱ የህግ የማስከበር አሰራር ነውና። ስለሆነም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን የመንግስት አቋም በመደገፍ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy