Artcles

የብሔርና ብሔረሰቦች ቀን ከሰላም አኳያ

By Admin

December 07, 2017

የብሔርና ብሔረሰቦች ቀን ከሰላም አኳያ

                                                       ታዬ ከበደ

ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም የሚከበረው የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አክብረን ስንውል ዕለቱ በአገራችን እንዲመዘገብ ያስቻለውን ሁለንተናዊ ለውጥን አንዘነጋም። በተለይም የሁሉም ነገሮች ቋጠሮ መፍቻ የሆነውን ሰላም ልንዘክረው የሚገባ ይመስለኛል።

ዕለቱ በአገራችን ላመጣው አስተማማኝ ሰላም እንዲሁም ህዝቦች በዚህ ሰላም ተጠቅመው ያሳኳቸውን ሁለንተናዊ ጉዳዩችን ማሰብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውሰጥ አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ አገራችንና ዜጎቿ ከራሳቸው አልፈው የጎረቤቶቻቸው መድን እንዲሆኑ መቻላቸውንም ማሰብ ያስፈልጋል።

በአገራችን እውን መሆን የቻለው አስተማማኝ ሰላም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ችሏል። ይህም የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ የሆነውን ሰላም በመመለስ ለትግላቸው እውቅና በመስጠት ጥያዌዎቻቸውን መመለስ ችለዋል።

ፌዴራሊዝም ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ፤ በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፌዴራሊዝም የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም እንዲችሉ አድርጓቸዋል።  

እናም ስርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል። ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩት ሁከትና ግጭቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ይመስሉኛል።

ያም ሆኖ ህዝቡ በሰላሙ ላይ ስለማይደራደር ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር እንዳይኖር አድርጓል። ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው የሚነቀሳቀሱ ሆነዋል።

በዚህም በመልካም አስተዳደርና በሙስና ህዝቡን ሲያማርሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሃይሎች የፈጠሩት ምሬት ከትምክህትና ከጥበት አራማጆች አጀንዳ ጋር ተዳምሮ የሀገራችንን ሰላም ማወኩ የቅርብ ጊዜ ትውሰታችን ነው።

እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ። የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሔር ብቻ ልዕለ ኃያል ነው ብሎ ያምናል። እንዲሁም ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየነው ብሎ ከማሰብ በተጨማሪ ‘ሁሌም ለመግዛት የተፈጠርኩ ነኝ’ በማለት የሚያምን ነው።

በአንፃሩም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራ እና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ፣ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ የመቁጠር አባዜ የተጠናወተው ነው።

የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም የመቀበል ተፈጥሮ የለውም። እናም በተቻለው መጠን ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን ቀዳዳዎችን በሙሉ ሲጠቀምባቸው ተመልክተነዋል። ይሁን እንጂ፤ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በህዳር 29 ድል ተቀልብሷል።

በአሁኑ ሰዓት የአገራችን ህዝቦች ፌዴራለዊ ሥርዓት በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡

ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም ችለዋል፡፡ እናም ሥርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት የቻለ ሆኗል፡፡

ምንም እንኳን ሥርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ ቁመና ቢያበቃትም ቅሉ፤ አሁንም አንዳንድ የሰላም ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ነው፡፡ ሆኖም ቸሁንም ቢሆን መፍትሔው ሥርዓቱ ብቻ ነው።

እርግጥ አገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትናንት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች እየፈታ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሥርዓቱን ተግዳሮቶቹ እየፈተኑት ቢሆኑም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንገስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በሥርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እየፈቱ ይቀጥላሉ፡፡  

በሌላ በኩልም በፌዴራል ሥርዓቱ እውን የሆነው ሰላም ለጎረቤቶቻችንም ዋስትና እየሆነ ነው። ኢትዮጵያ የራሷን ሰላም ከማሰከበር አልፋ የጎረቤቶቿም መመኪያና አለኝታ መሆን ችላለች።

የኢፌዴሪ መንግስት ለአገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ምክንያቱም የአገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለአገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም። አገራችን በአሁኑ ሰዓት በዳርፉር፣ በአብዬና በሶማሊያ የምታካሂደው የሰላም ማስጠበቅ ስራዎች ለጎረቤቶቻችን የተረፍን መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። ውጤቶቹም ህዳር 29 ያስገኘልን ነው።