Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተፈናቃይ ወገኖች እጣ ፈንታ ቅኝት

0 375

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተፈናቃይ ወገኖች እጣ ፈንታ ቅኝት

ኢብሳ ነመራ

2010ን የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን መቀበያ ለማድረግ ተፍ ተፍ ሲባል በነበረበት ሰሞን፣ በአንድ የሃገሪቱ ጥግ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ዜጎችን ከኑሯቸው ያፈናቀለ፣ ብዙዎች ህይወታቸውን ያጡበት የእርስ በርስ ግጭት አጋጥሞ ነበር፤ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች ነዋሪዎች መሃከል። ግጭቱ እንደወትሮው በድንበር አካባቢ ያጋጣመ አልነበረም። በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል እስከ ክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ የዘለቀ፤ በኦሮሚያ በኩልም በተለይ የጫት ንግድ ማዕከል በሆነችው የምስራቅ ሃረርጌዋ አወዳይ ከተማ ድረስ የዘለቀ ነበር። እናም ግጭቱን በሁለቱ ክልሎች መሃከል ወሰን ባለመካለሉ የተፈጠረ ነው ብሎ መውሰድ የዋህነት ነው። የግጭቱ ሰበብና ዓላማ ሌላ ነው። ይህን ጉዳይ በይደር ልተወውና በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎች እጣ ፈንታ ላይ ላተኩር።

በግጭቱ እስከ 5 መቶ ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ከኑሯቸው መፈናቀላቸው ሲነገር ሰምተናል። የተፈናቃዮቹን ቁጥር ይህን ያህል ነው ተብሎ ቁርጥ ያለው መጠን እስካሁን አልተገለጸም። በተለይ በፌደራል መንግስት ሚዲያዎችና የስራ ሃላፊዎች በድፍኑ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ሲባል ነው የሚሰማው። በኦሮሚያ ክልል በኩልም ቢሆን እስከ 4 መቶ ሺህ፣ አልፎ አልፎም ከ 5 መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ የሚል ግምት መሰል አሃዝ ከመጥራት ያለፈ ቁርጥ ያለ ቁጥር ሲገለጽ አልተሰማም። የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ደግሞ ጭራሽ በዚያም በኩል የተፈናቀሉ መኖራቸውን ከመግለጽ ያለፈ ቁጥር ለመጥራት የደፈረ አይመስልም። በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ያለው ሁኔታ ላይ አተኩረው የመስራት ዝንባሌ የሚታይባቸው አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎችም ቢሆኑ የገለጹት ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ፣ እስከ 5 መቶ ሺህ የሚደርሱ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ብዙዎች ይስማመሙበታል።

እነዚህ ተፈናቃዮች በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የምስራቅና የምእራብ ሃረርጌ አካባቢዎች፣ ምእራብ አርሲ ሻሸመኔ፣ አዲስ አበባም (አዲስ አበባ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሁለት ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ሰፍረው ይገኛሉ) በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የነብስ አድን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛሉ። እነዚህ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ቤተሰብ መስርተው፣ ሃብት አፍርተው የተረጋጋ ህይወት ሲኖሩ የነበሩ ዜጎች ከዚህ በላይ ለተራዘመ ጊዜ በጊዜያዊ መጠለያ የእለት ደራሽ እርዳታ እያገኙ መኖር የማይገባቸው መሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስማማ ይመስለኛል። ወደመደበኛ ቋሚ ኑሯቸው መመለስ አለባቸው። ተፈናቃዮቹ ንቁ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ሃብት በመፍጠር ራሳቸውን ከማሸነፍ አልፈው ለሃገሪቱ እድገት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ከሚችሉበት የኑሮ ሥርአት ውጭ ሆነው፣ ሌሎች ካፈሩት ሃብት ላይ እየተሸረፈ በሚሰጥ ምጸዋት እንዲኖሩ ያደረገ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ለመኖር መገደዳቸው ለአፍታም መዘንጋት የለበትም።

የኢፌዴሪ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ የያዘውን አቋም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል። ይህም ተፈናቃዮቹ ወደቀድሞ ኑሯቸው መመለስ አለባቸው የሚል ነው። ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት እስካሁን በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካኝነት የምግብ እርዳታ እያቀረበ ከመሆኑ ያለፈ ተፈናቃዮቹን ወደቀድሞ ኑሯቸው ለመመለስ የሰራው ተጨባጭ ነገር አልታየም። ተፈናቃዮቹ አሁንም ከ3 ወር በፊት ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሲሰፍሩ የነበረው አይነት ኑሮ ላይ ናቸው። እርግጥ በተለይ የኦሮሞ ህዝብ፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች፣ ባለሃብቶች ወዘተ ስፍራው ድረስ በመሄድ የሚያደርጉላቸው ማበረታቻና እርዳታ፣ እስካሁን ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም እስከ 4 መቶ ሚሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ ማሰባሰባቸውና ይህ ተጠናክሮ መቀጠሉ  ተፈናቃዮቹ ተስፋ እንዳይቆርጡ አድርጓቸዋል። ይህ ባይሆን ኖሮ እስካሁን ከክልሉም አልፎ የፌደራል መንግስቱን ፈተና ላይ የሚጥል ከባድ የፖለቲካ ቀውስ መፈጠሩ አይቀሬ ነበር።

የፌደራል መንግስት እየገለጸ ካለው ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት ኑሮ ከመመለስ ፍላጎት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃሙድ ኡመር ከክልላቸው የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል። አቶ አብዲ ሰሞኑን ከአንድ የግል ሬድዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ከግጭቱ አነሳስና መፈናቀል ጋር አያይዘው ያነሷቸው ጉዳዮች ዜጎች በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ እይታ እንዲኖራቸው ያደረገ ነው። የአቶ አብዲ መግለጫ የብዙዎችን ዜጎች ቀልብ ለመማረክ በቅቷል። አቶ አብዲ በቃለ መጠይቁ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሚያ ተወላጆች ወደነበሩበት አካባቢ ተመልሰዉ ቤት ንብረታቸዉ ተጠብቆላቸዉ እንደሁሉም ዜጋ በሰላም የመኖር መብት አላቸዉ። የተፈናቀሉትን ባሉበት ቦታ ሄጄ ለምኜም ቢሆን አመጣቸዋለሁ፤ በድርጊቱ በጣም አዝኛለሁ ሲሉ ተደምጠዋል። በመንግስት ቤቶች ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ተፈናቃዮች መሃከል 98 በመቶ የሚሆኑት በንብረታቸዉ ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን፤ በግለሰቦች ቤት ተከራይተዉ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችም ንብረት ጉዳይ በአከራዮቻቸዉ አማካኝነት ለፖሊስ ሪፖርት መደረጉንም አሳውቀዋል።

አቶ አብዲ የተናገሩት እውነት መሆኑ ላይ ማንም ጥርጣሬ የለውም። ይሁን እንጂ፤ በመቶ ሺህ ሚቆጠሩትን ተፈናቃዮች በፍቃዳቸው ወደነበሩበት ኑሯቸው፣ ሃብትና ንብረታቸው እንዲመለሱ ለማነሳሳት ይህ በቂ ነው ወይ? እውነቱን ለመናገር በቂ አይደለም። አቶ አብዲ አሁንም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ስለሚሰነዘረው በመሳሪያ የታገዘ ጥቃትና የሰዎች ሞት ምንም የተናገሩት ነገር የለም። ይህ ጥቃት አሁንም እንዳልተቋረጠ ከአካባቢው የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ጋዜጠኛውም አቶ አብዲ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ አልጠየቁም። ይህ ብቻ ይደለም፤ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀልና እስካሁን ቁጥራቸው ላልተገለጸ ሰዎች ህይወት መጥፋትና ሌሎችም ለወሬ የማይመቹ ጥቃቶችን በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለህግ በማቅረብ በኩል አሁንም ሰፊ ክፈተት ይታያል።

በዚህ ጉዳይ እስከ 39 የሚደርሱ ሰዎች መጠርጠራቸውን መንግስት ይፋ አድርጓል። አቶ አብዲ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ አንድ ሰው በክልሉ የጸጥታ ሃይል ተይዞ ለፌደራል መንግስት መተላለፉን ብቻ ነው የነገሩን። በሶስት ወራት ውስጥ ከአንድ ተጠርጣሪ በላይ መያዝ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው? ከዚህ በተጨማሪ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በማፈናቀል፣ በበርካቶች ሞትና በሌሎች ጥቃቶች የተጠረጠሩት ሰዎቸ ቁጥር 39 ብቻ መሆኑ ብዙዎችን ግር ያሰኘ መሆኑም ሊስተዋል ይገባል።

እነዚህ እውነታዎች ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ለመመለስ የደህንነት ዋስትና እንዲያጡ ያደርጋቸዋል። እናም የፌደራል መንግስቱ ተፈናቃዮችን ወደኑሯቸው ለመመለስ ያለው ፍላጎትና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር መግለጫ ብቻውን ተፈናቃዮቹ በፍቃዳቸው ወደነበሩበት እንዲመለሱ ያደርጋል የሚለውን መቀበል ስህተትነቱ ያይላል። እናም የደህንነት ዋስትናን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው።

በኦሮሚያ ክልል በኩል ተፈናቀለው ተወላጅ ወደሆኑበት ክልል የሸሹትን ዜጎች ለመርዳትና በሃገራቸውና በወገናቸው እንዲኮሩ፣ ተስፋ እንዲያድርባቸው ለማድረግ የተሰራውና እየተሰራ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው። ይህ አስደናቂ ተግባር በአርአያነት ሊጠቀስ የሚገባው ሆኖ ሳለ ከክልሉ ሚዲያ ያለፈ የማንኛውንም የሃገሪቱን ሚዲያ  (የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያ) ሽፋን አለማግኘቱ በብዙዎች ዘንድ በበጎ አልታየም። የኦሮሞ ህዝብ ሁኔታውን በዝምታ ትዝብት እያስተዋለው መሆኑን ልብ በሉ።

ይሁን እንጂ፤ የኦሮሚያ ክልል ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የተፈናቀሉትን የኦሮሞ ተወላጆች ወደነበሩበት ኑሮ፣ ሃብትና ንብረት እንዲመለሱ የማድረግ ተግባር ቀዳሚ አማራጭ መሆኑን ችላ ያለ ይመስላል። ተፈናቃዮቹን አስገድዶ ወደነበሩበት ኑሮ መመለስ ባይቻልም፣ ቀዳሚውና በአቅም ውስጥ ያለው አማራጭ ግን የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በዚህ ዙሪያ በተፈናቃዮቹ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር ለመመለስ ፍቃደኛ እንዲሆኑና እንዲደፋፈሩ በስነልቦና የማዘጋጀት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም። እንደውም በተቃራኒው ወደነበሩበት ኑሮ የመመለሱ እድል የተዘጋና ያበቃ ነው የሚመስለው።

ግማሽ ሚሊየን የሚደርሱ ተፈናቃዮችን እንደአዲስ ኦሮሚያ ውስጥ ማቋቋም ቀላል ስራ አይደለም። ክልሉ ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም ያስፈልጋል ብሎ ከገመተው 1 ነብ 5 ቢሊየን ብር በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ሃብት የሚጠይቅ መሆኑ እርግጥ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ለመኖሪያ የሚሆን ሰፊ መሬት፣ የመተዳደሪያ ስራና ለስራ ፈጠራ የሚያስፈልግ ቢያንስ በብድር መልክ የሚቀርብ ሃብት፣ ይህን የሚያስፈጽም ትልቅ ተቋምና ከፍተኛ የአስተዳደር ወጪ ይጠይቃል። በመሆኑም ተፈናቃዮቹን እንደ አዲስ ማቋቋም ወደኑሯቸው የመመለሱ አማራጭ አልሆን ሲል የሚወሰድ የመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ መወሰድ አለበት።

ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት አለመመለስ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ለዘለቄታው የሚኖረው መልካም ግንኙነትና ወንድማማችነት ላይ የሚያጠላ መሆኑም መታሰብ አለበት። ተፈናቃዮቹን ወደኑሯቸው መመለስ ከአቅም አንጻር የሚመረጥ ብቻ ሳይሆን ለህዝቦች መቀራረብና ትስስርም ወሳኝ የሆነ በገንዘብ የማይተመን ውድ ፋይዳ ያለው መሆኑ መታሰብ አለበት።

በአጠቃላይ የፌደራል መንግስትና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መንግስት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ተፈናቃዮች በፍቃዳቸው ወደኑሯቸው እንዲመለሱ ማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ የደህንነት ዋስትና የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው። የኦሮሚያ ክልልም ተፈናቃዮቹን እንደአዲስ ማቋቋም ከአቅም አንጻር ፈታኝ መሆኑን፣ ለዘላቂ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነትና ሰላምም የማይበጅ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት እንዲመለሱ በስነልቦና ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ተፈናቃዮቹን ኦሮሚያ ውስጥ እንደ አዲስ የማቋቋም ጉዳይ ተመራጭ የሚሆነው የፌደራል መንግስትና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር፣ ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ ተፈናቃዮቹ በራሳቸው ፍቃድ እንዲመለሱ የሚያነሳሳ ሁኔታ መፍጠር ሲያቅታቸው ብቻ መሆኑ ሊታወስ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy