Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያ የመልማት ግብና ለግብፅ “የሞትና የሽረት ጉዳይ” የመሆኑ የተሳከረ ፖለቲካ

1 492

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ የመልማት ግብና ለግብፅ “የሞትና የሽረት ጉዳይ”

የመሆኑ የተሳከረ ፖለቲካ

 

ስሜነህ

በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁ ነው የተባለ የዓሳ ማምረቻ ከቀናት በፊት በተመረቀበት ወቅት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፣ “የግብፅን የዓባይ የውኃ ድርሻ ማንም እንደማይነካው ለግብፃዊያን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤” ማለታቸውና የዓባይ ውሃ “ለአገሪቱ [ለግብፅ] የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው” ማለታቸው የተፋሰስ ሃገራቱን መገናኛ ብዙሃኖች ቀልብ የገዛና ሰሞንኛ የተፋሰስ ሃገራቱ ህዝቦች የሰርክ ወሬ ሆኗል።  

ለኢትዮጵያና ለሱዳን የግብፅን የዓባይ የውሃ ድርሻ ማንም ሊነካው እንደማይችል የተናገሩት አልሲሲ፣ ከህዳሴ ግድቡ ግንባታ ጀርባ ያለውን የኢትዮጵያን የመልማት ግብ እንደሚረዱ ገልጸው ሲያበቁ ይህ የኢትዮጵያ የመልማት ግብ ግን ለግብፅ “የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፤” የማለታቸው ተቃርኖ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

የግብፅ ባለሥልጣናት በህዳሴ ግድቡ የተፅዕኖ ግምገማና የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጥናት መዘግየት ሥጋት እንደገባቸውና የተፅዕኖ ግምገማው መነሻ እ.ኤ.አ. የ1959 የቅኝ ግዛት ስምምነት እንዲሆን ያቀረቡት ጥያቄ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን ውድቅ መደረጉ ከላይ ለተመለከተው የአልሲሲ ንግግር መነሻ እንደሆነ የሚናገሩ ባይጠፉም አብዛኞቹ ምሁራን ግን የንግግራቸው መነሻ በውስጥ የገጠማቸውን ፖለቲካ ለማስቀየስ ወይም ለማርገብ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። የእርሳቸው መነሻ ምንም ይሁን ምን ግን በግብጽ የሚገኙ አንዳንድ ሚዲያዎች እና ተቋማት የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በግብጽ ህልውና ላይ የተነጣጠረ አደጋ አድርገው የማስተጋባት ዘመቻቸውን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ተያይዘውታል። ይህ ተረክም የመልማታችንን መብት ለሚረዳው የግብጽ መንግስት መልሶ የመልማታችን መብት የሞት ሽረት ጉዳይ የሚሆንበትን ተቃርኖ የሚያሄስና የታላቁን ግድብ እውነታ የሚገልጥ ይሆናል።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የሦስቱ አገሮች (የግብጽ ሱዳን እና ኢትዮጵያ) ብሔራዊ ኮሚቴ 16ኛውን ስብሰባ ከማካሄዱ በፊት፣ የአገሮቹ የውሃ ሚኒስትሮች የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጎብኝተው የነበረ መሆኑ ይታወሳል። በወቅቱ የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ (ዶ/) የግድቡ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት በመዘግየቱ ሥጋት እንደተሰማቸው የገለጹ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም የግብፅ ሚዲያዎች ሚኒስትሩ በግድቡ ግንባታ ዕድገት ምክንያት የሦስትዮሽ የቴክኒክ ውይይቱ ትርጉም አልባ ነው የሚል እምነት መያዛቸውን ጨምሮ አፍራሽ የሆኑ ዘገባዎችን ማሰራጨታቸውን ቀጥለውበታል። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ድርድሩን በራሷ ተነሳሽነት የጀመረችው መተማመንን ለማዳበር እንጂ በፕሮጀክቱ ላይ ሌሎች አገሮች ውሳኔ እንዲያሳልፉ አለመሆኑ ይታወቃል። በጥቅሉ ሲታይ የእነዚህ ሚዲያዎች እና የተቋማቱ መነሻ ግድቡ በግብጽ የውሃ ድርሻ ላይ መሠረታዊ ጉዳት ያመጣል የሚል መሆኑ የማያከራክር እና የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን በጥንቃቄ ልንመለከተው የሚገባ ዘመቻ ነው።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፅዕኖ ግምገማ፣ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጥናት ላይ ድርድር እያደረጉ ቢሆንም፣ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመኑን እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት ግድቡ ሊያመጣ ለሚችለው ጉዳት መነሻ እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ በኢትዮጵያና በሱዳን ውድቅ መደረጉ እነዚህን ሚዲያዎችና ተቋማት ያንጨረጨራቸው ለመሆኑ አያጠያይቅም።

የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ስለሚኖረው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ እንዲሁም የውኃውን ሙሌትና አለቃቀቅ ለማስጠናት በድርድር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በካይሮ ለ17 ጊዜ ተገናኝተው ቢመክሩም፣ ግብጽ ከዚያው ካረጀው አስተሳሰብ ባለመላቀቋ ስምምነት ላይ ሊደርሱ አልቻሉም። ከዚህ አስተሳሰብ እስካልተላቀቁ ድረስ ደግሞ መቼም ከስምምነት ላይ የማይደርሱ እንደሆነ ከኢትዮጵያና ከሱዳን የማያወለውል አቋም መገንዘብ ይቻላል።

በሁሉም የአባይ አጀንዳ ላይ ያረጀው የቅኝ ግዛት ውል ታሳቢ እንዲደረግላት በምትሻው ግብጽ ምክንያት ሦስቱ አገሮች በጋራ የቀጠሩት ‹‹ቢአርኤል›› የተሰኘው የፈረንሣይ ድርጅት የሚሠራበትን መመርያ ለማዘጋጀት በተደጋጋሚ ጊዜ የሦስቱ አገሮች የአጥኚዎች ቡድንና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እየተገናኙ ቢመክሩም፣ በመመርያው ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ያልተቻለ እንደሆነም ከውሃ መስኖና ኤሊክትሪክ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ፡፡ ሦስቱ አገሮች በአዲስ አበባ በቅርቡ አድርገውት በነበረው 16ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባም ግብፅ መመርያው በመዘግየቱ ቅሬታ ከማቅረብ ባሻገር፤ የዚሁ አካል በሆነው 17ኛው የካይሮ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1959 የነበራት የውኃ መብት እንዲጠበቅላትና የአጥኚ ቡድኑ የጥናት መመሪያ ይህን ከግምት ያስገባ እንዲሆን ሐሳብ ማቅረቧ አሁንም ክፍት እንዳልሆነች የሚያመላክት ነው።

ከናይል ውሃ 85 በመቶ አስተዋጽኦ ያላትን አገር ጠብታ ውሃ እንዳትነኪ ማለት ከሞራልም ሆነ ከሕግ አንፃር ተቀባይነት የለውም፤ የሞት ሽረት ጉዳይ ሊሆን የሚችልበትም አግባብ ተጠየቃዊ አይደለም። ምክንያታዊ የሚሆነው የመልማት መብታችንን ከመረዳት በዘለለ ተቀብሎ ስለጋራ ልማት በጋራ መስራት ነው። በተደጋጋሚ በተደረጉት እና በከሸፉት የሶስትዮሽ ድርድሮች ላይ ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር ያደረገችው የውሃ ስምምነት የተፅዕኖ ግምገማውና የሙሌትና የአለቃቀቅ ጥናቱ መነሻ እንዲሆን ብትጠይቅም፤ እ.ኤ.አ የ1929 እና የ1959 የውሃ ስምምነቶች ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ እንዳይኖራት ያደረገ በመሆኑ ለድርድር ይዞ መቅረብ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።  

የህዳሴ ግድባችን ግንባታ ከፊል ገፅታ

 

 

 

የተፈጥሮ ሀብታችንን ተጠቅመን ከድህነት መውጣት የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የማንንም ፈቃድ ልንጠብቅ እንደማይገባ ግልጽ ነው። የውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂያችንም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው። ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ያላትን ሀብትና ሰብዓዊ አቅም አስተባብራ ትጠቀማለች በሚል በፖሊሲያችን ላይ በግልጽ ተመልክቷል። ከእነዚህ ሀብቶቻችን አንዱ ደግሞ የዓባይ ውሃ ነው። ይህንን አትጠቀሙ ማለት ከድህነት ጋር ተቆራኝታችሁ ኑሩ ማለት ስለሚሆን ግብጽ  ለእድሜ ዘላለሙ ተቀባይነት በማይኖረው አቋም ላይ መጣበቋ ቢያከስራት እንጂ አትራፊ ልትሆንበት አትችልም።

በፖሊሲያችን ላይ የመልማት መብታችንን ለማስከበር ሲባል በሌሎች አገሮች ላይ ጉዳት እናደርሳለን ማለት እንዳልሆነ በግልጽ ተመልክቷል። ይልቁንም ከዚህ በፊት ሃገራችን ታደርገው እንደነበረው ወደፊትም ከአገሮች ጋር በትብብር መሥራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ምሰሶ እንደሆነ ተመልክቷል። በፖሊሲያችን ላይ ተመለከተም አልተመለከተም ዋናው እና ግብጽ ልትገነዘበው የሚገባት ጉዳይ ቢኖር ከተፋሰስ ሃገራቱ አንዱም እንኳ ተጎጂ ከሆነ ዘላቂ መፍትሔ እንደማይመጣ ነው። ከላይ በተመለከተው አግባብ ግብፅ አሁንም ድረስ ኢምክንያታዊ በሆነ መልክ የዓባይ ወንዝ የሞት ጉዳዬ ነው ብትልም፤ ምክንያታዊ ለሆነችው ሃገራችን ደግሞ ከድህነት ጋር አብሮ የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ መሆኑን የግዷንም ቢሆን ልትቀበል ይገባል።

ታላቁ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ረሃብን ለማጥፋት የምታከናውነው ፕሮጀክት እንጂ የየትኛውንም የጎረቤት ሃገር ወንድም ህዝብ ለመጉዳት የምታከናውነው እንዳልሆነ የግብጽ ህዝብ ተገንዝቦ እነዚህን ኢምክንያታዊ የሆኑ ተቋማትና ሚዲያዎች ሊያስታግስ ይገባል። ይልቁንም ለመላው ግብጻውያን ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በማስገንዘብ የፖለቲካ መቆመሪያ ያደረጉ ሃይሎችን ሃይ ሊሏቸው ይገባል።

የህዳሴ ግድቡ ለተፋሰሱ አገሮች ጭምር የሚጠቅም ፕሮጀክት ነው። ግድቡ ለግብፅ ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች መካከልም የአፈር ዝቅጠትን መከላከሉ፣ የውኃውን ፍሰት መቆጣጠሩ፣ ከድርቅና ከጎርፍ የታችኛውን የተፋሰስ አገሮች መጠበቁ፣ ውሃ ማከማቸቱ፣ እንዲሁም ኃይል ማመንጨቱና የመሳሰሉት  ተጠቃሾች ናቸው።

ከሃገራችን የሚነሳውና በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ ሜዲትራኒያን ባህርን መዳረሻው የሚያደርገው አባይ ለጐረቤት ሱዳን በርካታ ጠቀሜታዎችን በመስጠት ላይ ነው። በዋናነት ከሚጠቀሱት ጠቀሜታዎቹ መካከል የመብራት ኃይል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ከዋና ከተማዋ ካርቱም በስተሰሜን አቅጣጫ በ350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተገነባው ሜሮዌ ግድብ ለሱዳን ከአንድ ሺህ 250 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ያመነጫል። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2004 ግንባታው የተጀመረው ሜሮዌ ግድብ ከአምስት አመት የግንባታ ሂደት በኋላ በመጋቢት 3/2009 እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር መብራት ማመንጨት ጀምሯል። ከዚህ በተጨማሪ ሜሮዌ፣ ዳባ እና ዶንጐላ የተባሉትን ከተሞች በመብራት ኃይል በማስተሳሰርና ፖርት ሱዳንንም ተጠቃሚ ለማድረግ በረሐውን እና ወጣ ገባውን የሱዳን መልክዓ ምድር የሚያቋርጥ ተጨማሪ የአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከመስመር ዝርጋታው ባሻገር ካርቱም የብሔራዊ የኃይል ቋቷን ደረጃም የማሻሻል ስራ አከናውናለች።

የሱዳን መንግስት በአባይ/ናይል ወንዝ ላይ ያለውን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግም በ2010 እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 360 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚችል ስራ ጀምሯል። ከ705 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይደረግበታል ተብሎ ግንባታው የተጀመረውና አጅባር የሚል መጠሪያ የተሰጠው ግድብ ለሱዳን የኢንዱስትሪ እድገት የራሱን ሚና እንደሚጫወት የብዙዎቹ እምነት ነው። ሱዳን እነዚህን ሁለት ግድቦች በዋናነት ለኃይል ማመንጫ በማሰብ ትገንባቸው እንጂ በመስኖ ስራ ላይም ለሃገሪቱ አርሶ አደሮች ጠቀሜታቸው የጐላ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ ያስረዳል። በቀጣይም ሱዳን በግድቦቹ ላይ የማስፋፊያ ስራዎችን በመስራት በኃይልና በመስኖ ስራው እንዲሁም በቱሪዝሙ መስክ ከአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ ማሰቧን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

ናይልን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቀሙ ሃገራት ግብጽ ቀዳሚ ናት። ከላይ በተመለከተው እና ለዚህ ተረክ መነሻ በሆነን ሰሞንኛ ጉዳይም በቅኝ ገዥዎች የተፈረሙ ውሎችን በማጣቀስ የናይል ወንዝ “አዛዥና ናዛዥ እኔ ነኝ” ማለቷን ቀጥላበታለች። ይህን ታሳቢ በማድረግም በአባይ ወንዝ ላይ የአስዋን ግድብ እ.ኤ.አ በ1960 ጀምራ በ1970 ጥቅም ላይ ማዋል ችላለች። የአስዋን ግድብ 111 ሜትር ከፍታ እና 3 ነጥብ 83 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ግድቡ አስራ ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሲኖሩት እያንዳንዳቸውም 175 ኪሎ ዋት ከማመንጨታቸውም በላይ ግድቡ ግብጽ የነበረባትን የኃይል ችግር እንድትፈታ አስችሏታል። የአስዋን ግድብ ለግብጽ የኢንዱስትሪ እድገት ሁነኛ ሚና ከመጫወቱ በላይ የአባይ ወንዝን ጐርፍ በመከላከል የሃገሬው አርሶ አደሮች በአመት ሁለት ጊዜ ጉልህ ድርሻ ያበረክታል። በግብጽ ያሉ አርሶ አደሮች በላይኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ዝናብ በበዛበት ወቅት ሰብላቸው በጐርፍ ይወሰድ ነበር፤ ብዙም ዝናብ በማይኖርበት ወቅት ደግሞ የግብጽ አርሶ አደሮች የመስኖ ውሃ ማግኘት ይቸገሩ ነበር። የአስዋን ግድብ ግን ይህን ችግር መፍታት የቻለ ነው። የህዳሴው ግድብ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ፋይዳ ይኖረዋል።

 

ናይል ለግብጽ እና ለሱዳን ዜጐች እየሰጠ ያለው ጠቀሜታ በእጅጉ የጐላ ነው። የውሃው መገኛ የሆነችው ሃገራችንና ዜጐቿ ግን እስካሁን ያገኙት አንዳች ጥቅም የለም።  አንደኛ ደረጃ ባለቤት የሆነውን እኛን ለመንፈግ ሌት ተቀን የምትዳክረው ግብጽ  ሁለ መናዋ ከአባይ ጋር የተያያዘ መሆኑን ስናሰላ ደግሞ ሁኔታዋ ያሰቅቃል፤ ሰዋዊና ወንድማማቻዊም አይመስልም። ልማታቸው፣ ታሪካቸው  የቱሪስት መስህባቸውን  ሳይቀር ከአባይ ጋር ያቆራኘችው ግብጽ ባለቤት የሆነውን እኛ ጠብታ ለመንፈግ ስትዳክር ማየት በእርግጥም እንደምታወራው ውሃው ስለሚያንስባት ሳይሆን የምቀኝነት ዛር ነው፤ የክፉ ቅናት ደዌ። ይሁንና  እጅና እግሩን በጉባ መንደር ላይ ተክሎ እውቀትና ኪሱን በታላቁ ግንባታ ላይ እያርከፈከፈ የሚገኘው የኢትጵያ ህዝብ  እየፈጸመ ያለው ጀብድ የሚያኮራና ታላቅ ብቻ ሳይሆን በጨዋነት የታጀበ እና የታችኛው ተፋሰስ ሃገራትን ጠቀሜታም ታሳቢ ያደረገ ድል ነው።

 

ሃገራችን በአባይ ውሃ ብቻ ሳይሆን የትኛው የልማት እንቅስቃሴዋ ከሁሉም ጎረቤት አገራትም ሆነ ከሌሎች የዓለማችን አገራት ጋር  በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ  መርህ የሚመራ መሆኑን የሚያውቀው የግብጽ ህዝብ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ሙግት ከተቋማቱና ሚዲያው ጋር ሊገጥም ይገባል።  በተለይ የድንበር ወሰን ካላቸው እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ኤርትራ የመሳሰሉ አገራት ጋር ያለንን እና በፖሊሲና ስትራቴጂዎቻችን ላይ በጸናነው አግባብ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በመከተል ከሁሉም አጎራባች አገራት ጋር ያለንን  ግንኙነት በአስረጂነት ወስደው ሊሟገቱ ይገባል።  

 

  1. Abebe Tesfa says

    የአገራችን ሚዲያዎችም የዓባይን ወንዝ በተመለከተ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ግድቡ ለተፋሰሱ አገራት የሚሰጠዉን ጠቄሜታ በማጉላት መስራት አለባቸዉ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy