Artcles

የያዝነውን እንጠብቅ፤ ያቀድነውን እናሳካ

By Admin

December 27, 2017

የያዝነውን እንጠብቅ፤ ያቀድነውን እናሳካ

ብ. ነጋሽ

በመጪው ግንቦት“ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” ከሚል መፈክር ከተፋታን 27ኛ ዓመታችንን እንይዛለን። አሁን እድሜያቸው እስከ 35 ዓመት የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ይህን መፈክር አያውቁትም። “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” የሚለው ፉከራ ሰዉንም ወደጦር ግንባር ማጋዝን የሚመለከት ነበር። አርሶ አደሩ፣ ላብአደሩ፣ ወጣቱ ተማሪ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል አምባገነኑ ወታደራዊ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በየአቅጣጫው የከፈቱበትን የነጻነት ጦርነት ለመመከት በግዳጅ ለውትድርና አገልግሎት ይመለመሉ ነበር።

ወታደራዊው ደርግ 1980 ዓ.ም በሃገሪቱ ሁሉም አቅጣጫ የተከፈተበትን የነጻነት ጦርነት ለመመከት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሚወጣውን የሃብት መጠን፣ ሊያስገነባ ከሚችለው የባቡር ሃዲድ፣ ሆስፒታል፣ ወዘተ. ጋር እያነጻጸረ ተናግሮ ነበር። እንደመፍትሄ ያስቀመጠው ግን ያለ የሌለ ሃይሉን – የሰው ሃይል፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ፣ ወዘተ. ለጦርነቱ በመመደብ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የሚል ነበር። በዚህ መሰረት አዲስ የክተት አዋጅ ለፈፈ። በዚህ አዋጅ በጡረታ የተገለሉ የቀድሞ ወታደሮችና የአገልግለት ጊዜያቸውን ጨረሰው ተሰናብተው የነበሩ የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የሰጡ ወጣቶች ወደጦር ሜዳ እንዲዘምቱ ዳግም የግዳጅ ጥሪ ተላለፈላቸው። አርሶ አደሩ ከእርሻው፣ ላብ አደሩ ከፋብሪካው ተነቅሎ ወደጦር ሜዳ እንዲዘምት ተጠራ። ደርግ “ይለያል ዘንድሮ…” እያለ እያዘፈነ የሃገሪቱን አቅም በሙሉ በጦርነቱ ላይ አዋለ። ይሁን እንጂ፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሲያካሂዱት የነበረውን የነጻነት ትግል መግታት አልቻለም። እንዲያውም በድል ላይ ድል እየተቀዳጁ የነጻነቱን ወቅት አቃረቡት።

በእነዚህ ዓመታት በገጠር የእርሻ ስራ ላይ መሰማራት የሚችለው አብዛኛው ወጣትና ጎልማሳ አርሶ አደር ወደጦር ሜዳ ዘምቶ ስለነበረ ማሳዎች ጦም ያድሩ ነበር። በአርሶ አደር መንደሮች አቅመ ደካማ አዛውንት ብቻ ቀርተው፣ አስከሬን የሚሸከም፣ የመቃብር ጉድጓድ የሚቆፍር ጎበዝ ጠፍቶ ነበር። የአርሶ አደሩ መንደሮች ቀድሞ ከነበረውም የባሰ ድህነት የነገሰባቸው አስፈሪ ሆነው ነበር።

ወታደራዊው ደርግ ያልተገነዘበው ጦርነቱ የሚፈጀውን የገንዘብ ወጪና የሰው ሃይል ወደልማት አዙሮ ከሃገሪቱ አንድ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ የባቡር ሃዲድ መዘርጋት የሚቻለው፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ማስገንባት የሚቻለው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብረት እንዲያነሱ ያስገደዳቸውን ብሄራዊ ጭቆና በማንሳት ነጻነታቸውን በማረጋገጥ ብቻ ነበር። ደርግ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባይሆንም በመራራ ትግል ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው መብትና ነጻነታቸውን ለመቀዳጀት በቅተዋል፤ ግንቦት 1983 ዓ.ም፤

የግንቦት 1983 ዓ.ም ድል የብሄራዊ መብትና ነጻነት ማረጋገጥ ያስቻለ ታላቅ ፖለቲካዊ ድል የተገኘበት ነው። በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት የዜጎችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋጋር ያስቻለ ዕድልም ያስገኘ ድል ነው።

በቀደሙት አሃዳዊ ስርአቶች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦቸና ህዝቦች ማንነታቸውን እንደጠበቁ እንደ ኢትዮጵያዊ የመቆጠር እድል ተነፍገው ነበር። በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት፣ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ላይ በራሳቸው ቋንቋ የመሟገት፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማስተማር፣ እንደየባህላቸው የመኖር፣ እውነተኛ ታሪካቸውን ይፋ የማድረግ ወዘተ. መብት አልነበራቸውም። ልብ በሉ፣ እነዚህ መብቶች የማይገሰሱ የሰው ልጅ መብቶች ናቸው። እነዚህ የማይገሰሱ መብቶች ነበሩ በአዋጅ የተገፈፉት፤

አሁን ይህ ሁሉ ተቀይሯል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው። በሚኖሩበት ክልል በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት ያገኛሉ። ፍርድ ቤት ቆመው ጉዳያቸው ላይ በራሳቸው ቋንቋ ይሟገታሉ። ልጆቻቸው አካባቢያቸውን መረዳትና ራሳቸውን መግለጽ በሚችሉበት የአፍ መፈቻ ቋንቋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እየተሰጣቸው ነው። ባህላቸውን እያስተዋወቁና እያዳበሩ ነው። እውነተኛ ታሪካቸውን እያወጡ እያስተዋወቁ ይገኛሉ። በማንነታቸው የሚኮሩ ሆነዋል። ይህ ድል በእጅ ከገባ በኋላ ቀላል ይመስላል። ሲያጡት ግን ለመቀበል የሚከብድ መራር ነው። የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ እነዚህ መብቶችና ነጻነቶች ተሰርተው ነው የጠበቁት። ስለዚህ የነበረና ያለ ቀላል ነገር ሊመስለው ይችላል።

አሁን በሃገሪቱ የህይወት መስዋዕትነት የሚጠይቅ፣ ከስራና ከትምህርት ገበታ ተፈናቅሎ መዝመትን የግድ የሚል ጦርነት የለም። በመላ ሃገሪቱ ሰላም ሰፍኗል። የኢትዮጵያ አርሶ አደር አሁን ከእርሻ ሰራው ላይ በግዳጅ ወደጦር ሜዳ የሚያዘምተው የለም። ሙሉ ጊዜውን ስራው ላይ ያሳልፋል። ሰርቶ ባፈራው ሃብት ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት አለው። ይህ ብቻ አይደለም። መንግስት አርሶ አደሩ እድሜውን ሙሉ ተጭኖት ከኖረው ድህነት እንዲላቀቅ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ድጋፍ ያደረግለታል። ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያስችለውን የካፒታል እጥረት የሚያቃልል የገንዘብ ብድር ተመቻችቶለታል። የተሻለ የምርት ግብአትና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን የሞያና የአቅርቦት ድጋፍ ይደረግለታል።

ይህ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሻሻል ገቢውን አሳድጎለታል። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር እጅግ የተረጋጋና የተሻለ ህይወት እየመራ ነው። ድሮ ለከተሜዎች ብቻ የተፈቀዱ የሚመስሉትን የፍጆታ ሸቀጦች ተጠቃሚ መሆን ችሏል። የተሻለ የጸዳ መኖሪያ ቤት ባለቤት ሆኗል። በረቱንና የጢስ ቤቱን ከመኖሪያው ለይቷል። የኢትዮጵያ አርሶ አደር አሁን የተሟላ የስራ፣ የክትና የሌሊት ልብስ አለው። ሲገዛ የነበረው ጨርቅ ምን ይመስል እንደነበረ መለየት እስኪያዳግት ተጣጥፎ ከተደራረተ ቁምጣና ሸሚዝ ተላቅቋል። ለእግሩም ጫማና ካልሲ አለው። ለመኝታው አልጋ፣ ለማረፊያው ወንበርና ጠረጴዛ አለው። የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ነው። በርካታ አርሶ አደሮች በጸሃይ ሃይል በመታገዝ የምሽቱን ጨለማ በኤሌትሪክ ብርሃን ማሸነፍ ችለዋል። የቴፕሪከርደር፣ ቴሊቪዥንና መሰል የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ተጠቃሚ ለመሆን የበቁ አርሶ አደሮች ቁጥር ቀላል አይደለም። አሁን አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ምርቱን በማሽን ሰብስቦ ማስገባት እየተለማመደ ነው።

የኢትዮጵያ አርሶ አደር አሁን ልጆቹን ያስተምራል። የአርሶ አደሩ ልጆች እግር ሲያወጡ የከብት ጭራ ተከትለው ለእረኝነት የሚወጡበት ዘመን ታሪክ ሆኗል። አሁን ወደትምህርት ቤት ነው የሚሄዱት፤ በሃገሪቱ የተስፋፉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ የቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች የአርሶ አደሩን ልጆች መጻኢ የመማር እድል ሰፊ አድርገውታል። የአርሶ አደሩ ልጆች ባለተስፎች ለመሆን በቀተዋል። አርሶ አደሩ ሲታመም በቤቱ ተኝቶ፣ የመዳን እድሉን ለፈጣሪው ትቶ የሚጠባበቅበት ሁኔታ ተቀይሯል። በአቅራቢያው የህክምና ተቋማት ተገንብተዋል። ነፍሰ ጡሮች በሃኪም እርዳታ ነው የሚገላገሉት፤ በመሆኑም የእናቶችና የህጻናት ሞት በጉልህ ቀንሷል።

አርሶ አደሩ አሁን ለመንገድ ቅርብ ነው። ምርቱን ይዞ ገበያ ለመውጣት፣ ከተማ ለመሄድ አህያ ጭኖ በእግሩ መጓዝ አይጠበቅበትም። በመኪና ተሳፍሮ የመሄድ እድል አግኝቷል። እርግጥ የመንገድ ልማት በተለይ የገጠር መንገድ ልማት አሁንም ይቀረዋል።  

ሃገሪቱ ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በአማካይ ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ ችላለች። የሃገሪቱ የዘመናት ድህነት ጫናው ከባድ በመሆኑ ሃገሪቱ መድረስ ከሚገባት ጋር ሲነጻጻር ብዙ ቢቀራትም፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። ኦሮሚያን ብቻ እንደ ምሳሌ ብንወስድ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ 35 ሺህ ፋብሪካዎች ይገኛሉ። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ይህ አሃዝ በተጋነነ ግምት ከጥቂት መቶዎች አይበልጥም ነበር። የመሰረተ ልማትና የኮንስትራክሽን ዘርፉ በተለይ በከተሞች በሚያስደንቅ ፍጥነት እያደገ ነው። በአሁኑ ወቅት ሁሉም የሃገሪቱ ከተሞች የኮንስትራክሽን ዎርክ ሾፕ ነው የሚመስሉት። የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ዘርፎች፣ ከግብርና ዘርፍም በተለይ የአበባ እርሻ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር አስችለዋል። እርግጥ የስራ ፈላጊው ቁጥር አሁንም አልተቃለለም። በዚህ ላይ በዙ መሰራት አለበት።

እንግዲህ ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት እነዚህ ለማስታወስ ያህል በወፍ በረር እይታ የዘረዘርኳቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ተገኝተዋል። ይህ በገሃድ የሚታይ ተጨባጭ እውነታ ነው። አሁንም ግን ብዙ ይቀረናል። የእስከዛሬ ድንቅ ስኬቶች ቀሪዎቹን በማሳካት ሃገሪቱን የስልጣኔና የብልጽግና ማማ ላይ ማድረስ እንደሚቻል አረጋግጠዋል። አሁን በመንግስትና በህዝቡ ዘንድ የይቻላል ስሜት ተፈጥሯል።

ታዲያ! የእስከዛሬ ስኬቶችን እያጣጣሙ ቀጣዮቹን እያሳኩ የተሻለ የመኖር ተስፋ እውን ማድረግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። የሰላም መደፍረስ የያዝነውን ያስጥለናል፤ ተስፋ ያደረግነውን መና ያስቀረዋል። ይህን በተለያዩ ሃገራት በተጨባጭ አይተነዋል። የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የነበረችውና በርካታ ዜጎቿ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ደርሰው የነበሩባት ሶሪያ በሃገሪቱ በተፈጠረ ግጭት አሁን ውብ ከተሞቿ ወደ አሸዋና የድንጋይ ክምርነት ተቀይረው የስቃይ፤ የረሃብ፣ የበሽታ፣ የሞት ሃገር ሆናለች። የኢራቅም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ሊቢያ መንግስት አልባ የታጣቂዎች መፈንጫ ሃገር ሆናለች። በሊቢያ አሁን ኑሮ የለም። የመን በዘመናዊ የዓለማችን ታሪክ ታይቶ ባይታወቅ ዘግናኝ ረሃብና የኮሌራ በሽታ ዜጓቿ የሚሰቃዩባት ምድር ሆናለች።

ይህ አስከፊ እጣ በእጁ ያለውን ሰላም መጠበቅ ያልቻለ ህዝብ ባለበት በማንኛውም ሃገር ሊደርስ የሚችል ነው። የሰላም ባለቤት ህዝብ ነው። የሰላም ጠባቂም ህዝብ ነው። ህዝብ ያልጠበቀውን ሰላም ማንም ሊጠብቀው አይችልም። ሰለም አስከባሪ ሃይል፣ ሰላም ፈላጊና ሰላሙን ለመጠበቅ የተዘጋጀ ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው ስኬታማ የሚሆነው፤ ህዝብ መንግስት ላይ ቅሬታዎች ቢኖሩት እንኳን ችግሮቹ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱባቸውን አማራጮች ብቻ መከተል ይኖርበታል። እልህ አሰጨራሽም ቢሆን ይሄው አማራጭ ነው የሚሻለው፤ የሁከትና የግርግር አማራጭ በእጅ ያለን ያስጥላል፤ የነገን ተስፋ ያጨልማልና! እናም ሰላማችንን በማስከበረ የያዝነውን እንጠብቅ! ያቀድነውንም እናሳካ።