የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውና ፈተናዎቹ
አባ መላኩ
ኢትዮጵያ ባለፋት ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በመገንባት ድህነትን ለማሸነፍ ባደረገችው ጥረት አበረታች ሊባል የሚችል ውጤት አስመዝግባለች። ይህ የዓለም ህዝብ ሳይቀር ምስክርነቱን የሰጠበት እውነታ ነው። እንዲህም ሆኖ ልዩነታችን ውበታችንና አንድነታችን ሆኖ ካልቀጠለ፤ በመነቋቆርና በመነካከስ፣ በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ ከተዘፈቅን ግን ትተነው ያለፍነውን የድህነት ታሪክ መልሰን ልንጨብጥ መገደዳችን አይቀሬ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ ምርጫ ሳይሆን ወሣኝ የህልውና ጉዳይ ነው የሚባለው፡፡
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከዴሞክራሲ ባህል ግንባታና ከአገራዊ መግባባት አንጻር ተጨባጭ ሊባል የሚችል ለውጦችን አምጥቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ግንባታን እውን ማድረግ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም። ዴሞክራሲ በሌለበት ሁኔታ መቻቻልንና በጋራ ጉዳዩች ላይ መግባባትን መፍጠር አይቻልምና።
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በጋራ ጉዳዩች ዙሪያ ለአገራዊ መግባባት መሠረት ከመጣል ባለፈ በዋና ዋና ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠርና ሁለንተናዊ እድገታችን እንዲለወጥ አስችሏል። በተለይ ደግሞ በአንድ ተራማጅ ሥርዓት ውስጥ እውን መሆን ላለባቸው የዴሞክራሲና የአገራዊ መግባባት መሠረት ሆኖ አሁን ድረስ ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማጎልበት በርካታ ርምጃዎችን ወስዷል። እነዚህ ተግባራት የኢትዮጵያ ህዝቦች የሞት ሽረት ጉዳያቸው ነው የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ ህዝቦች በራሳቸው ይሁንታ ባፀደቁት ህገ መንግሥት ላይ በግልፅ የሰፈረው ቁምነገር የሚያስረዳውም ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በሌላ መንገድ እንደማይገኝ ነው።
በዚህም የፖለቲካ ፖርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ይህን ሀቅ ተገንዝበውና የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ የላቀ ነው።
የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ገና 26 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ለጋ እድሜ ያለው ነው። በመሆኑም የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ሥር እንዲሰድ ብርቱ ጥረት ሙሉ በሙሉ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም መሠረታዊ የዴሞክራሲ ተግባራትን በማከናወንና ዴሞክራሲው እንዲጎለብት ረጅም ርቀት ተጉዟል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ደግሞ ጊዜን ይጠይቃል። ሂደት ነውና።
የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ሊረጋገጥ የሚችለው በመጎልበት ላይ ያለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ያለ አንዳች መደነቃቀፍ ቀጥሎ መስመሩን ሲይዝ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ፖርቲዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መጠናከርና መጎልበት ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው አያከራክርም።
በአገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው መንግሥት በእምነት ይዟል። ዘወትር ተደጋግሞ ሲገለጽ እንደምንሰማው የመንግሥት ፍላጐት የአገሪቱ የመድብለ ፖርቲ ሥርዓት በልፅጎና አብቦ ማየት ነው፡፡ ለዚህም የአገሪቱ ዜጎችን የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው የሚሰማበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየጣረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደቱን ጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተፈጥረው ተሳትፏቸው እየጐለበተ ሲሄድ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጭፍን የጥላቻ አካሄድ ወጥተው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ማበብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የማበርከቱ ጉዳይ ቸል ሊባል አይገባውም።
በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚሻውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ሥርዓቶች ራሳቸውን ሾመው አሊያም በአምባገነንነት ሥልጣንን በጉልበት ይዘው የሚሄዱበት አሠራር ጊዜው አልፎበታል። ላይመለስ ታሪክ ሆኖ ርቆ ተቀብሯል። እናም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ለኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ የውዴታ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱ የሚጠይቀው ግዴታም ሆኗል፡፡
ይህ ሁኔታ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ሲፈጥር አይተናል። በመላ ዜጎች ይሁንታ አግኝቶ በ1987 ዓ.ም በፀደቀው ህገ መንግሥት ላይም በግልጽ ተቀምጧል። እንዲህ ይላል። “ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ” ማለት፣ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች፣ የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልከዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት የተከናወኑት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የማጎልበት ተግባር ሂደቱ አልጋ በአልጋ ነበር፤ ጥረቱም ሳንካ አልገጠመውም ማለት አይቻልም። ባለፉት ሥርዓቶች በነበሩት ውስብስብ የብሔር ጭቆናዎች የተነሳ ይህን አስተሳሰብ በቀላሉ ወደ ህዝብ ማስረፅ አስቸጋሪ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የኢትዮጵያን አንድነት በማጽናት ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ አድርጓል።
የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት አድርጎ የተገነባው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በአሁኑ ወቅት ፍሬ ማፍራት ችሏል፡፡ ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር አብሮ በሠላም የመኖርና ችግሮች ሲከሰቱም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ግንኙነት በመጎልበቱ ነው፡፡
ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል። በዚህም የተነሳ ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ግጭት ሲከሰት አልተስተዋለም። ለዚህም ምክንያቱት አለው። ዋናው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ጭምር ነው። ይሁንና አልፎ…አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦችን በጋራ የመዋጋትቱ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።
ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድናን መፍጠር ችሏል፡፡ የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰብ ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መደፈቃቸው የማይቀር ነው። እየሆነ ያለውም ይኸው። እየተሸነፉም ነው።
ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ለአገራዊ ሠላምና መግባባት በር ከፍቷል። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባ ቁም ነገር ቢኖር አገራዊ መግባባት ማለት በሁሉም ጉዳዩች ዙሪያ ሁሉም ዜጋ ሙሉ ለሙሉ አንድ ዓይነት አቅም ይዞ ይስማማል ማለት እንዳልሆነ ልብ እንበል። የተለያዩ እሳቤዎችን በሚያስተናግደው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ሁሉም ዜጋ አንድ ዓይነት አስተሳሰብና አመለካከት ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅምና።
አገራዊ መግባባት ሲባል ዜጎች ልማት፣ ሠላምና ዴሞክራሲን በመሳሰሉ ቁልፍ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ይፈጥራሉ። አብነት መጠቃቀስ ካስፈለገ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ ላይ ለአገሩ ልማት በቀናነትና በጤናማ አዕምሮ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከአብዛኛው ህዝብ ጋር መግባባት ላይ ይደርሳል። እነዚህን መሰሉ አጀንዳዎች ላይ አገራዊ መግባባቱ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን ጉዳይ በጥቅል ስናየው ሥርዓቱ ለዴሞክራሲና ለአገራዊ መግባባት መሠረት መጣሉን የሚያስገነዝበን ይሆናል።