Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጥልቅ ተሃድሶው ለውጥ ማሳያ

0 318

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጥልቅ ተሃድሶው ለውጥ ማሳያ

                                                        ደስታ ኃይሉ

በጥልቅ ተሃድሶው ለውጦች ተገኝተዋል። ተሃድሶው ሙሉ ለሙሉ የታለመለትን ግብ መትቷል ባይባልም፤ ከተካሄዱት የለውጥ ሂደቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ በመዋቅሮቹ ውስጥ እያካሄዳቸው ያሉትን መሰረታዊ ለውጥ ከማሳያዎች ውስጥ አንዱ ይመስለኛል። የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በጥልቅ ተሃድሶው የወሰዳቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ የአቋም መግለጫው ላይ ችግሮቹን ወደ ራሱ መመልከቱ ተገቢና ትክክል ነው። ሊያስመሰግነውም ይገባል።

እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ የድርጅቱን መግለጫ በመንተራስ፣ ለውጡን ከአገራዊ የተሃድሶ ሂደት አኳያ ለመመልከት እሞክራለሁ። ይህም ህዝብን ማዕከል በማድረግ የሚካሄድ ማንኛውም እንቅስቃሴ በለውጥ የሚታጀብ መሆኑንም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ይመስኛል።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ35 ቀናት ባደረገው ጉባኤ በትክክል ራሱን ፈትሿል። ተገቢ ነው የሚለውንም አቅጣጫ አስቀምጧል። በተለይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመገንባት፤ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መዋቅራዊ ለውጥ ከማረጋገጥ፣ የህዝባችንን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመመለስ አንፃር ያሉበትን መሰረታዊ ክፍተቶችንና አዲስቷን ፌዴራላዊት ዴሞክሰራሲያዊት ኢትዮጵያ ከመገንባት አኳያ የተጋረጡ አሳሳቢ አዝማሚያዎች በጥልቀት መገምገሙ ትክክለኛ ነው። ምክንያቱም ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ያለበትን ችግር ለመፍታት አመላካች ጥርጊያ መንገድ ይፈጥራል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ህወሓት የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በየደረሰበት የትግል ምዕራፍ ውስጥ ሁሉ የሚገጥሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በስከነ ሳይነሳዊ አመራር፣ በአባላቱና በህዝብ የተሟላ ተሳትፎ በአስተማማኝ ሁኔታ እየመከተ ለድል የበቃ ድርጅት በመሆኑ ራሱን ወደ ውስጥ በመመልከት ያደረገው ግምገማ ፋና ወጊ ተግባር ነው።

ድርጅቱ የህዝብን ፀረ ጭቆና፣ ፀረ ኋላ ቀርነትና ፀረ-ድህነት ትግል ለስኬት ለማብቃት የሚያስችሉ የጠራ መስመር፣ መስመሩን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ስትራተጂዎችና ስልቶችን እየቀየሰ ከኣንድ የትግል ምዕራፍ ወደ ሌላው የትግል ምዕራፍ መሸጋገር የሚችል በመሆኑ ባካሄደው ጥልቅ ግመገማ የችግሩ ባለቤት ራሱን አድርጎ በማስቀመጡ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል። ችግሮችን ውጫዊ በማድረግ አንዱ በሌላኛው ላይ ጣቱን መቀሰር እንደሌለበትም ግምገማው አስተማሪ ነው ማለት ይቻላል።

ለአስተማሪነቱ በመግለጫው ላይ የተጠቀሰውንና “…ድርጅቱ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ አስተማማኝ የሆነ፣ ፈተናዎች በገጠሙት ቁጥር ራሱን በሚገባ እየፈተሸና ወቅቱ የሚጠብቀውን፤ ማንኛውንም የእርምት እርምጃ እየወሰደ ጥንካሬዎቹን የሚያጎለብት ድክመቶቹ ያለ ምህረት በማስወገድ በመስዋእትነት የደመቀ ታሪክ መስራት የቻለ አመራር ባለቤት ነው” የሚለው ተጠቃሽ ነው። መታገልና ማታገል በህወሓት/ኢህዴግ ውስጥ የነበረና ይህንንም ማድረግ የሚችል አመራር ይዞ የመጣ በመሆኑ ስር ነቀል ለውጥ የሆነ ግምገማ ለማካሄዱ ምክንያት ይመስለኛል።

በትጥቅ ትግልም ወቅት ሆነ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴያዎች እጅግ የሚያኮራ ተግባራትን የፈፀመ ድርጅት ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ከችግር አዙሪት መውጣት አቅቶት የሚንገዳገድበትና ለህዝብ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት ላይ ሰፊ ድክመት እያሳየ የመጣበት ሁኔታ እንደተፈጠሩ የገለፀው ድርጅቱ ዛሬ ላይ የወሰዳቸው ለውጦች ይህንን ቸግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉት ናቸው።

ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ስትራቴጂካዊ አመራሩ እየተዳከመ ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመና፣ አመለካከትና አደረጃጀቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ፣ ህዝባዊነቱ እየቀነሰ፣ የህዝብን ችግር በማያወለዳ መልኩ ሳይፈታ በትንንሽ ድሎች የሚረካ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ እንዳደረ የገለፀው የድርጅቱ መግለጫ፤ አሁን ያለበትን ቁመና ይዞ  የመጣበትን መስመርና የመለስን ሌጋሲ ማስቀጠል እንደማይችል አስረድቷል።

በእኔ እምነት እንዲህ ያለው ራስን በጥልቀት በመፈተሽ ችግሮችን ነቅሶ የማውጣት ተግባር የመፍትሔው ግማሽ ነው። የመፍትሔውን ግማሽ ያህል መራመድ የቻለ ድርጅት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ያሉበትን ችግር መቅረፉ አጠያያቂ አይሆንም። ምክንያቱም ያካሄደው ግምገማ በቁጭት መንፈስ የመጣበትን ትክክለኛ መስመር አጠናክሮ ለመጓዝ ያለመ ስለሆነ ነው።

እርግጥ ድርጅቱ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጥሞና መርምሮ ድርጅቱን በማያዳግም ሁኔታ ወደ ትክክለኛው መስመሩና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ለመመለስ በሚያስችለው መልኩ ራሱን በጥልቀት መፈተሹ ግልፅ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሲደረጉ ከነበሩት የይስሙላ ግምገማዎች በዓይነቱና መልኩ በተለየ ችግሮቹን በሚገባ ለመለየት ያስቻሉት መተጋገል ማካሄዱን አስታውቋል።

እናም ከተለመደው ግምገማ ለመውጣት ያስችላል ተብሎ የታመነበትና ስፋትና ጥልቀት ያለው ክርክር የጋበዘ የድርጅቱን አጠቃላይ ሁኔታና የአመራሩን ድክመት በሚገባ የፈተሸ ሰነድ ለአመራሩ ቀርቦ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎበታል። መደምደሚያውም በዋናነት ስትራቴጂክ አመራሩ ከገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቅቶት ሲዳክር በመቆየቱ መሆኑን ተገንዝቧል። ይህም የድርጅቱ ግምገማ የሰላና የስትራቴጂክ አመራሩን ድክመቶች አንጥሮ ያስቀመጠ ነው።

ይህም አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙሪያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርንና ጥቅም የሚያስቀድም እንዲያይ ያደረገው ነው። ድርጅቱ በስትራቴጂክ አመራሩ ላይ ያየው ድክመት በዚህ ብቻ አላበቃም።

አመራሩ ለህዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከአገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ፤ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ መምጣቱን በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል። የተፅኖዎችን ደረጃም በማስቀመጥ ከእንግዲህ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የመስጠት፣ የነበረውን የመተጋገል መንፈስ በማስቀጠል ህዝባዊነቱን እንደሚያስመሰክር ግልፅ አድርጓል።

በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ ግምገማ ለሌሎች እህት ድርጅቶችና አጋር ፓርቲዎች ምሳሌ ሊሆን የሚገባው ነው። ኢህአዴግም እንደ ኢህአዴግ ራሱን ከዚህ መነፅር አኳያ እንዲፈትሽ ሊያደርገው ይችላል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ መቅደም ያለበት ዋነኛው ጉዳይ ህዝባዊነት መንፈስ የመተጋገል ነባር ባህልን አጠናክሮ መውጣት ስለሚያስፈልግ ነው። በመሆኑም ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ ግምገማ አገራችን የምታካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ ለውጥ አንድ ማሳያ ተገርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy