Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጥልቅ ተሃድሶው መነሻና መድረሻ

0 244

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጥልቅ ተሃድሶው መነሻና መድረሻ

ወንድይራድ ኃብተየስ

በኢሕአዴግና በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ሥር እየሰደደ የመጣ ጉዳይ ነው – ጥልቅ ተሃድሶ። በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ድርጅቶችና የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደሚፈታ በእምነት ተይዟል። የተሃድሶው ሂደት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ተቋማት የህዝቡን ጥያቄ በሚመልሱ ደረጃ እየተቃኙ ይገኛል።

ይህ ጉዳይ ቀደም ሲል በነበሩ የተሃድሶ ሂደቶች የተከናወኑ ሥራዎችን የሚያጎለብት፣ የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው። ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በጽናት ለያዙት አቋም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አጋርነቱን ሊያሳይ ይገባል።

ኢሕአዴግና መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ ርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። እስካሁን ባለው ሂደት በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የመልካም አስተዳደር ህፀፆችን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። በተለያዩ ጊዜያቶች  በኦሕዴድ፣ በብአዴን፣ በህወሓት፣ በደኢሕዴን ድርጅቶች ብሎም በክልላዊ መንግሥታት ውስጥ የተከናወኑ ጥልቅ ተሃድሶዎች ይጠቀሳሉ። በእነዚህ የጥልቅ ተሃድሶ ሥራዎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች ተወስደዋል። አጥጋቢ ውጤቶችም ታይተዋል።

መንግሥት ከህዝቡ ጋር ሆኖ ባካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበሩና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ብልሹ አሠራሮች መሻሻል እያሳዩ ነው። ምንም እንኳን ገና ብዙ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም።  

በተለይ የሥልጣን መቀመጫን ለግል ጥቅም የማዋል ፍላጎትንና ተግባርን በመለየት ብሎም መረጃ የተገኘባቸውን ህግ ፊት ማቅረብ ተጀምሯል። ጥልቅ ተሃድሶው ገና ቀሪ ተግባራት ቢኖሩትም እስካሁን የተገኙት ውጤቶች ብዙ ሊያሰራ እንደሚችል አመላካች ሁኔታዎች አሉ። ይህ ሁኔታ ወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።  

ጥልቅ ተሃድሶው ለአገሪቱ በጎ ሊባል የሚችል ውጤት አስገኝቷል። ጥልቅ ተሃድሶ በተካሄደባቸው መድረኮች ሃሳቦች በግልጽነትና በነፃነት ተንሸራሽረዋል። ፐብሊክ ሰርቫንቱም ይሁን ህዝቡ ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለይተው አቅርበዋል።

የአገሪቱ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ እየተካሄዱ ባሉ የውይይትና የግምገማ መድረኮች የመንግሥትን ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው አንስቶ ለህግ አቅርቧል። በየመድረኮቹ የታዩ ሹም ሽሮችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ይህም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመታደስ ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት እያመጣ መሆኑን አመላካች ነው። ጥልቅ ተሃድሶው ዋጋ ያለውና የአገሪቱን ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚቻል ጠቋሚ ነው።

መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ውስጥ ራሱንና አሠራሮቹን ሲፈትሽ ዋነኛው ጉዳይ አድርጎ የተነሳው ሥር ነቀል ለውጥን ማዕከል በማድረግ ነው። ይህም ለይስሙላ የሚደረግ አሊያም ያለውን ችግር ሸፋፍኖ ለማለፍ እድል አይሰጥም። መንግሥት በየደረጃው ከህዝቡ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ያደረጋቸው የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎችን የመታገል ተግባሮች ለዚህ ሀሳብ ማረጋገጫ ይሆናል።  

በየደረጃው የተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ መንግሥትንና ህዝብን በቀጥታ ፊት ለፊት የሚያገናኝ ነው። ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮች በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ በግልፅ ተፈትሸዋል፤ ታይተዋልም። የችግሮቹ መሠረታዊ መንስዔዎች ተለይተው ታውቀዋል።  የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት አሁንም ጥልቅ ተሃድሶው ሳይስተጓጎል ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ መዝለቅ ይኖርበታል።  

የመንግሥት አሠራር ለህዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ለህዝብ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ህዝቡም በማንኛውም ጊዜ ተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ በማንኛውም ወቅት ከቦታው የማንሳት መብት እንዳለው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ይደነግጋል – የህዝብ የሥልጣን ሉዓላዊነት መከበር ለድርድር አይቀርብምና። ህዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት በመሆኑ የተነሳም ወደሥልጣን የሚያወጣና ከሥልጣን የሚያወርድ እርሱ ነው። ሥልጣን የሚመነጨው ከህዝብ እንጂ ከማንም አይደለምና። ማንኛውም ተሿሚ በህዝብ ይሁንታ ሥልጣን ላይ የሚቀመጥና ሲያጠፋም የሚነሳ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ተሿሚው በራሱ ፈቃድ ሳይሆን የህዝብ ይሁንታን ሲያገኝ ነው ሥልጣን ላይ የሚቀመጠው። ጥሩ ሲሰራ ተመስግኖ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት፣ ሲዳከም ጉድለቱን እንዲያርም አቅጣጫ የሚሰጠው ህዝብ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥር፣ በአደባባይ ምዝበራ ውስጥ ተዘፍቆ ሲገኝ ህዝብ ይቀጣዋል። ካለበት ቦታም ያነሳዋል። አዛዥ ህዝብ እንጂ ባለሥልጣን አይደለም፤ አይሆንምም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ተቀይሯል።  

በዛሬዋ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ያላመነበትና ያልመከረበት ነገር አይከናወንም። የፀረ ሙስናው ትግል በጥልቅ ተሃድሶው ጅማሮ ወቅት መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚዋጋ የገባው ቃል ዋነኛ ማሣያ ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነጥብ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድፈቅና መናድ አይቻል ይሆናል። ይሁንና ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነቱን እንዳይዝ ሁሌም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ኪራይ ሰብሳቢነት በገነነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ልማታዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብን መገንባት ያዳግታል። በዋናነትም ኪራይ ሰብሳቢነት ማነቆ ይሆናል።

ጥልቅ ተሃድሶው እስካሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውጤት አምጥቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል። በተለይም ከነጉድለቱም ቢሆን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በኩል ተገቢ ሊባል የሚያስችል ተግባር ተፈፅሟል። በጥልቅ ተሃድሶው የኢሕአዴግ ድርጅቶች ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጥ በማየት ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያሳዩትን ቁርጠኝነት እዚህ ላይ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል። በተለይ በቅርቡ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ ያደረገውን ግምገማ እዚህ ላይ ዋቢ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

አሁን በዚያን ሰሞን ህወሓት ከወር በላይ ያካሄደውን ጥልቅ ገምገማ ሲያጠናቅቅ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነበር። ድርጅቱ ፈተናዎች በገጠሙት ቁጥር ራሱን በሚገባ እየፈተሸና ወቅቱ የሚጠይቀውን ማንኛውንም የእርምት ርምጃ ይወስዳል። ጥንካሬዎቹን በማጎልበትና በድክመቶቹ ላይ የፀና አቋም በመያዝ ይታገላል። ይህም የቆየ የድርጅቱ ታሪክ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ድርጅቱ ለግምገማ ሲቀመጥ በሥራ ላይ ያለውና ተተኪው አመራር በጋራ ትኩረት ሰጥቶ ያየው ጉዳይ ከገባበት የአመራር አዙሪት ውስጥ ለመውጣት በተለመደው መንገድ መጓዝ በፍፁም እንደማያዋጣ ነው። ከተለመደው የግምገማ ሂደት በተለየ ስፋትና ጥልቀት ያለው ክርክርን የፈጠረ የድርጅቱን አጠቃላይ ሁኔታና የአመራሩን ድክመት በሚገባ የፈተሻ ሰነድ ለአመራሩ ቀርቦ ተመክሮበታል።

ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶችና ሌሎችም የሙያ የማህበራትና መሰል ኣደረጃጀቶች የለውጥ ባለቤት ሆነው የሚውጡበትን ዕድል በማምከን ድርጅቱን በቀጣይነት የሚመራ ብቁ ኃይል እንዳይፈጠር እንቅፋት የሆነ አመራር እንደነበር በመግለጫው ላይ ተወስቷል። ይህም ሁኔታ ህዝቡ በድርጅቱ ላይ የነበረው እምነት እንዲቀዛቀዝ አስተዋፅኦ ማድረጉም ተጠቁሟል። በአመራሩ ዘንድ የታየው ድክመት በከተማም ሆነ በገጠር የተጀመሩ ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት የማረጋገጥ ሥራዎችን ለአደጋ ማጋለጡን በመጠቆም ጭምር።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy