Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴራላዊ ስርዓቱን ውጤቶች በወፍ በረር ዕይታ

0 351

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራላዊ ስርዓቱን ውጤቶች በወፍ በረር ዕይታ

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን በመከተሏ ዓለምን ያስደመመ ፈጣን ዕድገት ባለቤት የሆነች፣ ድህነትን ከ54 ከመቶ ወደ 22 ከመቶ የቀነሰች፣ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች እያሳካች ያለችና የአፍሪካ የኃይል ምንጭ በመሆን ላይ የምትገኝ ባለተስፋ ሀገር ነች። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ማድረግ የቻለች፣ ለመላው ህዝቦቿ የጤና ሽፋንን በተገቢው መንገድ ለማዳረስ እየጣረች የምትገኝ ሀገር ናት።

ታዲያ የእነዚህና የሌሎች እመርታዎቻችን ድምር ውጤት ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገው ጉዞ አመላካቾች መሆናቸውን ማንም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ለውጤቶቹ መገኘት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደውም ሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓትን የመከተሏ ምስጢር መሆኑ ግልፅ ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓትን ባትከተል ኖሮ፤ እንኳንስ እነዚህ ሀገራዊ ለውጦች ሊመጡ ቀርቶ ዛሬም የድህነት ተምሳሌትነታችን በቀዳሚነት በተጠቀሰ ነበር።

ይህ ግን አልሆነም። ምስጋና ስርዓቱን ለማምጣት ውድ ህይወታቸውንና አካላቸውን መስዋዕት ላደረጉት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይግባቸውና ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር፣ የልማት ተምሳሌትና ስር የሚሰድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለቤት ሆናለች።

ከሰላም አኳያ በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ፈፌዴራላዊ ስርዓት ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ፤ በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፌዴራሊዝም የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም እንዲችሉ አድርጓቸዋል።  

እናም ስርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል። ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩት ሁከትና ግጭቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ይመስሉኛል።

ያም ሆኖ ህዝቡ በሰላሙ ላይ ስለማይደራደር ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር እንዳይኖር አድርጓል። ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሆነው ቢገኙም፤ ህዝብና መንግስት በጋራ በመሆን እነዚህ ሃይሎች ላይ ጥብቅ ርምጃ እየወሰዱ ነው። ፀረ ሰላምነት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንደሌለው በማያሻማ ሁኔታ እየገለፁ ነው።

ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ከራሳቸው አልፎ የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር ሆነዋል። እንደሚታወቀው የሀገራችን የዕድገት ተስፋ ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ብቻ ነው። ይህን ዕውነታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለዘመናት የህዝባችንን አንገት ያሰደፋውን ድህነት አሸንፈን ለድል ለመብቃት እየተደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ሊሆን የሚችለው የአካባቢያችን ያለመረጋጋት ችግር አንዱ መሆኑን ኢትዮጵያዊያን ይገነዘባሉ።

ለዚህ ደግሞ ከአካባቢያችን ሀገራት የሚመነጨው የሽብርተኝነት አደጋንና የእርስ በርስ ጦርነትን አደጋዎች መሆናቸውን ይረዳሉ። ርግጥም እነዚህ አደጋዎች ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍለ አህጉሩ አካባቢ ለሚገኙ እንዲሁም ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምን ያህል አስጊና አስከፊ መሆናቸው ግልፅ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን አካባቢያቸውን ሁኔታ ምን ጊዜም በትኩረት በመከታተል በአንድ በኩል በጎ ተፅዕኖዎችን ለማስፋፋትና ለማጎልበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ ጎጂ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዞ መረባረቡ የአማራጮች ሁሉ አማራጭ መሆኑን በሚገባ ያውቃሉ።

ሰላምን በቀጣናው ማስፈን ወደር የማይገኝለት ተግባር በመሆኑ በተለያዩ ወቅቶች ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻቸው ሰላም ጠባቂ ሆነው ተሰማርተናል። ትናንት በሩዋንዳና በብሩንዲ እንዲሁም በላይቤሪያ፤ ዛሬ ደግሞ በሱዳን ዳርፉርና በአብዬ ግዛት እንዲሁም በሶማሊያ ውስጥ እያከናወኑ ያሉት የሰላም ጠባቂነት ተግባራቸው ተጠቃሾች ናቸው። ይህም ፌዴራላዊ ስርዓቱ ከራሳቸው አልፈው ለአፍሪካዊያንና ለቀጣናው ወንደሞቻቸው ሰላምና መረጋጋት እንዲተርፉ ያደረጋቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያዊያን የአፍሪካ የልማት ተምሳሌቶችም ናቸው። ከአንዴም ሁለቴ በቀየሱት የልማት ዕቅዶች ተጠቃሚ ሆነዋል። እየሆኑም ነው። ዛሬ ሶስተኛ ዓመቱን በያዘው በሁለተኛው የልማት ዕቅድ የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ተደርጎ ውጤት ተገኝቶበታል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። እስካሁን ድረስ ያለው የዕቅዱ አፈፃፀም የሚያመላክተው ከወዲሁ እመርታዎች እየተገኙ መሆናቸውን ነው።

መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ እየተገኘ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል። ይህም የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዋልታ የሆነው የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሪ እንዲሆን አስችሎታል።

ኢንዱስትሪው ዘርፍ በቀጣይ የመሪነት ሚናውን ከግብርናው እንዲረከብና ሀገሪቱም የአፍሪካ የኢንዱስትሪ የስበት ማዕከል እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በተለይም በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ እየተካሄደ ነው። በዚህም የውጭ ኢንቨቬስተሮችን በስፋት በመሳብ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማዳበር ጥረት ተደርጎ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ነው።

የኢንዱስትሪ መንደሮችን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በመገንባት ስራ ፈጠራና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። አርሶ አደሮች ከመደበኛ የግብርና ስራቸው በተጓዳኝ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው መስራት መጀመራቸው እዚያው ሳለ ገቢን ከማዳበር ባባሻገር ግብርናውን ለማዘመን አቅም የሚፈጥር ሆኗል። እነዚህ ክስተቶች እየተከናወነኑ ያሉት ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠውን ፌዴራሊዝም በመከተሏ መሆኑን ብዙም ርቆ መመራመር የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም።

ኢትይጵያዊያን በሚከተሉት ፌዴራላዊ ስርዓት ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣምነናበአሁኑ ወቅት ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲ ባለቤቶች ሆነዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ዴሞክራሲ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዕውን እንዲሆኑም ብዙ ርቀት መጓዝ ችላለች። በተለይም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 31 ላይ፤ “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት አለው።…” በሚል በተደነገገው መሰረት፣ ማንኛውም ዜጋ ባሻው ማህበር ወይም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታቅፎ መንቀሳቀስ እንዲችል በመደረጉ ሀገራዊ ዴሞክራሲው በተሻለ ሁኔታ እንዲሰፋ ተደርጓል። በዚህም ለዴሞክራሲው መጎልበት ወሳኝ ሚና ያላቸው በርካታ ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን እያከናውኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

የመደራጀት መብቱን ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። በዚህም ባለፉት ዓመታት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎችና በርካታ የአካባቢና የማሟያ ምርጫዎች ተካሂደዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ‘ቁጥሩ ይነስ እንጂ ተቃዋሚዎችን የመረጠ የሀገራችን ህዝብ በመኖሩና የዚህ ህዝብ ድምፅ መሰማት ስላለበትም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር አካሂዳለሁ’ በማለት ድርድር እያካሄደ ነው። በዚህ ድርድርም የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ይበልጥ ጥረት እያደረገ ነው።

ይህም የሀገራችን ዴሞክራሲ ስር እየሰደደና እየጎለበተ መሄዱን የሚያሳይ ነው። ታዲያ ከ26 ዓመት በፊት በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ትታወቅ የነበረችው ሀገራችን ዛሬ ዴሞክራሲን እንደ ህልውና ጉዳይ ይዛ መንቀሳቀሷ ምስጢሩ ምንም አይደለም— ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት እንጂ። ያም ሆኖ በዚህ አጭር ፅሐሁፍ የፌዴራል ስርዓቱን ውሬቶች ተንትኖ መዝለቅ አይቻልም። እኔ የተመለከትኩት ወፍ በረር ቅኝት ግን ይህን ይመስላል። ቸር ያሰንብተን።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy