Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልተዘጋው የስደት በር

0 640

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያልተዘጋው የስደት በር

                                                    ታዬ ከበደ

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሊቢያው የባሪያ ንግድ ላይ ተመርኩዘው የሚያቀርቡት ዘገባ ህገ  ወጥ ስደት ምን ያህል ዘግናኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ከሊቢያው የባሪያ ንግድ ለማምለጥ የሚሞክሩ ህገ ወጥ ስደተኞች የሚያጋጥማቸው ነገር ሞት አሊያም የከፋ ጉዳት መሆኑን መመልከት ደግሞ በእጅጉ የሚያሳምም ጉዳይ ነው።

በአገራችን ውስጥ ምንም እንኳን መንግስት ህገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ከፍተኛ ስራዎችን ቢያከናውንም፤ ችግሩ ግን አሁንም መቀረፍ አልቻለም። የስደት በር በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት እንዲሁም በወላጆች የተሳሳተ ግንዛቤ ሳቢያ ሊዘጋ አልቻለም።

እናም ህብረተሰቡ ተግባሩን በማውገዝና የልጆቹ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በማሳየት ይህን የስደት በር በጋራ ለመዝጋት መሞከር ያለበት ይመስለኛል። ለዚህም እዚህ አገር ውስጥ ያሉትን መልካም ጅምሮችን ማሳየት ይገባል።

ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡

በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው።

እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም። በዚህ የኢኮኖሚ ስራ ውስጥ ገብቶ እንደሌሎቹ ወገኖች ራስን መቀየር እየታቻለ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ ተገቢ አይደለም። በተለይም በጉዳዩ ላይ ተሳታፈ የሆኑት ወጣቶች ስለ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። የግንዛቤ ማስጨበጫዎቹም በእነርሱ ላይ ማተኮር አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ ወጥ ደላሎች ግንኙነት እንደ ሰንሰለት በተያያዘ ሰንሰለት የተቆራኘ ነው። ይሁንና በዚህ አነስተኛ ፅሑፍ ላይ ከህገ ወጥ ደላሎቹ ማንነት፣ አሰራራቸውና በዝውውሩ ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አኳያ አዘዋዋሪዎቹን የአካባቢ፣ ድንበር አሻጋሪ፣ ጉዞ አቀላጣፊ፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በመዳረሻ ሀገራት የሚገኙ ደላሎች በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን።

የአካባቢ ደላሎች በሚገኙባቸው ቦታዎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ።

ድንበር አሻጋሪዎቹም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ በኮንትሮባንድ ነጋዴነት የሚፈረጁ ናቸው። እነዚህኛዎቹ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች የማስተላለፍ ስራዎችን ይተገብራሉ።

ጉዞ አቀላጣፊዎቹም ቢሆኑ መቀመጫቸውን ትላልቅ ከተማዎች ላይ በማድረግ ወደ መዳረሻ ቦታዎቹ የሚደረገውን ጉዞና የቅጥር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ሲሆን፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ዘመድና ጎረቤቶች እናግዛለን በማለት እነርሱ ወደ ነበሩበት ሀገር ሄደው እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በመደበኛነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

የእነዚህ ከስደት ተመላሽ ዜጎች እንቅስቃሴ በቤተሰባቸውም ይደገፋል። ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው ውጪ ሀገር ሄደው የሚያመጡት ገንዘብ በምን ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ከስደት የተመለሱት ልጆቻቸው ያስገኙላቸውን ጠቀሜታዎች በመዘርዘር የህገ ወጥ ስደቱ ሂደት ተካፋይ ይሆናሉ። ይህን የህገ ወጥ ስደቱ ተጠቂዎች መገንዘብ አለባቸው።

እርግጥ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘና በተግባር እየተከናወነ ያለ ጉዳይ ነው። እናም እዚህ ላይ ዜጎች ለምን ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ይሁንና ሰዎች በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ ሀገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት የተሻለ ስራ ፍለጋና ህይወት ወይም ልክ ወንድም እንደሆነው የኤርትራ ህዝብ ከጭቆና ለመሸሽ አሊያም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሊሆን ይችላል።

ዛሬ ላይ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠና እና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሃብት የማፈላለግ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል።

ለህገ ወጥ ስደቱ ተጠያቂዎቹ ቤተሰብ፣ ደላሎችና ሌሎች ወገኖች ብቻ ሊሆኑ አይችሉም። አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው የመንግስት ስራ የሚከውኑ ግለሰቦችም በሂደቱ ውስጥ ሊኖሩበት ይችላሉ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች በተለያዩ ወቅቶች እንደሚገልፁት ከሆነ፤ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የድለላ ስራ ውስጥ ለወገኖቻቸው ደንታ የሌላቸው አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች ይሳተፋሉ። በዚህም ሳቢያ ዝውውሩን ለመግታት በሚደረጉ ስራዎች ላይ ደንቃራ እየሆኑ ነው።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል ያለው ቁርጠኝነት በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየተደረገ ባለው አጠቃላይ ክትትልና እርምጃ ሁኔታው ወደ መሻሻል ያዘነበለ ቢሆንም፤ የግለሰቦቹን ተግባር በተገቢ ሁኔታ ለማረም ህብረተሰቡና መንግስት ተቀናጀተው መስራት ይገባቸዋል።     

እርግጥ በመንግስት በኩል ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመፍታት የፖሊሲ፣ የፕሮግራምና የህግ ማዕቀፎች ተበጅተው ሰፊ ርብርብ ተደርጓል፤ በመደረግም ላይ ይገኛል። ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ኃይል ከማቋቋም አንስቶ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እስከመስጠት ድረስ ያሉት ጥረቶች የሚያበረታቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ጥረቶቹ ህዝብን ባማከሉና ወደ መሬት ወርደው ገቢራዊ በሚሆኑ አሰራሮች ይበልጥ ሊደገፉና የችግሩን አስኳል ለይተው ሊያወጡ በሚችሉበት ሁኔታ መቃኘት ይገባቸዋል። ይህ ሲሆንም ያልተዘጋውን የስደት በር አጥብቆ መከርቸም የሚቻል ይመስለኛል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy