Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞራሲያዊ አንድነታችንን የሚያጠናክር ዕለት

0 266

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞራሲያዊ አንድነታችንን የሚያጠናክር ዕለት

                                                  ዘአማን በላይ

12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአፋር ሰመራ ከተማ በከፍተኛ ድምቀት ሊከበር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውታል፤ ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም። ዕለቱ የህዝቦችን የአንድነት መንፈስ የሚያጠናክር፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እንዲሁም አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት የራሱ ድርሻ ያለው ነው።

እንዲሁም ዕለቱ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ የበኩሉን ድርሻ ሊጫወት ይችላል። ዜጎች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱና ለፌዴራላዊ ስርዓቱ መጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያግዝም ነው። ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ አንድነታቸውን የሚያረጋግጡበት መድረክም ይሆናል። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዕለቱ የበቁት ያለፉትን ስርዓቶች ለመጣል ባደረጉት እልህ አስጨራሽና መራር ትግል መሆኑን በፅኑ አምናለሁ።

ትናንትን ከዛሬ ነጥሎ መመልከት እንደማይቻልም እገነዘባለሁ። እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ በቀዳሚነት ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች አስከፊዎቹን ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ለመጣል ያደረጉት ጥረትን በጨረፍታ በመመልከት፤ ህዝቦች ራሳቸው ይሁንታ የገነቡት ፌዴራላዊ ስርዓትን በያዝነው ወር ህዳር 29 ቀን ሲያከብሩ ዕለቱ ጠንካራ አንድነታቸውን ከማንፀባረቅ አኳያ ጥሩ መድረክ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ።

ርግጥ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ወክለው የመጡ አንግዶች  በአንድ ላይ ሲደሰቱ፣ ባህላቸውንና ትውፊታቸውን ሲያስተዋውቁ መመልከት ኩራትን ያጭራል። በጋምቤላ የነበረው ድባብ ህብረ-ብሔራዊነትን፣አንድነትንና መፈቃቀድን የሚያበስር ነው። ስለተለያዩ ባህሎች ይበልጥ ለመገንዘብ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡

የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ ከግብ ለማድረስ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ቃል ኪዳናቸውን ያደሱበት ታሪካዊ መድረክ ሆኗል። ርግጥ መሪ ቃልም ገቢራዊ እንደሚሆን ህዝቦች ከገቡት ቃል ኪዳን ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። እዚህ ላይ የሀገራችን ህዝቦች ለዛሬ ላይ የበቁት ምን ያህል መራር ሂደቶችን አልፈው ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት በጫንቃቸው ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን ዘውዳዊ የጭቆናና የአፈና ሥርዓት በቃን ብለው በየካቲት 1966 ሕዝባዊ ዓመጽ ለማስወገድ ታግለዋል። ግና  ከአፄው አስከፊ ስርዓት በከፋ ሃገሪቷን ለጦርነትና ለድህነት የዳረገው የደርግ አገዛዝ በጠመንጃ አፈሙዝ በትረ ስልጣኑን ለመያዝ ችሏል። ምንም እንኳን ደርግ በትረ ስልጣኑን ሲይዝ ስልጣን ለሰፊው ህዝብ የማስረከብ የይስሙላ ቃል ቢገባም ቃሉን ገቢራዊ አለማድረጉን ስልጣን በያዘ ማግሥት በሚፈፅማቸው አምባገነናዊ ድርጊቶቹ አረጋገጠ።

 

የህዝቦችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚደፈጥጥ አዋጆችን በማውጣት የስራ ማቆም አድማ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመናገርና የመፃፍ መብቶች አገደ፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩም ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚታገሉ ዜጐችን በግፍ መጨፍጨፉን በይፋ ተያያዘው። ይህ አስከፊ በደልና ጭቆና ያንገሸገሻቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአነስተኛ የሰው ኃይልና ትጥቅ ትግል በጀመሩ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ግንባር ቀደም መሪነትና መስዋዕትነት ጨፍጫፊውን ሥርዓት አምረው መታገል ጀመሩ።

 

እንኳንስ በተደራጀ ፖለቲካዊ አመራር ይቅርና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች በጭሰኝነትና ፊውዳላዊ በሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት የበላይነት በተረጋገጠበትና ከፍተኛ ጭቆናና ምዝበራ በሚደርስባቸው ወቅት እንኳን ግፉንና ጭቆናውን አሜን ብለው ሳይቀበሉ ባልተደራጀ ሁኔታ ለአፍታም ቢሆን ትግል አቋርጠው አያውቁም።

 

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፊውዳሉን ስርዓት ለመገርሰስ በተገኘው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተደረጉ የገበሬዎች አመፅ እንደታገሉ ሁሉ በወታደራዊው አምባገነን ስርዓት ወቅትም ስርዓቱን ለመጣል በበርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈው በተለያዩ አቅጣጫዎች መራራ ትግላቸውን አካሂደው የጭቆናና የአፈና አገዛዝ እንዲያበቃ አድርገዋል።

በእኩልነትና በአንድነት መንፈስ በጋራ የሚኖሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሁን ለደረሱበት የእኩልነት፣ የዴሞክራሲና የልማት ዘመን እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል።

ወደር የለሽ መስዋዕትነት የጠየቀ የትጥቅ ትግል አድርገውም አስከፊውን ስርዓት ከጫንቃቸው በመራራና እልህ አስጨራሽ ትግላቸው በመጣልና ታላቁን ሀገራዊ ድል በማብሰር ዛሬ ለተገኘው የፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች አብቅተውናል። ይህን እውነታ ማንም ሊክደው የሚችለው አይደለም።

ባለፉት ስርዓቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በገሃድ የሚጨፈለቁባቸው ጊዜያት ነበሩ። የመብት ጥያቄን ማንሳት “ውግዝ ከመአርዩስ” እንዲሉት ዓይነት ነበር። ዛሬ ላይ መላው የሀገራችን ህዝቦች በመስዕዋትትነታቸው እውን ባደረጉት የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለዘመናት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለማግኘት የበቁበትን ድል ተጎናፅፈዋል። ርግጥ የትናንቷ ኢትዮጵያ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦቿ የሰቆቃ ምድር እንደነበረች ማንም አይክድም።

የዚያ ዘመን ሰቆቃ ተዘርዝሮ አያልቅም። እነዚያ ወቅቶች ዜጎች ኑሯቸውን በቅጡ እንዳይገፉ የተቸገሩበት፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ግራ የተጋቡበት፣ መቋጫ በሌለው ጦርነት፣ ረሃብና ስደት የሚንገላቱበት ነበሩ። ግና ያ ሰቅጣጭ ወቅት ዳግም ላይመለስ ሀገሪቱን ተሰናብቷት ሄዷል—ዞር ብሎ እንደማያየን ለራሱ ቃል በመግባት። እናም አሁን የምንገኝበት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዘመን አዲስ ምዕራፍ ነው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የታገሉላቸው የዘመናት ጥያቄዎች መልስ ያገኙበት።

ይህ በመሆኑም ዛሬ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ኑሮን እያጣጣሙ ነው። ንፁህ አየር መማግ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ በነፃነት መንቀሳቀስና ሌሎች ሰላማዊ አየር በሀገራቸው ላይ እየናኙ ናቸው። ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ውድ የህዝብ ልጆች በከፈሉት የህይወትና የአካል  መስዕዋትነት ነው። ሀገሪቱም አስተማማኝ የሰላም ማማ ላይ ወጥታለች፤ ዓለም የመሰከረለት የልማት መስመር ላይም ናት፤ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ለማድረግ የተጓዘችው መንገድም ረጅም ነው።  

ታዲያ የዚህ ሁሉ መነሻው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደማቸው የፃፉትና ፍላጎታቸውን ከትበው ያኖሩበት ህገ መንግስት ነው።

በመላው ሀገራችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የስልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ ስር እንዲሰድ የተደረገው በህገ መንግስቱ ነው። እናም ህዳር 29 በየዓመቱ የዚህ ሁሉ ድል መነሻ የሆነው ህገ መንግስት በባለቤቶቹ ይዘከራል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው መንገድ እየተቀላጠፈ ይገኛል። የፌዴራል ስርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

ዕለቱ ሲከበር ዜጎች በህገ መንግስቱ ውስጥ የተጎናፀፉትን መብቶች ይዘክራሉ፤ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አንድነታቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ በማኖር የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚያስችላቸው መሆኑንም ይመሰክራሉ። የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት የስርዓቱ መሰረት መሆኑን ይገልፃሉ። አንዱ ብሔር ከሌላው የበላይ እንዲሆን የሚያደርግ ስርዓት እዚህች ሀገር ውስጥ እንዳልገነቡና እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት የማያምኑ ሃይሎች አጀንዳ መሆኑን ለፅንፈኞች በግልፅ ያስረዳሉ።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የህዝቦች የጋራ የሰላምና የልማት መናኸሪያ እንዲሁም ‘ሁሉም ህዝብ የእኔ ነው’ የሚል አስተሳሰብ ማራመጃ እንጂ የጠባቦችና የትምክህተኞች እንዲሁም እንደ አፓርታይድ ስርዓት መስመር እያሰመሩ ‘እገሌ ከዚህ እንዳታልፍ’ የሚባልባት አለመሆኑን የሚገልፁበት መድረክ ነው፤ ህዳር 29 ቀን።

ዕለቱ አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚን መገንባት የሚችል ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን መሆኑን ለወዳጅም ይሁን ለጠላት የሚነግሩበት ብሎም አብሮ ተደጋግፎና ተቻችሎ ለአንድ ዓላማ መኖርን የሚያሳዩበት የፍቅር አውድማም ነው። መልካም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ይሁንልን!

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy