Artcles

ፌዴራሊዝም እና ፅንሰ ሃሳቡ

By Admin

December 29, 2017

ፌዴራሊዝም እና ፅንሰ ሃሳቡ

                                                 አባ መላኩ

በፌዴራል የመንግሥት መስተዳድር እና በክልል መንግሥታት መካከል ሥልጣንና ተግባራት በሕገ መንግሥት በግልፅ የሚከፋፈልበት ሥርዓት ነው – የፌዴራል የፖለቲካ ሥርዓት። በዚህ ሥርዓት የመንግሥት ሥልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር፣ ግብር የመሰብሰብና የፋይናንስ ሃብት የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት በአንድ ማዕከል ወይም ቦታ ብቻ አይጠራቀሙም፤ አይከማቹምም። በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የሥልጣን ማዕከላት ወይም ሥፍራዎች ይከፋፈላሉ። ይህም ጉዳይ የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ያልተማከለ የመንግሥት ሥልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር እና የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት መኖሩን በግልጽ የሚያሳይ ይሆናል።

የፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የመንግሥት መስተዳድሮችን ያዋቅራል። ለተወሰኑ ጉዳዮች በጋራ መስተዳድር አማካይነት መስተዳድሮች ተቋማት የራስ አስተዳደር የሚያቋቁም የሥርዓት ዓይነት ነው። በዚህ ዓይነት የሥርዓት አወቃቀር የፌዴራል እና የክልል መስተዳድሮች የበላይና የበታች ግንኙነት የላቸውም።

ምንም እንኳን በህገ መንግሥቱ ተለይተው ለየራሳቸው በተሰጣቸው ጉዳዮች እያንዳንዳቸው ያላቸው ሥልጣን የተለያየና የየራሳቸውም ነፃነት የተጠበቀ ቢሆንም፣ የመንግሥት አስተዳደር ሥራና ሂደት በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት መካከል የመደጋገፍና የመቆራኘት ሥራን የግድ ማለቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም በሁለቱ መስተዳድሮች የተወሰነ የኃላፊነት መደራረቦች እና መደጋገፍ ይኖራል። ይህንንም ሁኔታ ሁሉም የፌዴራል ሥርዓቶች የሚጋሩት የወል ባህሪቸው ነው ማለት ይቻላል።

የፌዴራል የፖለቲካ ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የተፃፈ ሕገ መንግሥት አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ የዚሁ ሥርዓት ተከታይ አገሮች በተለያየ ሁኔታ ለሕገ መንግሥት የበላይነት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ። ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት የፌዴራል ሕገ መንግሥት፣ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ከመገንባት፣ ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን መሠረት ከማድረግ፣ የመንግሥትን ሥልጣን በሁለት ወይም ከዚያም በላይ ባሉ የመንግሥት አስተዳደር ማዕከላት መካከል ከማከፋፈል አልፎ ሥልጣንና ተግባር የወሰኑበት ከመሆኑ አንጻር ነው። እንዲሁም ጥቅሞችን ከማቻቻል፣ ከመደራደርና ሥልጣንን ከማከፋፈል፣ የፌዴራል ሥርዓታቸውን ከማዋቀር፣ ከማደራጀትና ስለ አሠራሩ ከደነገጉበት የበላይ ህግ መሆኑ ብቻ አይደለም። የአገራቸው አጠቃላይ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ የፖለቲካዊና የሕግ ሥርዓት የሚመረኮዝበትና የሚገነባበት ዋና የሕግ ማዕቀፍ በመሆኑም ጭምር ነው።

ሕገ መንግሥት በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ በጋራ ጉዳዮች ውስጥ የጋራ የመንግሥት መስተዳድር ተቋማትን ለማቋቋም፣ ለየራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ከሌላው የራስ መንግሥት መስተዳድርን ለማቋቋም ፈቃድና ፍላጎታቸውን የገለፁበት ከፍተኛ የህግና የፖለቲካ ቃል ኪዳን ሰነድ ነው። በዚህም ሥርዓቱ እያንዳንዱ መስተዳድር ለህገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከህገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ወይም የሚጋጭ ተግባር በህግ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለዚህ የህገ መንግሥት የበላይነትን መቀበል ለፌዴራል ሥርዓት መተግበርና ስኬታማነት ቁልፉና ወሣኙ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ህገ መንግሥትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትን በተግባር የማዋሉን ሁኔታ እጅግ አስፈላጊ የሚያደርገው፤ የፌዴራሉን መስተዳድር እና በእርሱ ሥር የታቀፉ አባል ክልላዊ መስተዳድሮች ማንነትና ህልውና የሚመነጨው እንዲሁም የሚመረኮዘው በህገ መንግሥቱ በመሆኑ ምክንያት ነው።

ምንም እንኳን በፌዴሬሽኖች መካከል እንደ ምሣሌነት ከላይ የተጠቀሱት የጋራ ባህሪያት ቢታዩም ሁሉም ፌዴሬሽኖች አንድ ዓይነት አወቃቀርን ሊከተሉ አይችሉም። እርግጥም ፌዴሬሽኖች ግዙፍ ልዩነቶች ሊኖራቸው የግድ ነው። ምክንያቱም ፌዴሬሽኖቹ ሥርዓቱን እንዲያቋቁሙ ያስገደዷቸው የየራሳቸው የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚለያዩ በመሆኑ ነው።

እርግጥ ፌዴራሊዝም በተለያዩ የፖለቲካ ክፍሎች ሥር የሚኖር፣ ነገር ግን የጋራ ቋንቋና ባህል ያለውን ህዝብ ወይም በጋራ የፖለቲካ ክፍሎች ውስጥ በአባልነት የመሳተፍን ጥቅም የሚፈልግ ነገር ግን በቋንቋና በባህል የሚለያይ ህዝብን አንድ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በፌዴራሊዝም የሚፈጠረው የአንድነት ውጤት በፌዴሬሽኑ የተካተቱ የአባል መንግሥት መስተዳድሮችን የተለየ መሆን የሚያዋህድ ወይም የሚያጠፋ ሆኖ መወሰድ አይኖርበትም።

ፌዴራሊዝም አንድነት የሚያራምደው ፌዴሬሽኑን ያቋቋሙትን አካላት የተለየ ማንነት የራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን እንዲሁም ለጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ መስተዳድራቸው የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚወከሉበትንና የሚሳተፉበትን ተቋማዊ ማዕቀፍ በህገ መንግሥት ዋስትና የሚሰጥ የሥርዓት አወቃቀር ነው። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ፌዴራሊዝም የሚያልመው በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ አንድነትንና ህብራዊነትን በመጠበቅና በመኮትኮት ዓላማ ያለው በመሆኑ ነው። በዚህም በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የጋራ እሴቶችን እና ሁሉ አቀፍ ማንነትን መገንባት ይቻላል።

ፌዴራሊዝም ከውጭ የሚመጣ ወታደራዊ ጥቃትን ወይም የጦርነት ሥጋትን በመከላከል ሠላም እና ደህንነት እንዲረጋጥ የሚረዳ ሥርዓት ነው። በተሳካላቸው ፌዴሬሽኖች ጀርባ ፌዴሬሽኖቻቸው በተመሠረቱበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ይህ ጥቃትንና ሥጋትን በጋራ የመከላከል እሴት ይስተዋላል። ለምሣሌ በአሜሪካ የውጭ ጥቃትን ወይም የጦርነት ሥጋትን በጋራ የመመከትና ሠላምና ፀጥታን ማስፈን ዓይነተኛ የፌዴራሊዝም እሴት ሆኖ አገልግሏል። በአሜሪካ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ የነበሩት መንግሥታት ፌዴሬሽንን ያቋቋሙት አንዱ ዐቢይ ምክንያታቸው ከውጭ ሊቃጣባቸው የሚችሉ ጦርነቶችን እና የጦርነት ሥጋቶችን ለማምከንና ለመከላከል ጠንካራ የመከላከያ አቅም ለመፍጠር በማሰብ ነው።

በሌላ ምሣሌ ደግሞ ሕንድንና ቤልጂየምን የመሳሰሉ ከዚህ ቀደም አሃዳዊ የመንግሥት የፖለቲካ ሥርዓት የነበራቸው ቢሆኑም፣ በውጭ ከሚመጣ ወይም ሊመጣ ይችላል ተብሎ ከሚገመት ሥጋት ሳይሆን፣ በውስጣቸው ያሉት የተለያዩ ማኅበረሰባዊ ልዩነቶች (Social diversities) ባላቸው ሕዝቦች የእኩልነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት የመሆንና የመጋራት ጥያቄዎችና ትግሎች አማካይነት ወደ ፌዴራላዊ የመንግሥት የፖለቲካ ሥርዓት ሊሸጋገሩ መቻላቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።

እርግጥ እነዚህ አገራት ፌዴራሊዝምን ለመምረጥ የተገደዱበት ምክንያት ስንመለከት ከውስጣቸው በተፈጠሩት ኃይሎች አማካይነት አንድነታቸው እንዳይሸረሸርና እንዳይጠፋ ለመከላከል በማሰብ ሆኖ እናገኘዋለን። ያም ሆነ ይህ ግን በሁለቱም ምሣሌዎቻችን ፌዴራሊዝም ለተጠቀሱት እሴቶች ማራመጃ ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግል የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም። በአንድ ወቅት ጽሁፌም በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ መጣጥፍ ስለማቅረቤ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ከዚህ በተጨማሪም ፌዴራሊዝም ነፃነትን እና ዴሞክራሲን በማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የመንግሥትን ሥልጣን እንደተለመደው ወደ ጎን በማለት በህግ አውጪው፣ በሕግ አስፈፃሚውና በዳኝነት አካላት መካከል ብቻ በማከፋፈል ሳይሆን ፌዴራሊዝም የመንግሥትን ሥልጣን በአግድሞሽ በፌዴራል መስተዳድሩና በአባል ክልል መንግሥታት መካከል በማከፋፈል በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተጨማሪ ገደቦችን በመጣል ለግለሰቦችና ለማኅበረሰቦች የተግባር ነፃነትን እና የፖለቲካ ሥልጣን ምህዳርን የማረጋገጥ ሚናን ይጫወታል።

አንድ ምሣሌ ማንሳት ይቻላል። ይኽውም በአሜሪካ ስለሚገኙ ፌዴሬሽኖች። ፌዴሬሽኖቹ እያንዳንዱ ዜጋ እና የፖለቲካ ቡድኖች በመንግሥት አስተዳደር ችግሮች ላይ ለመወያየት የሚሳተፉበትን የፖለቲካና የሕግ ምህዳር በመፍጠርና በመኮትኮት እንዲሁም ዜጎች በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በመንግሥት የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚሳፉባቸውን ዕድሎች በማስፋት ይታወቃሉ። ይህም ፌዴራሊዝም የማኅበረሰብንም ሆነ የግል ነፃነቶችን ለመጠበቅ የሚያገለግል ጠቃሚ የመንግሥት አወቃቀር መሆኑን የሚያስረዳ ነው። ፌዴራሊዝም ችግሮችን በመፍታት የጋራ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን የሚያመለክትም ጭምር ነው።