Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራላዊ ሥርዓቱና ጊዜያዊ የጸጥታ ችግሮች

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራላዊ ሥርዓቱና ጊዜያዊ የጸጥታ ችግሮች

                                                       ደስታ ኃይሉ

በቅርቡ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ጊዜያዊ የጸጥታ ችግሮች ህብረ ብሄራዊው ፌዴራላዊ ሥርዓት ያመጣቸው እንደሆኑ በአንዳንድ ወገኖች የተሳሳቱ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይደመጣሉ።

የእነዚህ ወገኖች አስተያየት ፈፅሞ ፈጽሞ ስህተት ነው። ምክንያቱም ጊዜያዊ ችግሮቹ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምክንያት የተከሰቱ ሳይሆኑ ከህዝቦች ተጨማሪ ፍላጎትና ከአፈጻጸም ሁኔታ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ በመሆናቸው ነው። ጊዜያዊ የፀጥታ ችግሮቹን ከፌዴራላዊ ስርዓቱ ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩ ሃይሎች ጨለምተኞች ይመስሉኛል።

ችግሮቹ ጊዜያዊ በመሆናቸው የፌዴራላዊ ሥርዓቱን ስኬቶች ማደብዘዝ የማይችሉና ህገ መንግስታዊው ሥርዓታችን ባበጀው መውጫ መንገድ በህዝቡ ባለቤትነት የሚፈቱ ናቸው። እናም የጨለምተኞቹ አስተሳሰብ ሚዛን የሚደፋ አይደለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ዛሬ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ጨለምተኞቹ ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም፡፡

አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ሥራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እድገትና አንድነት ሠላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ እንደማይኖር ግልፅ ነው።

ባለፉት ጊዜያትም ጨለምተኞች የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደማያባራ ጦርነት ውስጥ ትገባለች፤ ሀገሪቱም የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿም በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይጨራረሳሉ በማለት ሲያሟርቱ ነበር፡፡

እነዚህ ጨለምተኞች በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አልነበረም፤ ይልቁንም የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ፡፡ ጨለምተኞቹና ጽንፈኞቹ ያሻቸውን ቢሉም መንግሥትና ህዝቡ በውዠንብራቸው ሳይዘናጉ ብዝኃነታቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው ለጋራ ዕድገት መረባረቡን መረጡ፡፡  

የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም እምነት ተይዟል፡፡

ይህን እውነታ የተገነዘበው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊው የሀገሪቱ መንግሥትም ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት አገዛዝ ያላቀቀው ኢህአዴግ መራሹ ሥልጣን በህዝብ እና በህዝብ ብቻ የሚረጋገጥ እንደሆነ በማመን ዜጎች የትግላቸው ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏል፡፡

ህገ መንግሥቱ የህዝቦች የዘመናት ትግል ውጤት ስለሆነ፤ ይህን የህዝቦችን የዘመናት ትግል ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር ህገ መንግሥቱም ተረቅቆ ሥራ ላይ ሊውል ችሏል፡፡

አንዳንድ ጨለምተኞችና ፅንፈኞች ሀገሪቱ ባልተረጋጋ ውስጣዊ የፖለቲካ ችግር ትናጋለች፣ ህዝቦቿም እርስ በርሳቸው ይተላለቃሉ የሚሉ እሳቤዎችን ከተቃዋሚ ኃይሎች የእብደት ትንታኔ እየሰጡ ዋትተዋል፡፡ ሆኖም ይህን የሴራ አቋማቸውን ማንም አልተጋራቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ጨለምተኞቹ የሚሉትን ዓይነት በድንቡሽት የተገነባ ቤት ሳይሆን፤ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ በመሆኑ ነው። እናም ሥርዓቱን የተመለከቱበት መነፅር የተሳሳተና የተገለበጠ ህልም ብቻ የሚያሳያቸው መሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡

እነዚህ ጨለምተኞችና ጽንፈኞች የታላቁ መሪያችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ የዜና ዕረፍት ተከትሎ ያልቀባጠሩት አሉባልታና የወሬ ዓይነት አልነበረም፡፡ ሆኖም የእነርሱ በከሰረ የፖለቲካ እሳቤያቸው የሚያራምዱት ‘የሀገር ትበታተናለች’ የተሳሳተና መነሻና መድረሻ የሌለው ትንታኔ ከእነሱ ውጪ ማንንም ሊያሳምን አይችልም፡፡ ማንም ጤናማ አዕምሮ ያለው የሰው ፍጡር እንደሚገነዘበው ኢትዮጵያ በአሉባልታ ፈረስ የምትናድ አገር አይደለችም፡፡

ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው የፌዴራላዊ ሥርዓቱን ጥንካሬ ብሎም የህዝቦችን አንድነት በማጠናከሩ ረገድ የላቀ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው፡፡ ህገ መንግሥቱን በጽናት ለመጠበቅ ቃል ተገባብተዋል፡፡

ታዲያ ከትናንቱ ማንነታቸው ያልተማሩት ተቃዋሚ ተብዬዎችና ፅንፈኛ ኃይሎች ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ አይተው እንዳላዩ መሆንን መርጠዋል፡፡ ይልቁንም  ዛሬም ሥርዓቱን በባዶ ሜዳ ላይ ያለ አንዳች ተጨባጭ አስረጅ እንዲሁም በማኅበረሰቦች ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ጊዜያዊና ነባራዊ ሁነት በማጦዝ ስርዓቱ የፈጠረው ነው ከማለት አልቦዘኑም።

ታዲያ ይህ እኩይ ተግባራቸውም የሚያመላክተው ነገር፤ ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ታሪክ ራሱን በመድገም እነዚህ ኃይሎች የሥርዓቱን እመርታ ቁጭት በተንሸዋረረው  የተገለበጠ መነፅር እየተመለከቱ ለማደናገር መሞከራቸውን ነው።

እርግጥ የማምታታትና የማደናገር ሙከራቸው ምንም ውጤት ሊያስገኝላቸው አልቻለም፡፡ መላው የሀገሪቱ ህዝቦች በደማቸው የፃፉት ህገ መንግሥት ፀድቆ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም በአንድነት ተሳስረው የእድገት ጉዟቸውን ተያይዘውታል፡፡

አላዛኞችም የሚደልቁት የቆርጦ ቀጥልነት አታሞም ሰሚ አጥቷል፡፡ እናም በሚያስገርም ጨለምተኛ እሳቤያቸው ዓለም የመሰከረውንና ዕድገት ያመጣውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ከሽፏል ይሉናል፡፡

እነዚህ ሃይሎች በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን እያውቁም ወይም ቢያውቁም ለመናገር የሚደፍሩ አይደሉም። ምክንያቱም ለእነርሱ ጥላሸት የመቀባት ሥራ ይህ ሃቅ ምንም ስለማይጠቅማቸው ነው።

ሆኖም እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ በሥልጣኔ በበለፀጉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ አይቀርም።

ሆኖም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ መሆኑ ነው። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሥርዓት መፍጠር ተችሏል።

ዕድገት ሲኖር ፍላጎት ይጨምራል። የፍላጎት መስፋትም የግጭት መንስኤዎች ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ግጭት መቅረፍ የሚቻለው አቅም በፈቀደ መጠን የፍላጎቱን መስፋት በማቻቻል ነው። ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ደግሞ ይህን የማድረግ አቅም አለው። እናም ሥርዓቱ የጊዜያዊ ችግሮች መንስኤ ሳይሆን የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን በአግባቡ መፍታት የሚችል አቅም ያለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy