Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣቶችና ፌዴራላዊ ሥርዓታችን

0 440

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣቶችና ፌዴራላዊ ሥርዓታችን

ዳዊት ምትኩ

በአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እውን በመሆኑ በተለይ ወጣቶች የተጎናፀፏቸውን ድሎች በርካታ ናቸው። ወጣቶች ባለፉት ሥርዓቶች ለጦርነት የሚፈለጉና ራሳቸውን ሸሽገው የሚኖሩ፣ በአገሪቱ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ልማታዊ ክንዋኔዎች የሌላቸውና ከልማት አንዳችም ተጠቃሚ ያልነበሩ ናቸው።

ይሁን እንጂ፤ ፌዴራላዊ ሥርዓታችን በህዝቦች መስዋዕትነት በመረጋገጡ የአገራችን ወጣቶች በማንነታቸው መኩራት መቻላቸውን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ፣ እንዲዳኙና አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ብሎም በአገሪቱ ማናቸውም የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መሄዱን፣ መንግስት ባመቻቸላቸው የገንዘብ አቅርቦት ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸው የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ እያሳለጡ ይገኛሉ።   

እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች ባለፉት 16 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግስት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ተገንዝበዋል። ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግስት እየፈታው ነው። በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ማልማት ካልቻሉ ባለሃብቶች ቦታ በመቀማት ጭምር ወጣቶችን ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እያከናወነ ነው። ውጤትም እየተገኘበት ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት ምን ያህል ለወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ትኩረት የመስጠት ተግባሮች እውን እየሆኑ ነው።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም። የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ከ26 ዓመታት በላይ በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል።

ቀደም ባሉት ሥርዓቶች በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው። ይህም በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተገኘ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የአነስተኛና ጥቃቅን እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። ስለሆነም ወጣቶች በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ወጣቶች ከፌዴራል ሥርዓቱ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ የሥርዓቱ ባለቤቶች ጭምር ስለሆኑ ነው።

መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባውን የተስፋ ቃል ተፈፃሚ አድርጓል። አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ይህን ህዝባዊ ተግባሩን ይፈፅማል።

ታዲያ ወጣቱ ሥርዓቱ የእርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቀው ይገባል። በተለያዩ ጊዜያት እያሰለሱ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው ሥርዓቱን በውል ካለመገንዘብ አሊያም ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች የሚነሱ መሆናቸው ግልፅ ነው። እነዚህን ሃይሎች አደብ ለማስገዛት መንግስት ማናቸውንም ተግባሮች እንደሚከውን ቃል ገብቷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ የሚመነጨው በአገሪቱ በህዝብ አመኔታ ከተመረጠው መንግስት እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ሃይሎች አለመሆኑን ወጣቶች ያውቃሉ።

በመሆኑም መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቶች ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ በመራቅ የእነርሱ እኩይ ዓላማ መጠቀሚያ ላለመሆን መትጋት አለባቸው።

ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ የተለያዩ ሃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ጊዜያዊ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል። ወጣቶች የመንግሥትን የለውጥ ሃይልነት ስለሚያውቁ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት ወጣቶች በምንም ምክንያት የእኩይ ሴራ አራማጆች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም። ይህን ሥርዓት ታግለውና መስዋዕት በመክፈል ጭምር ያመጡት የትናንትናዎቹ ወጣቶች ለዛሬው ወጣት አስረክበውታል። የዚህ ትውልድ ወጣት ደግሞ እነዚያ ውድ የህዝብ ልጆች በደማቸውና በአጥንታቸው የሰጡንን ሥርዓት የማስቀጠል ሃላፈነት የዚህ ትውልድ አደራ ነው።

ይህ ትውልድ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መወጣት ይኖርበታል—ድህነትን በመዋጋት። የትውልዱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “የድህነትን ተራራ በዕውቀት ጥይት መናድ ይቻላል” እንዳሉት፤ ድህነትን ለመቅረፍ ዋነኛው መሳሪያ ትምህርት መሆኑን ወጣቶች መዘንጋት የለባቸውም። እናም የዕውቀት መገብያቸው የሆነውን ትምህርት ቤቶችን ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከትና ሽኩቻ እንዲሁም ከዘረኝነት አስተሳሰብ እንዲፀዱ ማድረግ ይኖርበታል። ነተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዘረኝነት አስተሳሰብ ርቀው የአንድ ሀገራዊ ዕድገት ማሳያ መሆን ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ሰዓት ሆን ተብሎ የአገራችንን ሰላም ለማወክ በፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች እኩይ ሴራ እንደሚቀነባበር መረዳት ያስፈልጋል። ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የራሳቸውን ውሸት እየጨመሩ ማናቸውንም አገራዊ ችግሮች ሊታከኩ ይፈልጋሉ። ወጣቶችን በማደናገር ይብሬር ግጭትን ሊያስነሱ ይሞክራሉ።

ስለሆነም ወጣቶች ይህን እኩይ ሴራ ተገንዝበው የእነርሱን ማንነት ሊታገሏቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፉ ይገባል። ወቅቱም አሁን ይመስለኛል። ወጣቶች ይህን ማድረግ ካልቻሉ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያገኙት የነበረውን ሁለንም ጥቅሞች ሊያጡና ወደ ድሮው ዘመን ሊመለሱ ይችላሉ። እናም ተስፋቸውን በመንግስትና በሥርዓቱ ላይ በመጣል የተጀመረውን የልማት ዕቅድ ማሳካት ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ሰዓት ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለሁለተኛ ጊዜ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፏል። የዕቅዱ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የአገራችን ህዝብ፤ በተለይም ወጣቶች ለስኬታማነቱ እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ ማጎልበት ይኖርባቸዋል። በዕቅዱ ቀሪ ዓመታት ወጣቶች በእነዚህ የስራ ባህላቸውንና ተነሳሽነታቸውን እንዲሁም የቁጠባ ባህላቸውን በበለጠ ሁኔታ ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy