DCIM100MEDIADJI_0009.JPG

የስራችን ውጤት ማሳያ

By Admin

December 27, 2017

የስራችን ውጤት ማሳያ

                                                  ዘአማን በላይ

የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት (IMF) ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ባደረጉት የስራ ጉብኝት ስለ አገራችን ምጣኔ ሃብት ዕድገት አንድ እውነታ ተናግረዋል። ዳይሬክተሯ ወደ ሀገራችን መጥተው ከመንግስት ከፍተኛ ባላስልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ የመጡት በአገሪቱ እየተተገበረ ያለውን የኢኮኖሚ ሞዴል  መመልከታቸውን ገልፀዋል። አገሪቱ በኢኮኖሚ እድገት ስኬት እያስመዘገበች መሆኗን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ይህ እማኝነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘንድ ያላትን ቦታ የሚያሳይ ነው። ተቋማቱ ለአገራችን ምጣኔ ሃብት ምስክርነት የሚሰጡት ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው ዕድገት በትክክለኛ መስመር እንደሚመራ፣ አብዛኛውን የአገሪቱን ዜጋ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ፣ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍልን በዘላቂነት በማረጋገጥ ላይ ያለና ወደፊትም ይህን ማድረግ የሚችል ቁመና ያለው በመሆኑ ነው።

እንደሚታወቀው አገራችን እያከናወነች ባለችው የልማት ስራዎች በርካታ ስኬቶችን መጎናፀፍ ችላለች። በእነዚህ ስኬቶች መላው የሀገራችን ህዝቦች በየደረጃው ተጠቃሚ ሆነዋል። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በልማቱ መስክ ያስመዘገባቸው ውጤቶች አብዛኛውን ህዝብ ያደረጉ ናቸው። በዜጎች ህይወት ላይም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት መቻላቸውም እንዲሁ።

ታዲያ ስለ ዕድገት ስናነሳ ቢያንስ የስራችን ውጤት የሆኑ ሁለት እውነታዎችን ማንሳት ይገባል—አገራችንን በግብርናው ዘንድ ከፍ እያደረጋት ያለውን ግብርናን እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር የጎበኙትን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ። ምክንያቱም እነዚህ ዘርፎች የስራችን ውጤቶች ማሳያ ስለሆኑ ነው።

ከግብርናው ስንነሳ ዘርፉ እስካሁን ድረስ የአገራችን ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር ሆኖ መቀየቱን እንገነዘባለን። በግብርናው መሪነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተከታተለ ባለ ሁለት አሃዝ ፍጥነት የሚያድግ እንዲሁም የአብዛኛውን የአገሪቱን ነዋሪ ህዝብ ህይወት ትርጉም ባለው ደረጃ መለወጥ የቻለ ነው። ዕድገቱም ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚናውን እስከሚረከብ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።

ግብርናው በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ የመወሰዱ ተገቢነት የሚያጠያይቅ አይደለም።

በሁለተኛው የልማት ዕቅድ የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ተደርጎ ውጤት ተገኝቶበታል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በዕቅዱ አፈፃፀም እንደሚያሳየው ከወዲሁ እመርታዎች እየተገኙ ነው።

መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ እየተገኘ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም።

ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

ለአርሶ አደሩም በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።

የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል። አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል።

መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

መንግሥት ባስቀመጣቸው የግብርናው ዘርፍ የልማት ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና መርሀ ግብሮች በመጠቀም ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን በማበረታታትና በመሸለም በርካታ ውጤታማ አርሶ አደሮችን ለማፍራት ተችሏል። እነዚህ አርሶ አደሮች ለሌሎች ፋና ወጊ በመሆን የዘርፉን ስኬቶች እያጎለበቷቸው ይገኛሉ። ይህም የኢንዱስትሪው ዘርፍ በግብዓት እጥረት እንዳይሰተጓጎል የራሱን ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከነበረት ኋላ ቀር ሁኔታ እየተቀየረ ነው። በተለይም መንግስት በየአካባቢው የገነባቸውና የሚገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፉን እያነቃቁት ይገኛሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሚስ ላጋርድ ወደ አገራችን መጥተው ስለ ስኬታችን እንዲሁም መስተካከል ስለሚገባቸው ጉዳዩች የተናገሩት አገራችን ምን ያህል በሌላው ዓለም ዘንድ ተቀባይነት ያላት መሆኗን የሚያሳይ ነው። ርግጥ የፋይናንስ ተቋማቱ ከአገራችን ጋር ያላቸው ጉዳይ ከእነርሱ ጋር የስጋ ዝምድና ስላለን አሊያም በርዕዩተ-ዓለም ደረጃ “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ” ስለሆንን አይደለም።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የዋና ዳይሬክተሯ ጉብኝት ይህ መንግስትና ህዝብ ተስፋ ያላቸው መሆኑን ተቋማቸው ስለተገነዘበው ነው። ይህ መንግስትና ህዝብ ያለባቸውን የፋይናንስ እጥረት መቅረፍ ከቻሉ ከራሳቸው አልፈው ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ኢኮኖሚ መድን ሊሆኑ እንደሚችሉ ስለተገነዘቡ ነው። ይህ መንግስትና ህዝብ ሰርተው መለወጥ የሚችሉና ነገ ማንም ከደረሰበት የብልፅግና ማማ ላይ መውጣት እንደሚችሉ አሳምረው ስለሚያውቁ ነው። ይህን የፈጠረው ደግሞ የስራችን ውጤት እንጂ፤ አንዳንድ በግራ ጎናቸው የተነሱ ወገኖች እንደሚያስወሩት አገራችን የምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖን ስለምትከተል አይደለም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ከምዕራቡም ይሁን ከምስራቁ ጎራ ጠቃሚ ልምዶችን ብትወስድ ክፋት የለውም። ግና በሁለቱም ጎራ ተፅዕኖ ስር ልትወድቅ አትችልም። የትኛውም ጎራ በተፅዕኖ ስር ሊያውላት አይችልም። የራሷን ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች የቀመረችና በእነርሱም እየተመራች ዓለም የሚያውቀው ዕድገት እያስመዘገበች ያለች አገር ነች። ከዚህች አገር ጋር መስራት ደግሞ የተቋማቱ ፍላጎት እንጂ ሌላ ተቀጥላ ስያሜ እየተሰጠው ስኬትን የሚያጥላላ ሊሆን አይገባም።