Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለውጥ አምጪው ዘርፍ

0 224

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለውጥ አምጪው ዘርፍ

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

ግብርና የምጣኔ ሃብታችን አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። አሁን በምንገኝበት ደረጃ የግብርና ሚና የላቀ ነው። ታዲያ ዘርፉን ለማዘመን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። መንግስት የተፋሰስ ስራን ለማጎልበት ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እየሰራ ነው። ህብረተሰቡም ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረገ ነው።

የህብረተሰቡ በተቀናጀ የተፋሰስ ስራ እያደረገ ያለው እጅግ አበረታች ተሳትፎ በግብርና ልማት ላይ ቀጥተኛ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ህብረተሰቡ የተፋሰስ ስራ ተጠቃሚ መሆኑ በአሁኑ ወቅት ምርትና ምርታማነት ጨምሯል። ይህም ሁለቴና ከዚያ በላይ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን መፍጠር ችሏል። የዕድገታችን ዋልታና ማገር የሆነው ይህ ዘርፍ እንዲያድግና በአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ላይ ጉልህ ለውጥ እንዲያመጣ የተጠናከረ ትኩረት ይሻል።

መንግስት ይህን በመረዳቱም የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው። በተለይ ድርቅን በመከላከል የተፈጥሮ ፀጋዎችን መንከባከብ ያስፈልጋል። በቅርቡ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የዚህን ዓመት የተፋሰስ ስራዎችን የዝግጅት ምዕራፍ የአፈፃፀም ግምገማ በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ እንደገለፁት፤ ሀገሪቱን ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ለመታደግ ጥራቱን የጠበቀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በየደረጃው ማከናወን ይገባል።

ባለፉት ጊዜያት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ የተለያዩ ችግሮችን አስከትሏል። በተለይም ለግብርና ልማት ወሳኝ የሆኑ የአፈር ለምነት፣ የገፀና የከርሰ ምድር ውሃ፣ እፅዋትና ደኖች መመናመን እንዲሁም ድርቅ በየጊዜው መከሰቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ችግሩ የደረሰባቸውን አካባቢዎች ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ በተፈጥሮ ሂደት እንዲያገግም እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን መልሶ የማዳን ስራ መከናወን አለበት ብለዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ተግባር ድርቅን ከመከላከል ባሻገር ለግብርናው የተመቻቸ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

እንደሚታወቀው መንግስት የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካትና የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን አጠናክሮ ለመቀጠል የተለያዩ ተግባራትን ህብረተሰቡን አንቀሳቅሷል። ይህም የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል፣ ከፍተኛ የኃይል ማመንጪያ ግድቦችና የመስኖ አውታሮች የታለመላቸውን ዘለቄታዊ ጠቀሜታ እንዲሰጡ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም።

ርግጥ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ጉልበት ሳይባክን ጥራቱን የጠበቀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በየደረጃው መከናወን አለበት። ይህም አካባቢያዊ ጠቀሜታዎችን ከማረጋገጥ ባሻገር ሀገሪቱን ብሎም ዓለምን እያሰጋ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ለመቋቋምና ለመላመድ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል። ይህም የግብርናው ዘርፍ እየዘመነ ትርፍ አምራች አካባቢዎች በድርቅ ለተጎዱት እንዲደርሱ እንዲሁም ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎችም የምራች እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመምታት ያህል ነው።

መንግስት እስካሁን ድረስ ግብርናውን ለማዘመንና የአምራች አካባቢዎችን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ተግባሮችን ከውኗል። በተለይም ግብርናውን ለማዘመን ተግባሩን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር እየተደረገ ያለው ጥረት ችግሩን የሚፈታው ነው።

እንደሚታወቀው የተሻሻሉ የሰብልና የቀንድ ከብት ዝርያዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ የግብርና ዘርፍ ማሳደጊያ ሰልት ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተለይም በተራቆቱና በተጎዱ አከባቢዎች ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትም ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ደን 80 በመቶ ለሚሆኑ የገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ዜጎች የኃይል ምንጭ ነው። በተለይም የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሆኑትን ሙቀት አማቂ ጋዞችን በማምከን ረገድ የደን ዘርፉ የማይተካ ሚና አለው።

የተለመደው የኢኮኖሚ ዕድገት አማራጭ ከቀጠለ እስከ 2022 ዓ.ም ባለው ጊዜ 9 ሚልዮን ሄክታር ደን ሊመነጠር እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለሀገር ውስጥና ለአከባቢያዊ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታን፤ ከታዳሽ የሃይል ምንጮች ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ኤሌክትሪክ ለዘመናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሃይል ምንጭ በመሆኑ አርሶ አደሩ የዚህ ተቋዳሽ እንዲሆን የተጀመሩት ስራዎች አበረታች ናቸው።

ከከተሞችና እንዱስትሪዎች የሃይል ፍጆታ አንስቶ ለመስኖ የሚያስፈልገውን ውሃ ለመግፋት የሚውል ነው። በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ የሚያድገው የሀገሪቱ አኮኖሚ በዓመት ከ14 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያስፈልገው ነው። እናም በዚህ ረገድ ሁሉንም የሃይል ምንጮች አቀናጅቶ ለመጠቀ ጥረት እየተደረገ ነው።

እንደሚታወቀው ሀገራችን ከታዳሽ የሀይል ምንጮች ብቻ 60 ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያስችል እምቅ አቅም አላት። ከዚህም ውስጥ የሃይድሮ ዘርፉ 45 ሺህ ሜጋ ዋት የሚይዝ ሲሆን፣ የታዳሽ ሃይል ምንጭ ደግሞ 75 በመቶ ድርሻ አለው። ከጂኦተርማል፣ ከንፋስና ከፀሀይ የሚገኘው ሃይል ቀሪውን 25 በመቶ ድርሻ የሚሸፍን ነው። እነዚህን ለሃይል አቅርቦት የሚውሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን አቀናጅቶ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል።

ይህ ሲሆንም ለግብርናው ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። በተቀናጀ የተፋሰስ ስራዎች አማካኝነት መገኘት የሚገባው ምርትና ምርታማነትም ያድጋል። ርግጥ በዚህ ረገድ ባለፉት ጊዜያት በተከናወኑት ስራዎች ብዙ ርቀት መሄድ የተቻለ ይመስለኛል።

በተለይም በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

ለአርሶ አደሩም በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።

የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል። መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

ይህ ሊሆን የቻለው እንደ የተቀናጀ የተፋሰስ ስራዎች ዓይነት ምርትን አሳዳጊ ተግባሮች በየደረጃው በመፈፀማቸው ነው። አሁንም ቢሆን የተቀናጀ የተፋሰስ ስራዎችን በማጠናከር በግብርናው ዘርፍ ለውጥን ማምጣት ቢቻልም፤ ይህን ስራ ይበልጥ ማስፋት ያስፈልጋል። በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዩችም በየጊዜው እየተገናኙ በመወያየት ስራው ይበልጥ የሚሰፋበትን ሁኔታ መቀየስ የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

 

  

    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy