Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ሕዝቤ ሆይ የቀድሞው ነኝ”

0 362

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ሕዝቤ ሆይ የቀድሞው ነኝ”

አባ መላኩ

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ግጭቶች ሲበረቱ እና  በርከታ ንጹሃን  ዜጎች በማያውቁት ነገር ሲገደሉ፣ በመቶ ሺዎች  ከቀያቸው ሲፈናቀሉና ሲንገላቱ እንዲሁም ንብረቶቻቸው በጠራራ ጸሃይ ሲወድምና ሲዘረፍ  ስመለከት ነብሴ ክፉኛ ተጨነቀች፣ መንፈሴም ተረበሸ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜትም ክፉኛ  ተጫጭኖኝ  “ኢህአዴግ ሆይ ወዴት ነህ?” ስል አንድ አጭር ጽሁፍ አዘጋጅቼ ነበር። ይሁንና  ነገሮች እንዳሰብኳቸውና  እንደፈራኋቸው ሳይሆኑ  ኢህአዴግ በአጭር ጊዜ በርካታ ነገሮች መልክ መልካቸውን እንዲይዙ ማድረግ በመቻሉ ደስ አለኝ።  ሰሞኑን የኢህአዴግ እህት ፓርቲ አመራሮች ለ17 ቀናት ያካሄዱትን ግምገማ ማጠናቀቅ ተከትሎ  የሰጡትን መግለጫ በጥሞና ለተከታተለው የአገራችን  ችግሮች  ዘለቂ መፍትሄ  እንደሚያገኙ ተስፋ የሚያጭር  ነው። በመሆኑም ኢህአዴግ “ሕዝቤ ሆይ የቀድሞው ነኝ”  ሲል  ድምጹን አሰምቷልና ይህችን ጽሁፍ አዘጋጀሁ።

 

ለአገራችን ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓት  ጭፍን ተቃውሞም ይሁን ድጋፍ የሚበጃት  አካሄድ አይደለም።   እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ከፈጸማቸው ስህተቶች ይልቅ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ያበረከታቸው ስኬቶች  እጅጉን  የጎሉ ናቸው። ኢህአዴግ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የከፍታ መንገድን አስጨብጧል፤ በርካታ ተጨባጭና ተቆጣሪ ለውጦችን ኢህአዴግ አስመዝግቧል። ለአብነት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ህገመንግስታዊና ጠንካራ  መንግስት እንዲኖራት አድርጓል፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፣  ነጻነትና እኩልነታቸው እንዲረጋገጥ በማድረግ  ህዝቦች  በማንነታቸው እንዲኮሩ መንገድ ጠርጓል፤ ጅምር ቢሆንም  ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት እንዲገነባ  በማድረግ በአገራችን ዘላቂ ሰላምን አረጋግጧል፣ በዚህም ሳቢያ ህዝብና መንግስት አትሩሮታቸውን ወደ ልማት በማድረጋቸው  ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይነት ያለው  ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ  ዕድገት በማስመዝገብ  ሁሉም  በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ አመቻችቷል፤  በዚህም በዓለም ዓቀፍ ተቋማት የተረጋገጠ ድህነትን ከግማሽ በላይ መቀነስ ተችሏል። በአፍሪካ የተመሰከረለት ጠንካራ፣ በዲሲፒሊን የታነጻ ህዝባዊነት የተላበሰ የመከላከያ ሰራዊት ገንብቷል።

 

በማህበራዊ መስክም  ተጨባጭ ለውጦች  ተመዝግበዋል። ዛሬ ላይ  ከአገራችን  አንድ ሶስተኛ  የሚሆንው  ህዝብ  ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ባለው ደረጃ ተማሪ  ሆኗል።  በጤናው ረገድም  በተባበሩት መንግስታት ተቋማት  ጭምር የተመሰከረ ስኬቶች ተመዝግቧል፤  በትራንስፖርቴሽን (ቀበሌን ከቀበሌ ማገናኘት የሚያስችሉ የገጠር መንገዶች እስከ ትላልቅ አገር አቋራጭ አስፋልት መንገዶች፣ የአገር አቋራጭና የከተማ ቀላል ባቡር ሃዲዶች ዝርጋታ፣ የኤርፖርቶች መስፋፋት)፣ በከተማም ሆነ በገጠር  የኤሌክተሪፊኬሸን መስፋፋት፣ ከነእጥሩም ቢሆን በተገልጋይ  ብዛት በአፍሪካ በቀዳሚነት የሚነሳ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ወዘተ  ማስፋፋት ተችሏል። እነዚህ  ነገሮች  አገራችን ተስፋ ሰጪ እና  የማንንም ቀልብ ሊያማልል  የምትችል  እንድትሆን አድርጓታል።  ኢህአዴግ  ገዢ  ፓርረቲ   ሆኖ  በመራው መንግስት  አገራችን በታሪኳ አይታው ወደማታውቀው አዲስ የከፍታ ዘመን መውጣት ጀምራለች።

 

ይሁንና ኢህአዴግ ከቅርብ  ጊዜ ወዲህ  እየፈጸማቸው ባሉ  አንዳንድ ተራና ትናንሽ  ስህተቶቹ  ሳቢያ   አንድ ሺህ ስኬቶቹ    ሲጠፉበትና ሲጣፋበት እየተመለከትን  ነው።  ይህ አማላይና ሁላችንንም የሚያጓጓ  ተስፋ  የጫረብን  የአገራችን  ዕድገት ከእጃችን ሊወጣ ተቃርቦ  ነበር። በርካታ አስተያየት ሰጪዎችም በኢህአዴግ  ቤት የቀድሞው  መደማመጥና  መከባበር  ቀንሷል፤  በዚህም ድርጅቱ  የቀድሞው ጥንካሬው  እየከዳው በመሆኑ አገሪቱን  በአግባቡ መምራት እየተሳነው  ይመስላል ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህም  በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ  መልኩ  በርካቶች  ህይወታቸውን እያጡ፣ ሚሊየኖች  እየተፈናቀሉ፣ ንብረታቸውን እየተዘረፉ ያለበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። ህብረተሰቡም ኢህአዴግ እንዲስተካከል  ድምጹን አሰምቷል። እውነትም  ከነችግሩም ቢሆን ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ  አስፈላጊ ፓርቲ ነው። ዛሬ ላይ ነገሮች ተቀይረዋል። በኢህአዴግ ቤት ድክመቶች በጋራ ተነቅሰው ወጥተው በጋራ መፍትሄ እየተፈለገላቸው ነው። የሚሰሩ እጆች ይቆሽሻሉ እንደሚባለው፤ ኢህአዴግ ስሰራ ለለውጥ ስታትር፤ ስህተቶችን  ፈጽሜላሁና  ልስተካከል ሲል ህዝብን ይቅርታ  ጠይቋል። ይህ ለእኔ  ታላቅነት ነው።   

 

የኢህአዴግ የቆየ ጠንካራ  የግምገማ  ባህል ያለው ድርጅት እንደሆነ እናውቃለን፡፡  ይህ ድርጅት ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች መካከል  አንዱና ቀዳሚው ነገር የድርጅቱ  ጠንካራ  የግምገማ ባህሉ ይመስለኛል። የድርጅተቱ ጠንካራ የግምገማ ባህል አባላቱ ጥሩ ስነ ምግባር እንዲላበሱ፣ ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ከሚያደርጋቸው  ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋንኛው ጉዳይ ናቸው፡፡ ይሁንና ከቅርብበ ጊዜ ወዲህ ሺዎች የተሰውለት  እነዚህ የድርጅቱ  እንቁ እሴቶች መሸርሸር ጀምረው ነበር። የድርጅቱም ግምገማም ይህንኑ አረጋግጦ የመፍትሄ  መንገዶችንም  አመላክቷል።  

 

ለኢህአዴግ  ስኬት መሰረቱ  የድርጅቱ ውስጠ ዴሞክራሲያዊነት፤  በእያንደንዱ  ውሳኔ  የብዙሃን ድምጽ  ተቀባይነት የሚያገኝበት አሰራሩ ነው።  በፓርቲው  የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት፣ ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ በመጨረሻም  የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት የነገሰበት ፓርቲ  ነው፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠንካራው የኢህአዴግ ቤት  ለማንም  የማይበጁ አንዳንድ  መደበላለቆችና መደነቃቀፎች  በከፍተኛ አመሩሩ ጭምር ስናስተውል፣ ይህ አካሄድ   በወቅቱ መታረም ካልቻለ ለአገራችን  እንዳይተርፋት ሲሉ  በርካታ  አገር ወዳድ ዜጎች  ስጋታቸውን  ሲገልጹ  ነበር።  እኔም ይህን ስጋት  እጋራው  ነበር። ምክንያቱም  በመደጋገፍና በመከባበር የሚታወቀው በኢህአዴግ ቤት እንዲህ ያለ  አለመናበብ  መከሰቱ  የተለመደ ነገር አይደለም።  እንዲሁም በበርካታ የአገራችን   አካባቢዎች መሰረታዊ እሴቶቻችን  እየተሸረሸሩ፤ በአንጻሩ ደግሞ  የጥበትና ትምክህት አስተሳሰቦችና ተግባሮች  እየነገሱ  ህዝቦች በመልካም አስተዳደር እጦት ሲንገላቱ  ስንመለከት  በበርካታ  አገር ወዳድ  ዜጎች ላይ ጭንቀት ፈጥሮ ነበር።   

 

ህብረተሰቡም ኢህአዴግ  አካሄዱን እንዲያሻሽል  ተቃውሞውን  በአደባባይ ገልጿል። እኔ እንደተረዳሁት ህብረተሰቡ ኢህአዴግን ጠራርጎ ያላጠፋው እስካሁን ማስመዝገብ በቻለው መልካም ነገሮች ሳቢያ ነው። እውነቱን እውነቱን እንነጋገግር ከተባለ ኢህአዴግን ከህዝብ እንዳይነጠል የታደገው በ27 ዓመታት ያስመዘገባቸው  ስኬቶች እንጂ በቅርቡ በአገራችን  እንደተከሰተው ችግር ቢሆን ኖሮ ህብረተሰቡ ኢህአዴግን ጠራርጎ ያጠፋው ነበር።   ይህ የሚያሳየው ህብረተሰቡ የሚፈልገው  ኢህአዴግ ከእንቅልፉ እንዲነቃና ወደ ቀድሞው ህዝባዊ ጎዳናው እንዲመለስ  እንጂ  ተጠራርጎ እንዲጠፋ አለመሆኑን ነው።

 

የኢህአዴግ  መርህ መሰረት የሚያደርገው የህዝብ ፍላጎትንና የህዝብ ድጋፍ ብቻ  ነው፡፡ እስካሁን ድርጅቱ ስኬታማ የሆነውም ጠንካራ ህዝባዊ  መርሁ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መደነቃቀፍ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከዚህ አዙሪት መውጣት የሚያስችለውን አካሄድ ተከትሏል። የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚዎች ለመደነቃቀፎች ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ለይተው ለስህተቶች መፈጠርም  ሃላፊነቱን በጋራ ወስደዋል። ይህ ታላቅነት ነው። በዴሞክራሲያዊ መዓከላዊነት የሚታወቀው ኢህአዴግ አሁንም ችግሮቹን  በጋራ ለይቶ  መፍትሄም በጋራ  አስቀምጧል።  ከላይ እንደጠቀስኩት  የኢህአዴግ ስኬቶች መሰረት የሚያደርጉት ህብረተሰቡን ነው። አገራችን በስኬት ጎዳና እንድትረማመድ  ኢህአዴግ  አመራር ይስጥ እንጂ ሞተሩ ህዝብ ነው። አሁንም ኢህአዴግ እስተካከላለሁ ወደ ቀድሞው አቋሜ ተመልሻለሁ ሲል ያስቀመጣቸው ነጥቦች ስኬታማ የሚሆኑትና የአገራችን ዕድገት ቀጣይነት የሚኖረው በህዝብ ተሳትፎ ሲታጀብ ነውና  ህብረተሰቡ ድጋፉን ሊያደርግለት ይገባል ባይ ነኝ። በአሁኑ ደረጃ  የኢህአዴግ  ስኬትም ሆነ ውድቀት ከአገራችን ህልውና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው  በመሆኑ  ህብረተሰቡ  ኢህአዴግ ወደ መስመሩ ለመመለስና የቀድሞውን ህዝባዊነት እንዲላበስ የሚያደርገውን ጥረት ሊያግዘው ይገባል ባይ ነኝ።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy