መልካም አስተዳደር:- የፈተናዎቻችን ሁሉ ቁንጮ
ይልቃል ፍርዱ
በሀገራችን የሚታየውን የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና፣ የፍትሕ እጦት፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና ተዛማጅነት ያላቸውን ችግሮች ለማስወገድ በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረው ትግል የተጠበቀውን ያህል ባይራመድም የተወሰኑ ለውጦችን ማሳየት ግን ችሏል፡፡ በቅርቡ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ ቀደም ሲል የተጀመሩት መልካም አስተዳደርን የማስፈን ዙሪያ መለስ ትግሎች በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥሉ መሆኑ በዝርዝርና በሀይለ-ቃል ተገልፇል::
የመልካም አስተዳደር ችግርን በመፍታት በመንግስታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና አስተዳደሮች ውስጥ ሕዝብን በማገልግል ረገድ የታየው ሰፊ ችግር ከብልሹ አስራር፣ ከሙስና፣ ከፍትሕ እጦት ወዘተ ጋር በሰፊው የተቆራኘ በመሆኑ ይሕን ትግል በስፋት በማካሄድ ውጤት ማምጣት የሚቻለው በዋነኛነት ሰፊውን የሕብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ነው፡፡
ሙስና የተወሳሰበ ባሕርይ ያለው የወንጀል ተግባር ነው፡፡ በዋነኛነት በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ በሀላፊነትና በተለያየ የስራ እርከን የተሰማሩት ሀይሎችን በማሳተፍና በስማቸው በመጠቀም ከውጭ የሚገኘው ደላላ፣ ጥገኛና ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል በመንግስትና ሕዝብ ሀብት ዘረፋ በመሬት ቅርምት፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በሰፊ የመሰረተ ልማትና የግንባታ ስራዎች ውስጥ ጨረታዎችን ያለውድድር፣ ውድድርም ቢኖር አስቀድመው በሙስና የተደራደሩዋቸው ሰዎች እንዲያሸንፉ በማድረግ ወዘተ ይህ ቀረሽ የማይባል መጠነ ሰፊ የመንግስትና የሀገር ሀብት ዘረፋዎች ተካሂደዋል፡፡ ይሄው ሁኔታ በቀጥታ በየተቋማቱ ካለው የመልካም አስተዳደር ብልሽት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
የመልካም አስተዳደር አለመኖር በብዙ መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡ ፍትሕን በገንዘብ በመሸጥ መጠነ ሰፊ በደል መፈጸም፤ ሕዝብን ማስመረር፤ ተገቢ አገልግሎት አለመስጠት፣ ተገልጋይን ማንገላታትና ማስመረር፤ ተገልጋዩ ለመጣበት ጉዳይ አስቸኳይ ውሳኔ ሰጥቶ ከመሸኘት ይልቅ ጉቦ በመጠየቅ ገንዘብ ካልሰጠህ ምን ታመጣለህ? በማለት ሕዝቡ እንዲከፋ፣ እንዲመረር የተደረገው ሁሉ በመልካም አስተዳደር አለመኖርና እጦት ነው፡፡ ይህን ችግር ከስሩ ለመንቀል በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰፊ ስራን መስራት ይጠይቃል፡፡
ወጣቶችን ከትምሕርት ቤት ጀምሮ ከስር ማስተማርን፣ በየደረጃው ኮትኩቶ አስተሳሰባቸውን መቅረጽን ይጠይቃል፡፡ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ከታች እስከ ላይ የሚገኙትን አስቀድሞ የሚጠልፈው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የሚረማመደው መልካም አስተዳደርን በመደፍጠጥ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ለበርካታ ማሕበራዊ ችግሮችም መንስኤ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ያደፈርሳል፤ የሕብረተሰሰቡን ማሕበራዊ ሕይወትና መስተጋብር ያስተጓጉላል። የመልካም አስተዳደር ችግር በሕብረተሰቡ ውስጥ ገኖ ሲሰፍን ለሁከት፣ ለብጥብጥና ለትርምስ መነሻ ይሆናል፡፡ በሀገራችን በመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤነት የተፈጠሩት ችግሮች ሌሎች ብዙ ችግሮችን ሲወልዱ የተመለከትነውም ለዚሁ ነው፡፡
ለዚህ ነው ይህንን ችግር በመፍታት በሕብረተሰቡ ውስጥ ከሁሉም በፊት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ መንግስት በተሀድሶው ለውጥ ለማምጣት ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በፌደራል መስሪያ ቤቶችና በአዲስ አበባ መስተዳድር እንዲሁም ክየክልል መንግስታትም በራሳቸው በኩል በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው በተገኙ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ እርምጃዎች ወስደዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው አመት እንደገለጹት ኢሕአዴግ ባደረገው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ ከ50 ሺህ በላይ አባላቱ በግምገማው መነሻነት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል፡፡ ከአባልነት የተባረሩ፣ ከነበሩበት ኃላፊነት ዝቅ የተደረጉ፣ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዲመራና በሕግ እንዲታይ የተደረጉም ይገኙበታል፡፡
ይህም ሁኖ ጅምር ስራውን ለማሰናከል ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው ኃይል ጥገኛውና ደላላው ጭምር ከቢሮክራሲው ጋር በመዶለት መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ሙስናን ለመዋጋት የተጀመረውን ትግል ለማኮላሸት ረዥም ርቀት ሄደው ሲዶልቱ ትግሉ የሚከሽፍበትን መንገድ ሲያሰሉ ቆይተዋል፡፡ በየስፍራው ከጀርባ ሁከት አቀጣጣይ ኃይል ሰላም አደፍራሽ ሁነው እስከመሰለፍ ተራምደዋል፡፡ ያልተረዱት ነገር ቢኖር መንግሰትና ሕዝብ መልካም አስተዳደር ለማስፈን ሙስናን ለመዋጋት የሚያደርገውን ትግል የሚገታው ምንም ኃይል አለመኖሩን ነው፡፡
የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመንግስትም ሆነ ለሕዝቡ የሞት ሽረት ጥያቄ ነው፡፡ የሚዘነጋ፣ የሚታለፍ፣ የሚረሳ አጀንዳ አይደለም፡፡ ዛሬም ወደፊትም መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚደረገው ትግል ተጠናክሮና ጎልብቶ በየደረጃው ይቀጥላል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በብዙ መልኩ የሚገለፅ ውስብስብ ባሕርይ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ደረጃ በደረጃ ነቅሶ ለማስወገድ ሰፊ ትግል ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ትግሉ በመንግስትና በሕዝብ የጋራ ተሳትፎ ብቻ ነው ሊሰምር የሚችለው፡፡
በመንግስት በኩል የተጀመረው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ምሁራን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛው፣ ወጣቱና ሴቶች ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ የጉዳዩ ክብደት ከፍተኛ የመሆኑን ያህል በመንግስት እንቅስቃሴ ብቻ ውጤታማ ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልምና፡፡
ይህንን ሀገራዊ ችግር ለመፍታት የሚቻለው ሕብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ቆሞ በሚያደርገው ሰፊ ርብርብ ብቻ ነው፡፡ መብቱን የሚጠይቅ፣ መብቱን የሚያስከብር፣ ለሕግና ስርአት መከበር በጽኑ የሚቆም ሕብረተሰብ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግርን የማይሸከም፣ የሚያጋልጥና ለሕግ የሚያቀርብ መሆን መቻል አለበት፡፡
ችግሮችን አይቶና ተመልክቶ የማያልፍ፤ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ መፍትሔ የሚያስገኝ እየሆነ ሲመጣ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በሂደትም ሙሉ በሙሉ እየከሰመ እንዲመጣ ለማድረግ ይቻላል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግርና በዚሁ መነሻነት የሚከሰቱት ፈርጀ ብዙ ችግሮች በአንድ ጀንበር በአንድ አመት የሚቀረፉ አይደሉም፡፡ ትግሉ ቢጀመርም የተራዘመ ጊዜያትን ይጠይቃል፡፡ በሕብረሰተቡ ውስጥ ሰፊ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት መስራት ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ስራ የሲቪክ ማህበራት የሙያ ማሕበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች የየራሳቸውን ሀገራዊ ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሰሞኑን በመቀሌ እየተካሄደ ባለው ሰባተኛው የሕወሀት ኮንፈረንስ ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አጽንኦት ሰጥተው የመልካም አስተዳደር ዋነኛ ጠንቅ የሆነውን ኪራይ ሰብሳቢነት በመለየትና ጠራርገን በማስወገድ አሁን የተጀመረውን ትግል በየአካባቢው ለማስቀጠል መረባረብ ይገባል በማለት የገለጹትም የችግሩን ግዝፈትና ክብደት ብቻ ሳይሆን የመንግስት ቁርጠኝነትንም ጭምር ያመለክታል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን ኢሕአዴግ የሚታየውን ችግር በጥልቀት ፈትሾ መፍትሔ ካላስቀመጠለት የድርጅቱ መስመርና የመለስ ውርስ መቀጠል አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ስርዓቱ ወደ ከፋ አለመረጋጋት እንደሚገባ በመገንዘብ በጥልቀት የመታደስ ትግሉን በማቀጣጠል ረገድ በተለይም የፖለቲካዊ አመራርን በመፈተሽ ረገድ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን ገልጸው የተጀመረው እንቅስቃሴ የተወሰነ ለውጥ ቢያመጣም መሰረታዊ ለውጥ ግን ሊያመጣ አልቻለም ብለዋል፡፡ ለዚህ ነው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመታገል ረገድ ሰፊ ትግል መንግስትና ሕብረተሰቡ በጋራ ማድረግ የሚገባቸው፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ከሚደረገው በሀገር አቀፍ ደረጀ ከተጀመረው ትግል ጋር በተያያዘ በክልሎችም ሰፊ ትግል እየተደረገ ይገኛል፡፡ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) የሕብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ያላቸውን የ17 አመራሮች ሽግሽግ ባለፈው ሳምንት ማድረጉም ለዚሁ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ለጀመረው ትግል እየሰፋ መሄድ ማሳያ ነው፡፡
የሊጉ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ያሲን ሁሴን ለመገናኛ ብዙሀን እንደገለጹት የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ሕብረተሰቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ በሕዝብ ተሳትፎ በየፈርጁ የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድርጅቱን ስኬት ወደ ኋላ ሊቀለብሱ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር የወለዳቸው እንቅፋቶች መስተዋል በመጀመራቸው ድርጅቱ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል፡፡ ከልማቱ ጋር እያደገ የመጣውን የሕብረተሰቡን ጥያቄ ለማስተናገድ የሚያስችለውን ግምገማ አድርጎ በየደረጃው ከፍተኛ ትግልን የሚሹ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ከነመፍትሄዎቻቸው ተለይተው የእርምት እርምጃ የተወሰደው የተሻለ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ አመራሮቹ የችግሮቻችን ሁሉ ቁንጮ የሆነውን መልካም አስተዳደር፤ እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነትና መሰል ችግሮችን ትኩረት ሰጥተው መዋጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡