Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መቼ ነው፣ የቢሊዮን ብሮችን ከንቱ ብክነት የምናስቆመው? ወይስ በራሱ እድል ይስተካከላል?

0 555

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

Written by  ዮሃንስ ሰ

.የመንግስት ፕሮጀክቶችና ቢዝነሶች በከንቱ የሚያባክኑት ሃብት፣ አገርን ያቃወሰ ችግር ነው ይላል – የኢህአዴግ መግለጫ።
.ከዚያስ? በፌደራል ብቻ ሳይሆን፣ በየክልሉም የመንግስት ቢዝነሶችና ፕሮጀክቶች እንደሚስፋፉም እቅዱን ገልጿል – ራሱ ኢህአዴግ።
.የእስከዛሬው የሃብት ብክነት መፍትሄ ሳያገኝ፣ ለሌሎች በርካታ የሃብት ብክነቶች አዲስ እቅድ ማውጣት ምን ይባላል?
.ወይስ፣ ሃብት ብናባክን፣ በራሱ እድል ሃብት ይፈጠራል? ያለማቋረጥ ስናደፈርስ፣ በራሱ እድል ይጠራል? ይሄ አያስኖርም።
.ለ6 ቢሊዮን ብር ብክነት መፍትሄ ሳይበጅለት፣ በ6 ሚሊዮን ብር ብክነት ላይ ለወጉ ማምረርና ሆይሆይታ መፍጠር!
.ወይስ በሰበቡ ሽኩቻና ቀውስን ማጋጋል እንጂ፣ መፍትሄ ማበጀት የለብንም? የሃብት ብክነት፣ በእድሉ መፍትሄ ያገኛል?

የመንግስት ቢዝነስ ማለት፣ ብክነትና ሙስና እንደሆነ የሚገባን መቼ ነው? የፓርላማ አባላት… ሁሉም ባይሆኑም፣ በርካታ የፓርላማ አባላት… “3ሺ ኩንታል ስኳር በብልሽት ከጥቅም ውጭ ሆኖ ተቀብሯል” ተብሎ ሲነገራቸው፣… እጅግ አማርረዋል – የንገብገብ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ለነገሩ፣ ከፓርላማ ውጭም፣ በየአቅጣጫው ለሁለት ለሦስት ቀን፣ ሰሞነኛ የሆይሆይታ ማገዶ ሆኗል – የ6 ሚሊዮን ብር ስኳር ቅሌት። “ኧረ ጉድ!… አገር ቀለጠች፣ ሰማይ ተደፈነ” ተብሏል።
ምን ይሻላል? ወገኛ ትዕይንቶች የበዙበት አገር ሆነን ቀረንኮ። የፓርላማ አባላት፣ የፓርቲያቸውን… የኢህአዴግን አዲስ መግለጫ በቅጡ ቢያዩትኮ… ወደፊትም የቢሊዮን ብሮች የሃብት ብክነት እንደሚቀጥልና መፍትሄ እንደማያገኝ ማወቅ በቻሉ ነበር። ቢዝነስን ለዜጎችና ለግል ድርጅቶች ከመተው ይልቅ፣ የመንግስት ቢዝነሶችና ፕሮጀክቶች በየክልሉም ይስፋፋሉ ብሏል – ኢህአዴግ። ያው የቢሊዮን ብሮች ብክነትም ይስፋፋል ማለት ነው። እስከ መቼ? አገሬው እስኪራቆትና የሚባክን ሃብት እስክናጣ ድረስ?
በእርግጥ፣ ይሄኛው የ6 ሚሊዮን ብር ብክነት፣ ቀላል ቅሌትና ብክነት ነው ማለቴ አይደለም። ግን፣… በሺ እጥፍ የሚበልጡ በርካታ ግዙፍ ብክነቶች በየዓመቱ በግላጭ እየታዩ፣… ለብክነት እንግዳ የሆንን የማስመሰልና ራሳችንን የማታለል ድራማ ብንሰራ ምን ፋይዳ አለው? በድራማ ብክነት መፍትሄ አያገኝም።
ደግሞም፣ ሌላውን ግዙፍ ብክነት በሙሉ ትተን፣ ይህችኛዋን ብክነት ብቻ ማስተካከል አይቻልም። ለወግ ያህል፣ የድራማ ያህል እንቁጠረውና ለአንድ ቀን እናጫጩህ፣  ካላልን በስተቀር ማለቴ ነው። በእርግጥ፣ ወገኛ ተውኔት፣ ብዙም ጥረት ስለማያስፈልገው… ሊማርከን፣ ለጊዜውም ሊስበንና ሊያታልለን ይችላል። ቁምነገር የሰራን እየመሰለንና እያስመሰልን፣ ራሳችንን እየዋሸን ሌሎችንም እንድናታልል ሊገፋፋን ይችላል። ነገር ግን፣ ያዛልቃል ወይ ነው ጥያቄው?
ዋናውን የኑሮ መድረክ እያናጋንና እያተራመስን፣ ግን ደግሞ ያደፈረስነውን ነገር በቅጡ ከማየት እየሸሸን፣… አገሬውን ሁሉ እያዝረከረክነው እንደሆነ ላለማየት ዓይናችንን እየጨፈንን፣… ካየንም እንዳላየን እያለፍን፣ … የወኞች ተውኔት ውስጥ መርመሰመስና መቅበዘበዝ ያዋጣናል?
እንደ ቀልድና ጨዋታ… እንዳሻን ነጋ ጠባ እያናጋን የምናተራምሰውን፣… ቀን ከሌት እንደዘበት የምናዝረከርከውን ነገር ሁሉ፣ ማን ያስተካክለው? የፓርላማ አባላት በወዲያኛው ሰሞን፣ ለዚህ ነበር አድማ ያደረጉት? ያው፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ፓርላማ ተገኝተው የጥያቄ ምላሽ ካልሰጡ፣ መደበኛ የፓርላማ ስራ አናካሂድም ብለው ስራ የማቆም አድማ ያደረጉት። የ6 ሚሊዮን ብር ብክነት ላይ የቀረበው ሪፖርትም፣ በርካታ የፓርላማ አባላትን እንዳስጮኸ ተነግሮናል። ፓርላማው አሪፍ ፓርላማ መሆን ጀመረ እንዴ ልትሉ ትችላላችሁ። ግን…
… እንግዲህ… የሃብት ብክነትን ከምር የሚቆጣጠሩ፣ የመንግስት ስራ አስፈፃሚ ባለስልጣናት ላይ… ጠቅላይ ሚኒስትሩም ላይ ጭምር በትጋት ክትትል የሚያካሂዱና ለስልጡን ፓለቲካ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የፓርላማ አባላት ቢበራከቱ መልካም ነው። ግን፣ አሁን እየሆነ ያለው ነገር፣… በፓርላማም ሆነ በጠቅላላ በአገሪቱ እየተበራከተ ያለው የፖለቲካ አይነት፣… ከዚህ ይለያል። ወደ ስልጡን ፖለቲካ የሚያደርስ የመሻሻል ለውጥ አይደለም እያየን ያለነው።
የሁሉም አባላት ባይሆንም፣ የበርካታዎቹ አባላት፣ የበርካታዎቹ ፖለቲከኞችና ምሁራን ሆይሆይታና እሪታ፣ አድማና አመፅ… በአብዛኛው አንድም ከየዋህነት፣ አልያም ከወገኛነት፣ ሲብስም የስልጣን ሽኩቻና የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ በዋና ተዋናይነት ባይሆን እንኳ በአጫፋሪነት የማጋጋልና በሆይሆይታ የማጦዝ ተሳታፊ እድምተኛ የመሆን ጉዳይ ይመስላል (ማለትም እንዲሁ ተሳታፊና እድምተኛ መሆን – ለማንገራገጭ፣ ለማደፍረስ ያህልም ቢሆን)።
ይህን የምለው ያለ መረጃ አይደለም።
ልድገመውና፣ የስኳር ብልሽት ቅሌትና የ6 ሚሊዮን ብር ከንቱ ብክነት፣ እንኳን በድሃዋ አገር በኢትዮጵያ ውስጥ ይቅርና፣ ሲንጋፖርና አሜሪካ ውስጥም ቢሆን፣ በመንግስት ሲባክን የሚያንገበግብ ጥፋት ነው።
ነገር ግን፣ በስንትና ስንት እጥፍ የሚበልጡ፣ በየጊዜው በሚፈለፈሉ የመንግስት ውሳኔዎችና ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ፓርላማው በሚያፀድቃቸው ህጎችና ፖሊሲዎች አማካኝነት የሚፈጠሩት ብክነቶችስ? እስቲ ሁለት ሦስቱን እንመልከት – ከትንሹ በመጀመር።

የ270 ሚሊዮን ብር ብክነት!
ረሃብ ባለበት አገር፣ በየአመቱ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ አንዳንዴም እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ገበሬዎች እርዳታ ጠባቂ በሚሆኑበት ድሃ አገር ውስጥ እየኖርን፣… “ማዳበሪያ” ላይ ቀልድና ጨዋታ ያስፈልጋል? እንዴትስ ይታሰባል? በመንግስት እቅድ መሰረትና ግፊት የተቋቋሙ “የማዳበሪያ ማቀላቀያ ድርጅቶች” ግን፣ ከዚህ የተለየ ትርጉም የላቸውም። የድርጅቶቹና የእቅዱ ነገር ኪራሳ እንጂ ጥቅም እንደሌለው የተገለጠላቸው፣… 140 ሚሊዮን ብር ወጪ ከባከነ በኋላ ነው። ድርጅቶቹ ያቀላቅሉታል ተብሎ የመጣው “ማዳበሪያም”፣ ከጥቅም ውጭ ሆኗል – ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ቢወጣበትም። በአጠቃላይ ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መሆኑ ነው።
የፓርላማ አባላት ይህንን አያውቁም? ሌላውስ ሰው? ሌሎች ባለስልጣናት፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ተቃዋሚዎችስ? እንዲያውም፣ ለማወቅ የሚፈልግና ደንታ ያለው ማንም ሰው፣ ይህንን መረጃ ማወቅ ይችላል። በሚስጥር የተደበቀ መረጃ አይደለም።

የ9 ቢሊዮን ብር ብክነት!
በመንግስት በጀት የተጀመረው ትልቁ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ደግሞ አለ – የባሰበት የቅሌት ፕሮጀክት! ፕሮጀክቱ፣ ከኪሳራ የዘለለ ውጤት እንደሌለው በግልፅ የታወቀው ዛሬ ሳይሆን ከአመታት በፊት ነው። 9 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተጀመረው የመንግስት ፋብሪካ፣ ለአመታት ዘግይቷል። ግን ገና ለበርካታ አመታት ይጓተታል። ትርፍ ሊኖረው ይቅርና፣ የብድር ወለድ ለመክፈል የሚችልም አይመስልም። የግንባታ ወጪው ከእጥፍ በላይ ወደ 18 ቢሊዮን ብር ይደርሳል ተብሏል።
በግል ኩባንያ ላይ የተወሰነ ጭማሪ… ለምሳሌ 20% ያህል ተጨማሪ የግንባታ ወጪ ከተከሰተ፣ “በሙስና ያስጠረጥራል” ብሎ የሚያስር መንግስት፤ 100% ያህል የ9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የግንባታ ወጪ ሲያባክን ምን ማለት ነው? ቢያንስ ቢያንስ 6 ቢሊዮን ብር በከንቱ እንደባከነ ማን ይክዳል?
ታዲያ ይህንን የሚያውቁና ሁነኛ መፍትሄ ለማበጀት ሲጥሩ የማይታዩ የፓርላማ አባላት፣ 6 ሚሊዮን ብር ባከነ ብለው አገር ምድሩን ቢቀውጡ ምን ይባላል? በሺ እጥፍ የሚበልጠውን የ6 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ለመፍታት ሲታትሩ ማየት አልነበረብንም?
በሌላ አነጋገር፣ “መንግስት የገባበት የቢዝነስ ፕሮጀክትም ሆነ ፋብሪካ፣ የድሃ አገር ሃብትን እንደሚያባክን አውቀው፣… መንግስት ወደ ቢዝነስ እንዳይገባ በመምከር በተቻለ መጠን ለመቀነስ፣ ቀስ በቀስም ወደ ግል ይዞታ እየሸጠና ከቢዝነስ እየወጣ፣ የሃብት ብክነትን ቀስ በቀስ እያስወገደ፣… በምትኩ፣ ሃብትና የስራ እድል ፈጣሪዎች የሚበራከቱበት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን እንዲያስፋፋ መንግስትን መወትወት!” ማለቴ ነው።
ይህንን ሁነኛ መፍትሄ የሚያቀርቡና ለማስረዳት ድምፃቸውን የሚያሰሙና የሚጣጣሩ የፓርላማ አባላትን አይተናል?… አላየንም። ይሄ ይሄ፣ ቁምነገር ነው – ወገኛ ተውኔት፣ አድማ፣ ሽኩቻ፣ ትርምስና አመፅ አያስፈልገውም። የምር መፍትሄ ከተፈለገ።
ግን፣ አሁን አሁን፣ ስለ መፍትሄ በቁምነገር ጠንቅቆ የማሰብ ነገር፣ እየተረሳ ነው። እና፣… ችግሮች፣ በራሳቸው እድል መፍትሄ ያገኛሉ?
በቃ፣ ከኛ የሚጠበቀው፣ በየጊዜው ለወግ ያህል፣ “ኧረ ጉድ፣ ኧረ አገር ቀለጠች” የሚል ሆይሆይታና ሽኩቻ፣ አድማና ግርግር ብቻ ነው? ማደፍረስ ብቻ? ስናደፈርስ፣ በራሱ ጊዜ ይጠራል? አይጠራም። በራሱ መንገድ አይስተካከልም፤ በእድሉ መፍትሄ አያገኝም።

የ6 ቢሊዮን ብር ሌላ ብክነት! የ10 ቢሊዮን ብር የነፋስ ተርባይን ብክነቶችን ትተን!
በፌደራል የውሃ ስራዎች ድርጅት እና በየክልሉ በተቋቋሙ ተመሳሳይ የመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት የሚከናወኑ የግድብና የመስኖ ግንባታዎችንም ማየት ይቻላል – ብረታብረት ኮርፖሬሽን ከሚሰራቸው ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ማለት ነው። ለምሳሌ፣ የከሰም ተንዳሆ ፕሮጀክትን በተመለከተ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በነሐሴ 2003 ዓ.ም የታተመውን ዘገባ ተመልከቱ።
ከ2 ቢሊዮን ብር ባነሰ ወጪ፣ በ1999 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ በመንግስት የተጀመረው ፕሮጀክት፣ በየዓመቱ “ዘንድሮ ይጠናቀቃል” እየተባለ ተጨማሪ በጀት እየተጨመረለትና በፓርላማ እየፀደቀ፣ ብዙ ሃብት እየባከነ እንደሆነ የሚገልፅ ዘገባ ነበር – ያኔ ከዛሬ 7 ዓመት በፊት የወጣው ዘገባ። በዚያ አላቆመም።
የሃብት ብክነቱ፣ ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንደሆነም፣ በተከታታይ በታተሙ የአዲስ አድማስ ዘገባዎች ተገልጿል። በ1999 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት፣ እስከ 2009 ድረስ በጀት እየተመደበለት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ አልፈጀም? የፓርላማ አባላት ይህንን አያውቁም? የዚህ ተሳታፊ አይደሉም ለማለትስ ይቻላል? በየአመቱ የሚመደበው ተጨማሪ በጀት በፓርላማ ነው የሚፀድቀው።
“ኧረ ይሄ ነገር፣ እንዴት ነው?” ብሎ ጥያቄ በማቅረብ፣ ለሁነኛ መፍትሄ ጥረት ያደረገ የፓርላማ አባል ስንት ነው? በሆይሆይታ አዳራሹን ይቀውጡ ወይም አድማ ያድርጉ ማለቴ አይደለም። ያማ መፍትሄ አይደለም። ወገኛ ተውኔት ነው።
እንዲያው፣… የድራማ ማዳመቂያ፣ የሽኩቻ ማመካኛ እናድርገው ብለን ቁማር ካልተጫወትንበት በስተቀር፣… “በአንድ ስብሰባ አይደለም፣ በአንድና በሁለት አመትም”… በአንዳች ተዓምር የሃብት ብክነትን መፍታት አይቻልም። የይስሙላ “መፍትሄ” መሳይ ወገኛ ተውኔት ሳይሆን፣… የምር፣ ሁነኛ መፍትሄ ማለቴ ነው – ለዘለቄታው የሚበጅ። ማለትም፣… በየአቅጣጫው እየተንደረደረ ወደ ቢዝነስ የመግባት ሱስ የያዘውን መንግስት ትንሽ እንዲረጋጋና ፍሬን እንዲይዝ፣… ቀስ በቀስም ከቢዝነስ እንዲወጣ፣… ያለመታከት ለበርካታ ዓመታት በትኩረትና በትጋት መስራት ማለቴ ነው።
አዎ፣ ይሄ ዓመታትን የሚፈጅ ብርቱ ጥረት፣ ሁነኛ መፍትሄ ቢሆንም፣… ሆይሆይታና ግርግር ለመፍጠር የሚያመች ነገር አይደለም። ሌላ ሁነኛ መፍትሄ ደግሞ የለም። ወይስ፣… ሁነኛ መፍትሄውን ትተን፣… የሃብት ብክነትን መጫወቻ እናድገው? የፖለቲካ ጩኸት የምናማሙቅበት መቆመሪያ፣ መሻኮቻና መበሻሸቂያ፣ ማጋጋያና ጠልፎ መጣያ፣ የሹምሽር ማመካኛና የአመፅ ማቀጣጠያ ብቻ እንዲሆንልን እናድርገው? ከዚያስ? በአንዳች ተዓምር፣ በራሱ እድል፣ በራሱ ጊዜ… የመንግስት ፕሮጀክትና ቢዝነስ፣ ሃብት ማባከኑን እርም ብሎ ያቆማል? እንደዚያ ይመስላል የአገራችን ፖለቲካ! ቢሆን ነው።
የፓርላማ አባላት፣ በፌደራልም ሆነ በየክልሉ የሚገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎችና ፓለቲከኞች፣… ምሁራንና ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚዎችና ሌሎች ዜጎች፣… በመንግስት ፕሮጀክቶች ሳቢያ፣ በየአመቱ የብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት እየባከነ እንደሆነ አያውቁም? …አይናቸውን ካልጨፈኑ በቀር፣ አይተው እንዳላዩ ካልካዱ በቀር በግልፅ ማወቅ ይችላሉ።
ግን፣ ስለሁነኛ መፍትሄ አስቦ፣ ሃሳቡን ለማስረዳት ስንቱ ይጥራል? ኧረ ምን በወጣቸው? በቃ የሚጠበቅብን፣ በዚህም በዚያም ብለን የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ማዳመቂያ ማድረግ አልያም በተቃራኒው ማጦዝ፣ ኢህአዴግን ለማንገራገጭና መንግስትን ለማናጋት መሟሟት ብቻ? ስልጣን ላይ ሆኖ በብክነት ጎዳና መቀጠል ወይም አመፅና ትርምስን ማባባስ ብቻ? ስናባክነው በራሱ ጊዜ ይካካሳል? ስናናጋው በራሱ እድል መልክ ይይዛል? ስናንገጫግጨው፣ በአንዳች ተዓምር ልክ ይገባል?

የብክነት መፍትሄ፣ ሌላ የብክነት እቅድ?
በኢህአዴግ መግለጫ ከተነሱት 8 ነጥቦች መካከል አንዱ፣ በመንግስት ፕሮጀክቶች አማካኝነት የሚከሰተው  የሃብት ብክነት ነው። የፕሮጀክቶቹን ችግር አጥንቶ የሚያስተካከል ኮሚቴ እንደተቋቋመም ተነግሯል። ግን፣ ስለ ሁነኛ መፍትሄ እየተናገረ ነው ብላችሁ አታስቡ። እስከዛሬ እንደተደረገው፣ እዚህና እዚያ አንዳንድ ጊዜያዊ ማስታገሻ ውሳኔዎችን በመተግበር፣ እዚህና እዚያም አንዳንድ ሃላፊዎችንና ባለስልጣናትን በማባረር ጭዳ ከማድረግ የዘለለ “መፍትሄ” ለማበጀት ያሰበ አይመስልም – ኢህአዴግ።
የቢሊዮን ብር ሃብት የሚባክነው፣… መንግስት ያለቦታው በቢዝነስ ስራ ውስጥ በመግባቱ እንደሆነ ከምር ለማመን አልፈለገም – ኢህአዴግ።
የመንግስት ቢዝነስ ለኪሳራ፣ ለሙስናና ለብክነት እጅጉን የተጋለጠ እንደሆነ ኢህአዴግ መቼም አምኖ አያውቅም ማለት አይደለም። በፖሊሲ ሰነዶቹ ውስጥ፣ አልፎ አልፎ በፅሁፍ አስፍሯል – የመንግስት ቢዝነስ ለውድቀት እንደሚዳርግ በመጥቀስ።
ነገር ግን፣… መንግስት ቢዝነስ ውስጥ መግባት አለበት የሚል የረዥም ጊዜ እምነቱን የሙጢኝ እንደያዘ እንደሚቀጥል፣ በተደጋጋሚ በብዙ ቦታ ገልጿል፣ የዘወትር ስለት አድርጎታል እንጂ። በአዲሱ መግለጫውም ውስጥ ሳይቀር!
በመንግስት ፕሮጀክቶች ሳቢያ የሚፈጠረው የሃብት ብክነት ትልቅ የአገር ችግር መሆኑን የሚጠቅስ መግለጫ፤ እዚያው በዚያው ምን ይላል? በፌደራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በየክልሉም የመንግስት ቢዝነሶችና ፕሮጀክቶች እንደሚስፋፉ ይገልጻል።
የእስከዛሬው የሃብት ብክነት መፍትሄ ሳያገኝ፣ ለሌላ የሃብት ብክነት እቅድ ማውጣት ምን ይባላል? እና በፌደራልና በክልል፣… የመንግስት ቢዝነስና ፕሮጀክት እንደአሸን እየፈላ፣ የሃብት ብክነት እየተባባሰ አገር ምድሩን ይበልጥ እንዲቃወስ የሚያደርግ ሌላ ጣጣ ጎትቶ ማምጣት እንደማለት ነው።
ብክነት ከተባባሰ በኋላ፣ ኢኮኖሚ ይባስ ከተቃሰ በኋላስ?… የተባባሰው ችግር፣ በእድሉ ይቃለላል? የተቃወሰው ኢኮኖሚ በራሱ ስውር እጅ ይቀናጃል?

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy