Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መግለጫው በተግባራዊ እርምጃ ይደገፍ

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መግለጫው በተግባራዊ እርምጃ ይደገፍ

ሰለሞን ሽፈራው

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የነደፈው የጥልቅ ተሃድሶ መርሃ ግብር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥልቀት እየጨመረ ስለመምጣቱ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ በተለይም ደግሞ ካለፈው ታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት አንሰቶ የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ 15 ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የቆየው የጥልቅ ግምገማ መድረክ መጠናቀቁን ተከትሎ፤ ቅዳሜ ታህሳስ 21 ቀን 2010ዓ.ም የወጣው የአቋም መግለጫ፤በጥልቀት የመታደሱ መርሐ ግብር ሀገራችን አሁን ላይ የምትገኝበትን አሳሳቢ ፓለቲካዊ ቀውስ ለመቀልበስ ወደሚያስችል ጥንካሬ መሸጋገሩን የሚያመላክት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እንዲሁም ከታህሳስ 21 ቀኑ መግለጫ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ዙሪያ የሚያጠነጥን ወቅታዊ ቃለ ምልልስ የሰጡት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ሰሞነኛው ግምገማ በእርግጥም የተለየ የፓለቲካዊ ቁርጠኝነትን የጠየቀ ስፋትና ጥልቀት የተስተዋለበት ውጤታማ መድረክ እንደነበር አስምረውበታል፡፡ በግንባሩ ከፍተኛ የአመራር አካላት መካከል ይስተዋል የነበረውን የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማጣት ችግር ሊያስቀር የሚችል የጋራ መግባባት ላይ እንደተደረሰም ነው ሊቃነ መናብርቱ የገለፁት፡፡

ከዚህ የተነሳ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ያካሄደው የጥልቅ ግምገማ መድረክ፤ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች “ከፀሐይ በታች” ያሉ የጋራ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያለ ገደብ ተነጋግረው በአመራሩ መካከል ምንም ዓይነት የዕርስ በርስ መጠራጠር ስሜትን ሊፈጥር የሚችል ብዥታ እንዳይኖር የሚያደርግ ጤናማ የጋራ ግንዛቤ ከተጨበጠበት ሰፊ ውይይት በኋላ ወደ አስተማማኝ ቁመና መደረሱንም ጭምር ነው ሊቃነመናብርቱ በአንድነት ያስረዱት፡፡ ስለሆነም ለ 15 ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥልቅ ግምገማ፤ በእርግጥም የጥልቀት ተሃድሶውን መርሃ ግብር ወደ ላቀ ጥልቀት ያሸጋገረ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የተቻለበት ነው የሚለውን ጉዳይ አምኖ የማይቀበል አካል ያለ አይመስልም፡፡ አሁን ከየአቅጣጫው ጎላ ባለመልኩ የሚደመጠው አስተያየት በሰሞነኛው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጥልቅ ግምገማ መድረክ ላይ ተመክሮ ተዘክሮባቸው ለሀገራችን ወቅታዊ ችግሮች መፍሔነት ይበጃሉ በሚል የጋራ አቋም የተያዘባቸውን የስምምነት ነጥቦች በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲለወጡ ማድረግ ይገባልና መንግስት ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይጀምር የሚል ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ከታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት አንስቶ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ሲያካሂድ በየቆው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥልቅ ግምገማ ላይ እየተነሱ በጥልቀት ከተፈተሹ በኋላ የጋራ አቋም የተያዘባቸው የመፍትሔ ሃሳብ ማመላከቻ ነጥቦች፤ እጅግ ጠቃሚ ቁም ነገር ያዘሉ የመሆናቸውን ያህል ቶሎ ተግባራዊ መደረግ ይኖርባቸዋል መባሉ የሚደገፍ እንጂ የሚነቀፍ ጉዳይ አይደለም፡፡

ምክንያቱም፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር አንቅልፍ እየነሳን ያለውን ፈርጀ ብዙ ወቅታዊ ችግር ያስከተለው በተለይም የኢህአዴግ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች የአመራር አካላት ዕርስ በርሳቸው ተናበው ለመስራት እንዳይችሉና ይልቁንም አንዱ ሌላውን በስጋት ዓይን እያየ ጠልፎ ለመጣል ሲቃጣው እንዲስተዋል ያደረገ አሉታዊ ግንኙነት ስለነበራቸው ነው ከተባለ ዘንዳ፤ ይህን አደገኛ አዝማሚያ ለማባባስ ያለመ በሚመስል የቅንነት ማጣት ችግር ምክንያት የየራሳቸውን ነገር የማወሳሰብ ፓለቲካዊ ሴራ ከማውጠንጠን የማይቦዝኑ ቡድኖች ላይ ተግባራዊ የእርምት እርምጃ ቶሎ ካልተወሰደ በስተቀር፤ ውሳኔውን የሚቀለብስ ደባ ላለመፈፀሙ እርግጠኛ መሆን እንደሚያዳግት ብንጠረጥር አይፈረደብንም፡፡ ስለዚህ እኔ ራሴም ብሆን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጥልቅ ተሃድሶው ንቅናቄ መድረክ ትርጉም ወዳለው ጥልቀት የመሸጋገሩን እውነታ ባሳየ መልኩ ያካሄደው ሰሞነኛ ግምገማው ላይ፤ ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በግልፅ ተወያይተውና ተደማምጠውም ጭምር አስተማማኝ የጋራ አቋም እየያዙ ስለመውጣታቸው የተገለፀበትን አግባብ ከልብ የሚደገፍ የእውነተኛ ተራማጅ ታጋዮች ህዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሰ ሆኖ እንዳገኘሁት እየጠቆምኩ፤ ግን ደግሞ ይህ ሀገር ለማዳን ያለመ ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት አሁኑኑ ወደታች ወርዶ መተግበር እንዲችል የማድረግ ጉዳይ እጅጉን አንገብጋቢ አጀንዳ ነው የሚለውን የበርካታ ዜጎች አስተያየት እንደምጋራ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ከዚህ መሰረተ ሃሳብ በሚመነጭ ቅን ስጋት “የከፍተኛ አመራር አካላቱ በዚህን ያህል ጥልቀት ዕርስ በርሳቸው ተገማግመውና ተወያይተው ሀገሪቷን ለገጠማት ፓለቲካዊ ቀውስ፤ እንዲሁም ደግሞ ቀውሱ ላስከተለው ፈርጀ ብዙ ጉዳት ሳይቀር ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ የሚያመለክት የጋራ አቋም መግለጫ መስጠታቸው፤ ምናልባትም በኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ያልተለመደና የመጀመሪያው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይሄው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሁሉንም የገዢው ፓርቲ የአመራር አካላት በሚያካትት ተመሳሳይ ግምገማ አማካኝነት መላውን የግንባሩ ፓለቲካዊ ቁመና በደንብ የመፈተሽና የማጥራቱ ተግባር አሁኑኑ እንዲጀመር ማድረግ ካልተቻለ ህዝቡ ላይ ያጠላውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት መቀልበስ ያዳግታል” ሲሉ የሚደመጡ ወገኖች የሚሰነዝሩትን ምክር አዘል አስተያየት መቀበል ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ፡፡

ይሄን ስልም ደግሞ፤ከላይ ያለው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና እንዲሁም የኢፌዴሪ መንግስት ከፍተኛ የአመራር አካል በአሁኑ የጥልቅ ግምገማ መድረክ ሂደት አማካኝነት መፍጠር የቻለውን የአስተሳሰብ አንድነት፤ ወደታችኛው የግንባሩ አባል ድርጅቶች ፓለቲካዊ መዋቅር ወርዶ  ዕርስ በርስ የመተጋገል ተራማጅ አቋም በተጨባጭ ተግባር ሲገለፅ የሚታይበት ሀገራዊ መነቃቃት እንዲቀጣጠል ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው በጥገኛ ሃይሎች ፈርጀ ብዙ ደባ ምክንያት ደብዝዘው የቆዩትን የጋራ አስተሳሰብ ልዕልናችን መገለጫ እሴቶች ከጥፋት አደጋ መታደግ የሚቻለው ማለቴ ነው፡፡ ስለሆነም እንደኔ እንደኔ፤ ሀገራችን ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉት አሳሳቢ ችግሮች ለሚጠይቁት ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚመጥን ጥልቀት የታየበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞነኛው ጥልቅ ግምገማ፤ በየትኛውም መልኩ ሲመዘን፤ የፌደራል ስርዓቱ ላይ የተጋረጠበትን የቅልበሳ አደጋ ለማስቀረት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የተጨበጠበት እጅግ በጣም ጠቃሚ መድረክ ተደርጎ ይወሰድ ዘንድ ግድ ነው፡፡ ይህ  የማይካድ የግምገማው ጠቃሚ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የመድረኩን በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎ የወጣውን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫና እንዲሁም የአራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ወቅታዊ የጋራ ማብራሪያ የተተነተነው፤ ንድፈ ሃሳባዊ ቁመና ወደ መሬት ወርዶ ተግባር ላይ ሲውል ምን ይመስላል? እውን ለ15 ተከታታይ ቀናት ሲካሔድ የሰነበተው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ መድረክ ላይ የተደረገው የዕርስ በርስ መተጋገል ሁሉንም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት በእኩል የሀገራዊ ሃላፊነት ስሜት ድክመቶቻቸውን እንዲያዩና እንዲቀበሉም ጭምር ስለማድረጉ የተነገረንን አምነን እንፅናና ይሆን? ወዘተ የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ለሚደመጡ ወገኖች የሚያጠግብ ምላሽ የሚሰጥ ተግባራዊ የእርምት እርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነት ፈፅሞ ቸል ሊባል የማይገባው መሰረታዊ የጋራ ጉዳያችን ነው እላለሁ እኔ በበኩሌ፡፡

ይሄን ጥርጣሬ አዘል የግል እይታየን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት ገና ከወዲሁ ልብ እንዲሉልኝ በአፅንኦት ላስገነዝብ መገደዴም ያለ ምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቅስ ቀድሞውንም ቢሆን፤ እቺን ሀገር ከድህነትና ከሁዋላ ቀርነት ድቅድቅ ጨለማ የሚያወጣ ነው ብለው ከልብ ለሚያምኑበት ለኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር በመታመን ረገድ፤ የተመሰገኑ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የአመራር አካላት፤ አበክረው የቆሙለት መሰረታዊ የጋራ ዓላማ እንዲዘነጋ በሚያደርግ ጥቃቅን ሰበብ አስባብ እንዲቃቃሩና የትምክህት፤ ወይም ደግሞ የጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ አመለካከትን እንደ ጠቃሚ አቋም የመውሰድ አዝማሚያ የበላይነትን እየያዘ ለመጣበት፤ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማጣት ችግር እንዲጋለጡም ጭምር ምክንያት ስለሆነው መንስኤ የማውቀውን እውነት ከመናገር የቦዘንኩበት አጋጣሚ የለምና ነው፡፡ በግልፅ አነጋገር ‹‹የኢህአዴግ ማልያ ለብሶ የመጫወት ታክቲክ›› የሚል ዘመን አመጣሽ የተቃውሞው ጎራ ፅንፈኛ ቡድኖች ስርዓቱን ከውስጥ ሆኖ ለመገዝገዝ ያለመ ህቡዕ እንቅስቃሴ በሚካሔድበት አግባብ አማካኝነት፤ ከእያንዳንዱ የኢፌዴሪ መንግስት ከፍተኛ የአመራር አካል በስተጀርባ የማይፈፀም ፖለቲካዊ ደባ እንደማይኖር ስለሚታመንም ጭምር ነው ጉዳዩን በተለየ ጥንቃቄ መያዝ እንዳለብን የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ የሚጠበቅብን፡፡ አለበለዚያ ግን፤ አሁንም ለመላው የዚህች አገር ህዝቦች ዕርስ በርስ ተፈቃቅዶ፤ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ የመኖር ፅኑ መሰረት የተጣለበትን ህብረብሔራዊ ፌደራሊዝም ከሚፈታተኑት ተደጋጋሚ የቅልበሳ አደጋዎች በአስተማማኝ መልኩ እየታደግን፤ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የሚያስችለንን የአስተሳሰብ ልዕልና እንዳንቀዳጅ የሚሹት የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፓለቲካዊ አመለካከት አቀንቃኞቹ ተቃዋሚ ቡድኖች፤ ጥረታችንን ሁሉ፤ እነርሱ “የኢህአዴግን ማሊያ ለብሶ የመጫወት ታክቲክ ነው” ከሚሉት ፈሊጣቸው በሚመነጭ ቅንነት ማጣት ምክንያት ሊያወሳስቡት እንደማይችሉ ዋስትና የለንም፡፡      

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy