Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምና የጎሳ መሪዎች ሚና

0 282

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላምና የጎሳ መሪዎች ሚና

ዳዊት ምትኩ

በየአካባቢው የሚገኙ የጎሳ መሪዎች የሀገራቸውን ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ የጎላ ሚና አላቸው። የጎሳ መሪዎች በህዝቡ ውስጥ ተቀባይነት ያላቸው፣ በተለይ ወጣቶች የአካባቢያቸውን የጎሳ መሪዎች የሚሰሙና የሚቀበሉ በመሆናቸው በሰላሙ ሂደት ላይ እነዚህ ወጣቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። የጎሳ መሪዎች ተደማጭነት ያላቸው የእድሜ ባለፀጋዎች እንደመሆናቸው መጠን፤ በህይወት ዘመናቸው ያዩትንና የሰላምን ከፍተኛ እሴት ለወጣቶቹ በማካፈል ወጣቶች ስለ ሰላም በሚገባ እንዲገነዘቡ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የሰላም አለመኖር እንኳንስ የእድሜ ባለፀጋ ለሆኑት የጎሳ መሪዎች ቀርቶ ለማንኛውም ዜጋ ግልፅ ነው። ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ስለ ዴሞክራሲ ማበበብና ስለ ኢኮኖሚያዊ እድገት መናገር ጉንጭ አልፋ ከመሆኑም በላይ በአገራዊ ህልውናችን ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ይጥላል። በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል።

የሰላምና መረጋጋት እጦት ዕድገትን ያቀጭጫል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለሰላምና መረጋጋት በቂ ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጡን ከሚችሉ ጽንፈኛ ሃይሎች ራሱን መጠበቅም ይኖርበታል።

ፅንፈኛ ሃይሎቹ ዋነኛው ግባቸው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት እንዳይኖር፤ ህብረተሰቡ በሰላም ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ወዘተ ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ሺህ ዜጎች ሰርተው የሚያድሩበትን ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ልማቶች፣ የመንግስት ቢሮዎች፣ የግለሰብ ድርጅቶች፣ በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች፣ የህዝብ መገልገያ አምቡላንሶች እንዲወድሙ ሲሰሩ ተመልክተናል፡፡

የእነዚህ ሃይሎች እቅዳቸው ያተኮረው ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ማሰናከል፣ ማጥፋት በተለይም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችንም ማስቆም ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ለዚህ ድርጊታቸው በግንባር የተሰለፉ ሃይሎችን በፋይናንስ፣ በስልጠና፣ በስምሪትና በአማካሪነት በቅርብ የሚረዷቸው እንደ ኤርትራ ዓይነት የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ሁሌም የሚሰሩ ሀገሮች መሆናቸውንም እናስታውሳለን፡፡ ያ ሁሉ ተግባራቸውም አልፎ ዛሬ ለዘላቂ ሰላም በሚያበቃን ሰላምና መረጋጋት ውስጥ እንገኛለን፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት መርሁ ሰላም ነው። በዚህም ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን መሳብ ችላለች፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው።

ከዚህ አኳያ ባባፉት 26 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሆነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሀገራችን የሰላም ተምሳሌት ተብላ ስትጠቀስ ኖራለች። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ ለልማት አብረውን እየተረባረቡ ነው።

የኢትዮጵያ ሰላም ላለፉት 26 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ እንደ ደንቡሽት ቤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈራርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው። ይህም ወደ ሀገራችን መምጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች አስተማማኝ ዋስትናን ይሰጣል።

አገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው። ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋሞች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ አገር እንደምትሆን ሲተነብዩ መጥተዋል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በሀገራችን የልማት ግስጋሴ ውስጥ ትርጉም የሌለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን የሚያሳይ ነው።

እርግጥ ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም ሊባል አይቻልም። ይሁንና ችግሩ ከመንግስትና ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን አይደለም።

በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና በመስተካካል ላይ ያለ ጉዳይ ነው። የሰላም ማጣት ትንሽ ባይኖረውም፤ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ፣ ችግሩ ያስከተለው የልማት መስተጓጎል እዚህ ግባ ሊባል የሚችል ሊሆን አይችልም። በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም አለመኖር ምክንያት የደረሱ የሰው ህይወት ህልፈት፣ የንብረት ውድመት መፈናቀል እዚህ ላይ በእማኝነት ሊቀርብ የሚችል ነው።

እርግጥ ሰላም ከሌለ የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም። መብት አይከበርም። መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂት ጉልበተኞች ይሆናሉ። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል። በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች የሚወሰን ይሆናል።

ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል። ሃይል ያለው ሁሉ በህገ ወጥ መንገድ ሰላምን አስጠባቂ ነኝ ሊል ይችላል። ህዝቡ ከሁሉም ነገር በላይ ለአገራዊ ሰላምና መረጋጋት ህዝቡ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት አለበት። ለሰላምንና መረጋጋትን ቅድሚያ አጀንዳ ማድረግ ካልቻልን ምንም ዓይነት ውጤት ማግኘት አይቻልም። ይህን የሰላም እውነታ የጎሳ መሪዎች ለየአካባቢያቸው ወጣቶች ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy