Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰሞኑን በአስመራ ምን እየተዶለተ ነው?

0 1,032

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰሞኑን በአስመራ ምን እየተዶለተ ነው?

ሰለሞን ሽፈራው

እውነት ለመናገር የድህረ ነፃነቷ ኤርትራ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ህዝቦች ግንባር ቀደም የሀገራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ ሆና ትቀጥላለች የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡እንዴት ብትሉኝም በኛና በኤርትራውያኑ ወንድሞቻችን መካከል ለዘመናት የተገነባ ፈርጀ ብዙ ትስስር ከመኖሩ የተነሳ የሁለት ሉዓላዊ ሀገራት ህዝቦች እንደሆንን ተደርጎ መወሰዱ እንብዛም ትርጉም አይኖረውም የሚል ቅን ስሌት ከነበራቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች አንዱ ነኝና ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያ ቅን ሰሌቴ ስህተት እንደነበረ ከተዳሁ እነሆ አስራምናምን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ይህ ሊሆን ስለቻለበት መሰረታዊ ምክንያት የግል እይታየን መግለፅ ካለብኝም ደግሞ፤ ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የዕድሜ ልክ ፕሬዘዳንታዊ ስልጣን መታመንን የመረጠው ሻዕቢያ መራሹ የአስመራ ግፈኛ አገዛዝ፤ በዕልፍ አዕላፍ የኤርትራ ህዝብ ልጆች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ነፃነት ስለቀለደበት ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡

ለዚህ የግል አቋሜ እንደ ዋነኛ አሳማኝ ምሳሌ አድርጌ ላነሳው የምፈልገው የመከራከሪያ ነጥብም፤ ኤርትራውያን ለድፍን 30 ዓመታት ከተካሄደው እጅጉን ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የተቀዳጁትን ነፃነት ገና በቅጡ ሳያጣጥሙት፤ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ዕብሪተኛነት ወዳስከተለው ሌላ ዙር የጦርነት እሳት እየተማገዱ የሻዕቢያ መራሹን ነውጠኛ መንግስት ጠብ አጫሪ ፓሊሲ ማስፈፀሚያ ሲሆኑ የታዘብንበትን አሳዛኝ እውነታ ይሆናል፡፡ ይህን ስልም፤ የአስመራው አምባገነናዊ ስርዓት ገና ኤርትራ ነፃነቷን እንዳገኘች የሚያወሳው ዜና በተሰማ ማግስት ከሱዳን እስከየመን፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ እስከ ጅቡቲ ድረስ ያሉትን ጎረቤት ሀገራት በመደዳ እየወረረ የድንበር ይገባኛል ጥያቄን በማሳበብ የጫረውን የጦርነት እሳትና በቀጣናው ወንድማማች ህዝቦች ላይ ያስከተለውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ማስታወስ ብቻ ይበቃል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ በተለይም የአቶ ኢሳያስን ገደብ የለሽ እብሪተኝነት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ጭምር የታዘበበት እንደነበር በሚነገርለት የሻዕቢያ አመራር ማን አለብኝነት ምክንያት፤ የጎረቤት ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የጣሰ ድንገተኛ ወረራ ማካሄዳቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የድንበር ጦርነት፤ የሁለቱንም ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች ፈፅሞ ያልተጠበቀና ምናልባትም አምኖ ለመቀበል የሚያዳግት ጭምር ዋጋ ያስከፈለ ፈርጀ ብዙ ኪሳራ ላይ ጥሏቸው ስለማለፉ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

እናም ያ በድህረ ነፃነቷ ኤርትራ መንግስት ማን አለብኝ ባይነት ምክንያት የተፈፀመብንን ወረራ ለመቀልበስ ሲባል ያልተጠበቀ ጦርነት ውስጥ ለመግባት የተገደድንበት ክስተት በኢትዮጵያ አሸናፊነት እልባት ካገኘ ከአስር ዓመት በላይ ቢሆንም ቅሉ፤ የአስመራው ማፍያ ስርዓት ሽንፈቱን ተቀብሎ ከመቀመጥ ይልቅ ሀገራችንን በእጅ አዙር ጦርነት ለማተራመስ ያለመ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀሱን ስለቀጠለ፤ ግንባር ቀደም የደህንነት ስጋት ምንጭ ሆኖብን መቆየቱ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህ የተነሳም እንደቀልድ ተቀስቅሶ የኢትዮ ኤርትራን ወንድማማች ህዝቦች እጅጉን የሚዘገንን የህይወትና የንብረት ኪሳራ ወዳስከተለ የሞት ሽረት ውጊያ ሲያመራ የተስተዋለው የድንበር ጦርነት እንደቆመ ከተነገረን አስራ አምስት ያህል ዓመታት ቢቆጠሩም፤ የአስመራው ግፈኛ አገዛዝ የፊት ለፊት ሽንፈቱን የተበቀለ እየመሰለው፤ ሀገራችንን በአንድ ወይም ደግሞ በሌላ መልኩ የማተራመስ ሙከራ የሚያደርግበትን የመንግስታዊ ሽብርተኝነት ተግባር ለመፈፀምና ለማስፈፀም ከመንቀሳቀስ ቦዝኖ እንደማያውቅ ነው ምንጮች የሚያመለክቱት፡፡ ለአብነት ያህልም፤ በኢፌዴሪ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብለው ከተፈረጁ በርካታ ዓመታት ያስቆጠሩትን እንደ ኦ.ነ.ግ.፣ ኦ.ብ.ነ.ግ. እና ግንቦት ሰባት ዓይነቶቹን ፅንፈኛ ፓለቲካዊ አቋም በማራመድ የሚታወቁ ተቃዋሚዎች ጨምሮ፤ ማንኛውንም ፀረ ኢትዮጵያ ሃይል ወደ አስመራ እየጠሩ አሰልጥነውና አስታጥቀው እኛን እንደ ሀገር ሰላም ለመንሳት ያለመ ዕኩይ ተልዕኳቸውን የሚያሳካ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሰማሩበት ስትራቴጂ መኖሩን ድፍን የዓለም ማህበረሰብም ጭምር ይመሰክራል፡፡

ምንም እንኳን ግፈኛው የሻዕቢያ አመራር ከኤርትራ ህዝብ ጉሮሮ ላይ እየቀማ ቀለብ በሚሰፍርላቸው ጉዳይ አስፈፃሚዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ ጥረት የማድረጉን ያህል ተሳክቶለታል የሚያሰኝ ጉዳት ያስከተለበት ሁኔታ አለመስተዋሉ ባይካድም፤ ግን ደግሞ ከእያንዳንዷ የሀገራችንን ሰላም ለማናጋት ሲባል የምትደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ በስተጀርባ የአስመራው መንግስት ጣልቃ ገብነት ይኖራል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይሄ ሁሉ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ፀረ አትዮጵያ አቋም የወለደው ትንኮሳ የሚገለፅበት ተደጋጋሚ የጠብ አጫሪነት ድርጊት ተደማምሮ የድህረ ነፃነቷ ኤርትራ ለመላው የሃገራችን ህዝቦች ቁጥር አንድ የደህንነት ስጋት ምንጭ እንድትሆን አድርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሻዕቢያ መራሹ የጦረኝነት አባዜ የተጠናወተው የዚያች አገር መንግስት ለሌሎች ፀረ ኢትዮጵያ የውጭ ሃይሎች በጉዳይ አስፈፃሚነት ሲያገለግል የሚስተዋልበት አግባብ እንዳለ ይታወቃል፡፡ በተለይም ደግሞ የኛ ዕድገትና ብልፅና ከማያስደስታቸው እንደ ግብፅ ካሉት የዓረቡ ዓለም አንዳንድ ሀገራት ጋር በመሞዳሞድ ረገድ የሚታወቁት የሻዕቢያ መሪዎች፤ ለካይሮ ፖለቲከኞች ፀረ ኢትዮጵያ ማስፈፀሚያ ከመሆን ወደኋላ አይሉም ነው የሚባለው፡፡ ከዚህ የተነሳም ይመስላል የግብፅ መንግስታት ሀገራችን ላይ አንዳች አሉታዊ ተፅእኖ ለማሳደር ያለመ ዕክል የመፍጠር ፍላጎት ሲኖራቸው የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ኤርትራ እንደዋነኛ ጉዳይ አስፈፃሚ ሀገር ሊጠቀሙባት ሲሞክሩ የሚስተዋሉት፡፡ እንግዲያውስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግብፅ ወታደሮቿን ወደ ጎረቤት ኤርትራ አስገብታ ሁለቱ ሀገራት እንብዛም ያልተለመደ ሊባል የሚችል ይፋዊ የጦር ሰራዊት ቅንጅት የመፍጠር አዝማሚያ እያሳዩ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ሰሞነኛ መረጃዎች ከወደ አስመራ እየወጡ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረትም ግብፃውያኑ ወታደሮች ‹‹ሳዋ›› እየተባለ  ወደሚጠራው የሻዕቢያ መንግስት የጦር ሰራዊትን ማሰልጠኛ ተቋም  ስለመግባታቸው ነው የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች አክለው የዘገቡት፡፡ ይሕ የሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ እንቅስቃሴም ጭምር የታገዘ ጉድኝት ያሳሰበው የሱዳን መንግስት ከኤርትራ ጋር የሚያዋስኑትን ድንበሮቹን ለመዝጋት እንደተገደደም ምንጮቹ ያመለክታሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰሞኑን ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ካይሮ ተጉዘው ከግብፅ አቻቸው ጋር ያውም ኤርትራን በማይመለከታት የዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት ግንኙነት ጉዳይ ዙሪያ እንደተወያዩም ታውቋል፡፡ ስለዚህም ነው እኔ ሰሞኑን በአስመራ ምን እየተዶለተ ነው? የሚል ጥያቄ አነሳ ዘንድ መገደዴ፡፡ ምክንያትም ደግሞ ይሄው በግብፅና በኤርትራ መንግስታት መካከል ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የተጠናከረ ወታደራዊ የጋራ ዝግጅት የማድረግ ትብብር እየተስተዋለ ስለመሆኑ የሚያመለክተው ወቅታዊ መረጃ ከማንም በላይ ሊያሳስበን የሚገባው እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦችን ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለይም  ወደ ኤርትራ እንዲገባና ከሻዕቢያ ሰራዊት ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ እንዲያሟላ የተደረገው የግብፅ ወታደራዊ ሃይል በከፍተኛ ደረጃ የጦር መሳሪያ ስለመታጠቁ ጉዳይ የታመኑ የመረጃ ምንጮችን ጠቅሰው በመዘገብ ላይ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን መኖራቸው ሲታይ፤ በእርግጥም ሰሞኑን አስመራ ውስጥ ምን እየተዶለተብን እንደሆነ አጥብቆ መጠየቅን ግድ እንደሚል ነው ለኔ የሚሰማኝ፡፡

ምክንያቱም፤ይህ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፤ እጅጉን ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጂአ ፖለቲካዊ እውነታ ያለው ስለመሆኑ ጉዳይ ለመረዳት ያን ያህልም ምርምር የሚያሻው አይደለምና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ እንደ ሻዕቢያ መራሿ ኤርትራ ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚመጣ ፀረ ኢትዮጵያ የውጭ ሃይል፤ በሩን ከፍቶና እጁን ዘርግቶ የሚቀበል ጎረቤት ሀገር ሲኖር ጉዳዩ የሞት ሽረት ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ የህልውና ጉዳይ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂን የዕድሜ ልክ ስልጣን ለማስቀጠል ሲባል በፈረደባቸው የኤርትራ ህዝብ ልጆች ህይወት መቀለድን እንደ ‹‹አዋጭ የፖለቲካ ባህል›› የቆጠረው የሚመስለው ሻዕቢያ መራሹ ግፈኛ አገዛዝ አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አካባቢውን ወደለየለት የጦርነት ቀጣናነት የሚያስገባ ዕብሪቱን ለማሳየት እየተዘጋጀ ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለን? ለሚለው የበርካታ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ወቅታዊ ጥያቄ የሚያጠግብ ምላሽ መስጠት ከባለድርሻ የኢፌዴሪ መንግስት አካላት ዘንድ ይጠበቃል፡፡

በእርግጥም የአሁኑ የግብፅና የኤርትራ መንግስታት የሁለትዮሽ ወታደራዊ ሽርክና እየተገለፀበት ያለው አጠቃላይ ቅኝት፤ ከኢትዮጵያ ይቅልቅ ሱዳን ላይ ነው ያነጣጠረው የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ የሚደመጡ የፓለቲካ ተንታኞች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ለአብነት ያህልም፤ አንድ መሐሪ የተባሉ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካዊ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፤ ከሰሞኑ ሁኔታውን በቅርበት ለመከታተል ወደ ባድመ ተጉዘው በነበረበት አጋጣሚ ለመገናኛ ብዙሃን ሰዎች የሰጡትን የስልክ ማብራሪያ ስለመስማቴ ማስታወስ ይቻላል፡፡ እናም እርሳቸው እዚህ መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኝ አንድ ኤፍ .ኤም ሬዲዮ ጣቢያ በሰጡት የስልክ ቃለ ምልልስ ላይ እንዳብራሩት ከሆነ “ግብፅ በከፍተኛ ትጥቅና ስንቅ የታገዘ ወታደራዊ ሃይል ወደ ኤርትራ ምድር የመላኳ ጉዳይ እውነትነት እንዳለው ባያጠራጥርም፤ ግን ደግሞ ዝግጅቱ ከኢትዮያ ጋር ለሚደረግ የቀጥታ ጦርነት ነው? ወይስ ሱዳንን በመውረር ለኛ የምታሳየውን የልማት አጋርነት አቋም ለማስቀየር? ለሚለው ጥያቄ አሁን ላይ ቁርጥ ያለ ምላሽ ማግኘት ይከብዳል” ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ የዘርፉ ምሁራንም እንዲሁ ከመቐለ ዩኒቨርስቲው የፓለቲካ ተንታኝ ጋር እንደሚስማሙ የሚያመለክት ትዝታቸውን በመግለፅ ላይ ስለመሆናቸው ነው ሰሞነኛ ዜናዎች የሚጠቁሙት፡፡

ከዚሁ የግብፅ መንግስት ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮቹን ወደ ጎረቤት ኤርትራ ምድር ስለመላኩ ከሚያትተው የሰሞኑ አነጋጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚነሳው ሌላ ተያያዥ ነጥብም ደግሞ፤ አንዳንድ የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ጭምር አስመራና ካይሮ ከተሻረኩበት ፓለቲካዊ ጉድኝት በስተጀርባ መኖራቸውን የሚያሳይ አዝማሚያ አለ የሚል ነው፡፡ በግልፅ አነጋገር፤ የገልፍ ሀገራት ተብለው የሚታወቁትን የዓረብ ባህረ ሰላጤ ባለ ፀጋ መንግስታት ያካተተ ጂኦ.ፓለቲካዊ የሃይል አሰላለፍ ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ብርቱ ሽኩቻና የጥሎ ማለፍ እሽቅድምድም እየተስተዋለ ነው ብለን ብናጠቃልል ስህተት እንደማይሆን መረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ የተነሳም፤በሻዕቢያ መራሹ የአስመራ አገዛዝ ፊታውራሪነት እየተቀነባበረ ያለው የእብሪት ጦርነት የመቀስቀስ ሴራ፤ ዋነኛዋ ኢላማ ኢትዮጵያም ሆነቺ ሱዳን ለውጥ እንደማያመጣ ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለዚህም እንደኔ እንደኔ የኢትዮ ሱዳን መንግስታት ይሄን አደገኛ አዝማሚያ ያገናዘበ ሁለንተናዊ የትብብር ማዕቀፍ ይኖራቸው ዘንድ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፡፡አሁን ላይ ኤርትራ ውስጥ የሚገኘው የግብፅ ወታደራዊ ሃይል ከሻዕቢያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅቶ ስለሚያደርገው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተሟላ መረጃ ማሰባሰብን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከዚያች ጎረቤት ሀገር ጋር የሚዋሰኑባትን እያንዳንዷን የድንበር አካባቢ በንቃትና በብቃት ከመጠበቅ አኳያ መወሰድ ያለበትን የጥንቃቄ እርምጃ የመውሰድ ጉዳይ ፈፅሞ ቸል ሊባል የማይገባው ስለመሆኑ የጋራ ግንዛቤ ከመጨበጥ ውጭ ሌላ አማራጭ መፍትሔ አይኖርም የሚል ነው የኔ አስተያየት ሲጠቃለል፡፡ በተረፈ ግን የሰይጣን እግሩ ተሰብሮ የጦርነት ስጋታችን ሳይሰምር ይቀር ዘንድ  ልባዊ ምኞቴን እነሆ በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ መዓሰላማት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy