Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሲጨፍሩና ሲያጫፍሩ የነበሩ ወደየት ይሆኑ?

0 512

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሲጨፍሩና ሲያጫፍሩ የነበሩ ወደየት ይሆኑ?

ወንድይራድ ኃብተየስ

ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን  በማንኛውም  ነገር  የአገራቸውን  ጥቅም ያስጠብቃል  ያሉትን አቋም እንደሚይዙ ታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን  በተመለከተ  የሚያራምዱትን  ሃሳብ   መመልከት  ተገቢ ነው። የግብጽ  ፖለቲከኞችና ምሁራን የአገራቸውን  የተውገረገረ  አቋም ህጋዊ ለማድረግ በጋራ ሲሯሯጡ በአንጻሩ ደግሞ የእኛው አገር  ጽንፈኛ ሃይሎች ለመናኛ የፖለቲካ ትርፍ የህዝባቸውንና  የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው ሰጥተው እንደነበር  የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።  

 

በተለይ ኦነግን የመሰሉት ፓርቲዎች ከአስመራ ካይሮ  ድረስ  በመጓዝ ከአንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን ጋር ግንባር ፈጥረው  የህዳሴ ግድብን ግንባታ  እንዴት ማደናቀፍ እንደሚቻል ሲመክሩና ሲያማክሩ፤ ሲጨፍሩና ሲያጫፍሩ እንደነበር የአደባባይ ሚስጢር ነው። የህዳሴውን ግድብ  እናፈርሰዋለን፤  ግንባታውን እንገታዋለን በማለት ለግብጻዊያን ሲምሉና ሲገዘቱ  ነበር። እነዚህ የእኛው አገር ጉዶች ዛሬ ላይ  የት ይሆኑ? ዛሬ ላይ ሲያሟርቱበት የነበረው ፕሮጀክት 63 በመቶ በላይ ደርሷል። በቅርቡም ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተገዕጿል። እነዚህ ጉዶች ምን ይውጣቸው ይሆን?  

 

ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች እና  አንዳንድ  ፓርቲዎች  መናኛ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለውጭ ሃይል  አሳልፈው እንደሰጡ በተግባር አሳይተዋል። እነዚህ ሃይላት  አገራቸውንና ህዝባቸውን ሸጠዋል፤ ክደዋል።  ማንም የፈለገውን አይዲዮሎጂ ሊያራምድ ይችላል።  ይሁንና በመሰረታዊ የአገራችን ጥቅም ልንደራደር አይገባም።  እነዚህ  ሃይሎች  አገርንና መንግስትን  ለይተው  መመልከት አልቻሉም። በየትኛውም የዐሰለም  አገራት  መንግስታትና ፓርቲዎች  ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ስርዓትም ይለወጣል፤ ነገር ግን አገርና ህዝብ  ቋሚ ናቸው። ሁሉንም በማጃመል፣ በዳበሳና በማጥላላት የፖለቲካ በሽታ  የተዘፈቁ አካላት ራሳቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል።  

 

በሁሉም ነገረ ከመንግስት አቋም በተቃራኒው  መሰለፍ የሚቀናቸው የእኛ አገር ጽንፈኛ ሃይሎች አገራዊ ጥቅምንና መንግስትን  መለየት ይኖርባቸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃብት ነው። የዚህን  ግድብ  ህልውና  የሚወስነው  የኢትዮጵያ  ህዝቦች ብቻ ናቸው።  ይህ ግድብ  ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ በላይ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  የአብሮነትና የአንድነት ማሳያ ፕሮጀክት ነው።  ይህ ፕሮጀክት   ነገን የምናይበት፣  ይህ ትውልድ  ለቀጣዩ ትውልድ ሊያወርሰው የሚችለው አንድ ቋሚ  ሃብት ነው። ማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ  በዚህ ግድብ ላይ አሻራውን የማኖር  ዜጋዊ  ግዴታ አለበት። ይሁንና  አንዳንድ  ሃይሎች ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት  ከጽንፈኛ  የግብጽ ፖለቲከኞችና  ምሁራን ጋር በማበር  የአገራቸውንና የህዝባቸውን ጥቅም  የሚጎዳ ተግባር ሲፈጽሙ ተመልክተናል። በዕውኑ አፍረንባቸዋል፤ አዝነንላቸዋልም። ምክንያቱም ነገ የታሪክ ተጠያቂዎች ናቸውና።  

 

ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 15 ዓመታት  ፈጣንና ተከታታይነት ያለው  ባለሁለት አሃዝ ኤኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ ላይ ነች። ይህም በመሆኑ አሁን ላይ  አገራችን ህዝቦቿን  ብቻ ሳይሆን  የአካባቢውን  አገራት ህዝቦች  ጭምር  ተጠቃሚ  የሚያደርጉ  ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ላይ ነች።   ለአብነት   ዘመናዊ የባብር ሃዲድ ዝርጋታ፣ የአውሮፕላን  በረራ፣  ትላልቅ የኤሌክትሪክ  ሃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታና  ሃይል ማስተላለፊያ  መስመር ዝርጋታ፣ ትላልቅ አውራጎዳናዎች ግንባታ ወዘተ በማካሄድ ላይ ነች። ከኢትዮጵያ የልማት ስራዎች ሁሉም የጎረቤት አገራት ህዝቦች በቀጥታ አሊያም  በተዘዋዋሪ  ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። ዛሬ ላይ አገራችን ወደ አንድ ሚሊዮን  የሚጣጋ  የጎረቤት አገራት ስደተኞችን አስጠልላለች።  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ለስደተኞች የሚችሉትን ነገር ሁሉ በማድረጋቸው   አገራችን በስደተኞች እንደሁለተኛ አገር እየተቆጠረች  ነው።

 

አንዳንድ  የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት  ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብም ኢትዮጵያ ለቀጠናው  አገራት ያበረከተችው ስጦታ አድርገው ይገልጹታል። ምክንያቱም የዚህ ግድብ ወጪ ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሆኖ ሳለ ሁሉም ጎረቤት አገራት በየደረጃው ተጠቃሚዎች ናቸው።  ኢትዮጵያ ደሃ ትሁን እንጂ  ጠንካራና ተባባሪ ህዝብ ያላት አገር ናት። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ደግሞ  ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር  የሚጠይቅ ፕሮጀክት በራስ ወጪ መሸፈን መቻሏ ነው።  አሜሪካን  የምታክል አገር  የሆቨር ግድብን ስትገነባ ወጪው  የተሸፈነው  በብድር  እንደሆነ  መረጃዎች ያመላክታሉ።  አገራችን ግን ይህን እድል ማግኘት ባለመቻሏ  የዚህን ግድብ ወጪ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመሸፈን  ተገዳለች። በእርግጥ ወጪው በራሳችን መሸፈኑ ያስገኘልን ጥቅሞች የሉም ማለት አይቻልም።  ለአብነት ወጪው ሙሉ በሙሉ በራሳችን ለመሸፈን መነሳታችን በህብረተሰባችን ውስጥ የእንችላለን ስሜት እንዲፈጠር አግዟል፤  እንዲሁም  ሁሉም ኢትዮጵያዊ  የራሱን አሻራ በግድቡ ላይ እንዲያኖር ዕድል በመፈጠሩ ፕሮጀክቱን የእኔነት ስሜት በሁሉም ዜጎች  ዘንድ እንዲፈጠር አግዟል።  

 

ታላቁ የኢትዮጵያ  የህዳሴ ግድብ   ከኢትዮጵያ  ባሻገር  ጎረቤት አገራትም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ  የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው።  እስካሁን ባለው ሁኔታ  ሱዳንና ጅቡቲ  ከኢትዮጵያ  ሃይል እያገኙ ሲሆን ኬንያና ደቡብ ሱዳን ደግሞ  በዝግጅት ላይ ናቸው።   ታላቁ  የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ሁሉም የጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ በቂ ሃይል የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚኖር መረዳት የሚከብድ አይደለም። ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለተፋሰሱ አገራት በተለይ  ለሱዳንና ለግብጽ ከሃይል አቅርቦት ባሻገር  ተጨማሪ ጥቅሞችን  ለአብነት  ከደለል ይታደጋቸዋል፣  ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ  ያግዛል፣ የውሃ ብክነትን ይከላከልላቸዋል።   

 

እንግዲህ የእኛዎቹ ጉዶች ይህን ፕሮጀክት ነው በመቃወም ላይ ያሉት። ሱዳናዊያኖች የኢትዮጵያ መንግስትን ከአካባቢው አገሮች ጋር አብሮ  የመልማት እቅድ አድንቀው የማይታጠፍ እጃቸውን ዘርግተዋል። የግብጽ መንግስት አንዴ መጣ አንዴ ደግሞ ሄድ እያለ ቢሆንም  እውነታውን  የማታ ማታ  መቀበሉ  አይቀርም። ይሁንና ማንም  ተመቸውም፣ ቆረቆረው፤ ተቀበለው፣ አልተቀበለው የህዳሴውን ግድብ ማንም ሊገታው እንደማይችል ግን በዕርግጠኝነት መናገር  ይቻላል።  ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደም ውስጥ ገብቷል።  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የትኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ ሃይል በሚፈጥሩት ወጀብ ከዓላማቸው ሊገታቸው እንደማይችል በተግባር አረጋግጠዋል።   

የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ  ያራምደው የነበረው “በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍተሃዊ የውሃ  ክፍፍል” የሚለው መርህ  አሁንም የአገራችን  ጠንካራ አቋም ነው። ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለሃይል ማመንጫነት እንጂ ለመስኖ አትጠቀምም፤  ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደሱዳንና ግብጽ  ሰፊ የመስኖ መሬት የሌላት ከመሆኑም በላይ የግድቡ ስፍራ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተጠጋ በመሆኑ  የህዳሴው ግድብ ለመስኖ ስራ እምብዛም የሚያገለግል አይደለም። ይህ ተጨባጭ እውነታ ነው፤  ኢትዮጵያም  በተደጋጋሚ አሳውቃለች። ሱዳን ከኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች በተለይ ከተከዜ የሃይል ማመንጫ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት  በመቻሏ  የኢትዮጵያ የልማት ስራዎች  አካባቢውን ሊጠቅሙ የሚችሉና የቀጠናውን  የኢኮኖሚ ትስስሩን የሚያሳድጉ መሆናቸውን በመረዳቷ  ለታላቁን የህዳሴ ግድብ  ፕሮጀክትም  ድጋፉን በተገኘው መደረክ ሁሉ  አረጋግጣለች። ይህ የሱዳን ህዝብና መንግስት አቋም እጅግ የሚደነቅ ተግባር ነው። ሱዳናዊያን እውነተኛ ጉርብትናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።

 

አሰዋን  ግድብ  ለግብጻዊያን  ከሚያስገኘው የኢኮኖሚ ፋይዳነት  ባሻገር  የአንድነታቸው ማስተሳሰሪያ እና የአገራቸው ህልውና  አድርገው  ይቆጥሩታል።   ለእኛም   ለኢትዮጵያዊያኖች  ታላቁ  የህዳሴ  ግድባችን  ከኤኮኖሚያዊ  ፋይደው ባለፈ  ለእኛ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች   የትብብራችን   ማሳያ እንዲሁም   የብሄራዊ  ኩራታችን  መገለጫና  የገጽታችን  መለውጪያ  ማሳያ  ነው።  በመሆኑም  ይህን ግድብ እውን እስኪሆን  ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ  እስካሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ  አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy