Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬትና ተግዳሮቶቻችን ሲፈተሹ

0 374

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬትና ተግዳሮቶቻችን ሲፈተሹ

 

አባ መላኩ

 

ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ገደማ በርካታ ቁም ነገሮች ገጥመዋታል። የኢፌዴሪ  መንግሥት መልካም አጋጣሚዎችን ብቻ ሳይሆን ተግዳሮቶችንም ወደ ስኬቶች መቀየር የቻለ ነው።  አብነቶችን እንጠቃቅስ። ጥቂቶችን ላነሳሳ። ከመልካሙ ልጀምር። ኢትዮጵያ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ መሠረታዊ ለውጦች ካሳየችባቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ነጻነትን ያረጋገጠ ህገ መንግሥት ማግኘቷ ነው።

 

ህገ መንግሥቱ ለአገራችን ህዝቦች ካስገኛቸው ጥቅሞች ቀዳሚው ፌዴራላዊ ሥርዓት እንድትከተል በማድረጉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብትን አጎናጽፏቸዋል። የፌዴራል ሥርዓቱ ህዝቦች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው እንዲተዳደሩ፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ህዝቡም በማንነቱ ኮርቷል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተረጋግጧል። በአገሪቱ  ዘላቂ ሠላም ሰፍኗል።  የህዝቦች አብሮነትና አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ ቆሟል። ህገ መንግሥቱም የቃል ኪዳን ሰነዳቸው ሆኗቸዋል።

 

የኢፌዴሪ  ህገ መንግሥት ለዘመናት በህዝቦች መካከል የነበረን የተዛባ አሠራርና አስተሳሰብ ማረም ችሏል። አገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን መተግበር ጀምራለች።  በርካታ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ህዝቦች ለመጀመሪያ  ጊዜ ድምጻቸውን ይበጀኛል ላሏቸው ተወካዮቻቸው መስጠት ችለዋል። አገሪቱ እስካሁን አምስት አገራዊ ምርጫዎችን በማድረግ ህዝቦች ይበጀኛል ይወክለኛል ለሚሉት አካል ድምጻቸውን መስጠት ችለዋል። የምርጫ ሥርዓቱ የየራሳቸው እጥረቶች ቢኖሩባቸውም  ሂደታቸው ግን  ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ ታይቶባቸዋል። በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ  የታጀቡም ነበሩ።      

 

ህገ መንግሥቱ የቆየውን የአገራችንን የተዛባ  አካሄድ እንዲስተካከል በማድረጉ በአገሪቱ ዘላቂና ዋስትና ያለው ሠላም ማስፈን ተችሏል። ይህም በመሆኑ አገሪቱ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አኃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ሌለኛው የኢትዮጵያ ትልቁ ስኬት ነው። አገሪቱ በፍጥነት በሚባል መልኩ ከድህነት መውጣት ጀምራለች። በእርግጥ አሁንም በርካታ ዜጎች በድህነት ውስጥ የሚኖር ቢሆንም መንግሥት በተከተለው ትክክለኛ  ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በርካታ ዜጎችን ከድህነት አላቋል።   የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ26 ዓመታት በፊት ከነበረበት ከአራት እጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል። በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተመጣጣኝ ዕድገት እንዲኖር መንግሥት ጠንክሮ ሰርቷል። ከምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል።    

 

ባለፉት 27 ዓመታት ገደማ ማህበራዊ መገልገያዎች ተስፋፍተዋል። በተለይም በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል። በተለይ ትምህርት ከፍተኛ  ለውጥ የታየበት ዘርፍ ነው።  በትምህርት ላይ ማለትም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ሰላሣ ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ። በፌዴራል መንግሥት ብቻ በዕትዕ ሁለት እየተገነቡ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ሳይጨምር አሁን ላይ ከ43 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ።  ዛሬ ላይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች በመረጡት የትምህርት መስክ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል። ለዚህም ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። በጤናው ረገድም ቢሆን በርካታ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የዞን ሆስፒታሎች፣ ሪፈራል ሆስፒታሎች፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተገንብተዋል።   

 

የአገራችን ስኬት የሆነውና ትኩረትን የሳበው ሌላው ጉዳይ በአገሪቱ በፍጥነት እያደገ የመጣው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው። አገሪቱ ፈርሳ እንደገና የምትገነባ እስክትመስል ድረስ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ግዙፍ ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

 

ለዚህ ጥሩ ማሣያ ተደርጋ የምትጠቀሰው መዲናችን – አዲስ አበባ ነች። አዲስ አበባ ፈርሳ የምትገነባ ከተማ ሆናለች። የቀድሞ ደሳሳ ቤቶች ፈራርሰዋል። በምትካቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ማህበራዊ መገልገያዎች፣ የንግድ ተቋማት ወዘተ … በመገንባት ላይ ናቸው። በአፍሪካ በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ረገድ እንደ ኢትዮጵያ ጥረት ያደረገ አንድም መንግሥት መጥቀስ አይቻልም። ይሁንና በአገሪቱ የግንባታው ዘርፍ ከዜሮ ሊባል ከሚችል ደረጃ የተነሳ በመሆኑ አሁንም የግንባታው ዘርፍ ብዙ ሥራን ይጠይቃል።     

 

በመሠረተ ልማት ግንባታ ማስፋፋት በተለይ በመንገድ  ረገድም ሌላው የአገሪቱ ትልቁ ሰኬት ነው። አገሪቱን ከጎረቤት አገራት የሚያገናኙ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች (ኤርፖርቶች) ወዘተ… በመሰራት ላይ ናቸው።  በመንገድ ደረጃ  አርሶና አርብቶ አደሩን ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ ቀበሌዎችን ከቀበሌዎች፣ ቀበሌዎችን ከወረዳዎች ወዘተ…የሚያገናኙ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ መንገዶች ተገንብተዋል። በከተሞች መሠረታዊ ለውጦች ተካሂደዋል። የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አብዛኛው ህዝብ የሚኖርበትን ገጠሩን ማዕከል ያደረገ ስለሆነ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በሁሉም አካባቢ እንዲኖር ተችሏል። መንግሥት የሃብት ክፍፍሉን ፍትሃዊ ለማድረግ በርካታ ሃብትን የሚያፈሰው መሠረተ ልማት በማስፋፋት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በመገንባት ነው።

 

በትምህርትም ሆነ በጤና አገልግሎት ዘርፎች ላይ የጥራት ችግሮች ቢኖሩም ባለፉት  ዓመታት አገሪቱ እነዚህን ዘርፎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ  ስኬታማ መሆን ችላለች። በሰው ሃብት ልማት ረገድ እነዚህ ሁለት ዘርፎች ያላቸው አስተዋጽኦ ወሣኝ በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኙ አድርጓል። በዚህም አሁን ላይ ብቻ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።    

 

በአገሪቱ የተረጋጋ ሠላም በመስፈኑ መንግሥት አገሪቱን ከድህነት ማውጣት የሚያስችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ለተግባራዊነታቸው እየተረባረበ ነው። ለአብነት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በተለይ ከታዳሽ የኃይል አቅርቦት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ረገድ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ ነው። እነዚህ ለአገራችን ሌላው ስኬቶች ናቸው።

 

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ከገጠሟት ተግዳሮቶች መካከል አንኳር የሆኑትን ደግሞ እንጠቃቅስ። ዋነኛው በ1983 ዓ.ም የአምባገነኑን ደርግ ሥርዓት ውድቀትን ተከትሎ በርካታ የታጠቁ አካላት አገሪቱን ለመቀራመት የተነሱበት ወቅት መሆኑ ነበር። በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች “እኛ እኩልነትንና ነጻነትን ፍለጋ  ትግል አደረግን እንጂ ለመለያየትና ለመበታተን አይደለም” በሚል አቋም ተነሳስተው አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአዲስ ቃል ኪዳን እውን አደረጉ። አገሪቱ ሳትበታተን፣ የህዝብ እልቂትም ሳይከሰት የአገሪቱ አንድነትን ማስጠበቅ ተቻለ። ይህ አገሪቱ  ከገጠሟት የከፉ አደጋዎች መካከል ቀዳሚው ነበር ማለት ይቻላል። ያ አስከፊ  ወቅት  አልፎ ዛሬ አገሪቱ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት የነገሰባት አገር ለመሆን በቃች።

 

ሌላው ፈታኝ ወቅት የነበረው የኤርትራ  ወረራ ወቅት ነበር። ከኤርትራ ወረራ ቀደም ባሉ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥት መንገድና ትምህርት ቤት ሲያስፋፋ፣ ድህነትን ለመቅረፍ ሲጣጣር የኤርትራ መንግሥት ግን የጦር መሣሪያዎችን ሲገዛና ወታደር ሲያሰለጥን ነበር ያሳለፈው። በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት ግምት የነበረው “ኢትዮጵያ ተከፋፍላለች፣ ሉዓላዊነቷን ማስከበር አትችልም” የሚል ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአምባገነኑን የኤርትራን ጦር ከመሸገበት ጠራርገው እንዲወጣ አድርገዋል። በዚህም በአጭር ጊዜ የአገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር  ወደ ልማት መመለስ ተችሏል። ያ ክፉ ወቅትም  በስኬት ተደምድሟል።

 

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ሌላው ለአገሪቱ ፈተና እንደነበር በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በአንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ በተፈጠረው የሥልጣን መባለግ ምክንያት በፓርቲው ውስጥ የመከፋፈል አደጋ ቢጋረጥም ፓርቲው ባዳበረው ጥልቅ ግምገማ የተበላሸ  አመራሩን በማስወገድ ኢሕአዴግ ራሱን አደሰ።  

 

ቀጥሎም ኢሕአዴግ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ በመገምገም አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነደፈ። አገሪቱም ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስመዝገብ ጀመረች።  ከዚያን ጊዜ አንስቶ አገሪቱ ባለሁለት አኃዝ ዕድገት በማስመዝገብ የህዝቦችን የቆየ የልማት ጥያቄዎች መመለስ ጀመረች። በዚህም አገሪቱ ዛሬ ላይ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት የዓለማችን አገራት ተርታ መሰለፍ በቃች።

 

ለኢትዮጵያ ፈታኝ የሆነው ሌላው ገጠመኝ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ የተነሳው ሁከት ነው። በወቅቱ ቅንጅት አጠቃላይ ምርጫውን ያሸነፍኩት እኔ ነኝ በሚል ያስነሳው ሁከት የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል፣ ንብረት አውድሟል። ይህም የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሂደት ከፉኛ ጎድቶታል። ያ ወቅት ብዙዎች ለአገሪቱ አስቸጋሪ ወቅት ነበር ብለው ቢገምቱም መንግሥት በብልሃትና አርቆ በማሰብ ሁኔታዎች እንዲበርዱና መልክ እንዲይዙ አድርጓል። መንግሥት በተከተለው የሰከነ አካሄድ ሁኔታዎች ተረጋግተው አገሪቱ የጀመረችውን ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስቀጠል ተችሏል።

 

ከባለፈው ዓመት  አንስቶ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ ሁከቶች ሌላው ለአገሪቱ መልካም ያልነበሩ ክስተቶች እንደነበሩ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁከቶች መሠረታቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢሆኑም አካሄዳቸው ግን ጽንፍ የረገጠ እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ ነገም የሚኖሩ መፍትሄም የሚሰጣቸው በሂደት እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። ከዚህም ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮች በነውጥና ሁከት ምላሽ ሊያገኙ አይችሉምና ልብ ሊባል ይገባዋል።   

 

የመልካም አስተዳዳር ችግሮች የአንድ ወቅት ክስተቶች አይደሉም። የዴሞክራሲ ባህላችን እየዳበረ  በሄደ ቁጥር  ጠያቂ ኅብረተሰብ ይፈጠራል፤  ጠያቂ ኅብረተሰብ ደግሞ  ትንሽም ቢሆን መብቱን  መስጠት አይፈልግም። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን በመቀራረብና በመነጋገር ብቻ ነው። በአገሪቱ የሠላማዊ ትግል ሜዳ ተመቻችቷል። ሆኖም የሠላማዊ ትግል ባህል መጎልበት ይቀረዋል።  ይህን  የሠላማዊ ትግል ባህልን ማጎልበት የኅብረተሰቡ ቀጣይ የቤት ሥራ መሆን አለበት። በየትኛውም መስፈርት ቢሆን በነውጥና በሁከት ወደ መንግሥት ሥልጣን መምጣት  አይቻልም። እንዲህ ያለ አካሄድን ህገ መንግሥቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግቶታል። የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት ወይም መፍትሄ ማፈላለግ የመንግሥት ኃላፊነት  አይደለም፤ የኅብረተሰቡም  ጭምር ነው። አሁንም መንግሥት  ከህዝቡ  የተነሱ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ እልባት በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ  መጎልበት እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት ይጠበቃል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy