Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሽግግር ከቃል ወደተግባር

0 325

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሽግግር ከቃል ወደተግባር

                                                            ስሜነህ

ባሳለፍናቸው 26 ዓመታት በሃገራችን የልማት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምኅዳር  በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ መሆኑ እሙን ነው። ይህ በሆነበት አግባብ ደግሞ ከ26 ዓመታት በኋላ አገሪቱን ቋፍ ላይ ያስቀመጡ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ችግሮቹን ለየት የሚያደርጋቸው እና አሳሳቢው ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱን ጥያቄ ውስጥ የከተቱና የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮች መሆናቸው ነው። በዚህም  ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚለው የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የግለሰቦች ግጭት የብሔር ገጽታ እየተላበሰ የዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ የነበረው ሰላምና መረጋጋት ደፍርሷል፡፡ በአገሪቱ ሕዝብ መካከል አንዳችም ዓይነት ቁርሾና ጥላቻ ሳይኖር፣ አገሪቱን ለውድመት ያጋለጡ አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ የወጣቱን ትውልድ መሠረታዊ ችግርች በመፍታት መረጋጋት ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮግራም ተነድፎ ወደተግባር ቢገባም፤ የበለጠ ትርምስ የሚፈጥሩ እንካ ሰላንቲያዎች በተፈለገው መጠንና ፍጥነት ሊቆሙ አልቻሉም።

ይህን እና መሰል ሃገሪቱን ቀውስ ውስጥ የከተቱ ጉዳዮችን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ 17 ቀናትን የፈጀ ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል፡፡ ስራአስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁምበአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን መፍጠሩንም አመልክቷል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝቦችና ለመላው የድርጅት አባላቱ የተላለፈ እንደሆነ የሚያስረዳው ይህ መግለጫ በድርጅታዊ ቋንቋ የታጨቀ፤ እንዲሁም ድርጅታዊ እና መንግስታዊ የአፈጻጸም ቅደም ተከተሎችን ያላብራራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በህዝቡ ዘንድ ብዥታ ተፈጥሯል። ስለሆነም በእነዚህ የውሳኔ አፈጻጸም ቅደም ተከተሎች እና መሰረተዊ በሆኑት የመግለጫው ነጥቦች ላይ መነጋገር እና እንደምታዎቹ ላይ መወያየት ተገቢ ይሆናል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፉት አስራ ሰባት ቀናት ባደረገው ግምገማ በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች፤ በተለይም በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደመጣ አረጋግጫለሁ ማለቱ የመጀመሪያውና አንድምታው ሊታይ የሚገባው የመግለጫው ዓብይ ነጥብ ነው። የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ማለት ከፍተኛ አመራሩ እንደግለሰብም ሆነ በመላው አባላት እና በግምባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ከዚህ ቀደም የነበረው መተጋገል በጸረ ዴሞክራሲ ሃይሎች ተጠልፎ ግለሰቦች ያሻቸውን የሚያነግሱበትና ከድርጅቱ መርህ ጋር የተሰለፉትን ወይም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ያልተሰለፉትን ታፔላ ለጥፈው የሚመቱበት፤ በዚህም ግንባሩ ህዝባዊነት አጥቶ የግለሰቦች መፈንጫ መሆኑን የሚያመለክትና ከዚህ ቅርቃር ለመውጣት አቋም መያዙን የሚያጠይቅ ጽንሰ ሃሳብ ነው። በሌላ መልኩ ሲታይ ደግሞ እነዚህ የድርጅት ካባ የለበሱ ፀረ ዴሞክራሲ ሃይሎች በየደረጃው የሚገኙትን የድርጅት መዋቅሮችና መድረኮች ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርባቸው የመታገያ መድረኮች እንዳይሆኑ በማድረግ በአመራሩ ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነትና ጥራት እንዳይፈጠር መሰናክል ሆነው መቆየታቸውን የሚያረጋግጥ ብቻ ሰዳይሆን እነዚህን ሃይሎች ቆርጦ በመጣል የሃሳብና የተግባር አንድነት መፍጠር የሚያስችልሥርአት መቀመሩን የሚያጠይቅ ነው፡፡ የነዚህ ሃይሎች ደባ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ሌላም መንግስታዊ ችግር ፈጥሯል። በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ደረጃ ከታየው የተዛባ የስልጣን አተያይና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የድርጅቱ አይነተኛ መለያ የሆነውን ዴሞክራስያዊነት በማዳካም ሳይወሰን ስልጣን የህዝብ መገልገያ እንዲሆን የተጀመረውን መልካም ጉዞ ለአደጋ ያጋለጠ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በዚህም ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ስልት ወደመሆን መሸጋገሩን የሚያጠይቀው መግለጫ ይህን የመሰለው በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርህ አልባ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹን የማዳከም ውጤት ማስከተሉንም ሥራ አስፈጻሚው ማመኑን ጠቁሟል። ይህ ደግሞ ኑዛዜ ሳይሆን አፈፃፀሙ በሂደት የሚሆን (የግምባሩን ጉባዔ፣ የየብሄራዊ ድርጅቶቹን እና የኢህአዴግን ማእከላዊ ኮሚቴ ውይይቶች) ተከትሎ በሚውሰዱ እርምጃዎች ብልሽቱ የሚጸዳ ይሆናል ማለት ነው።

ሁለተኛውና ከላይ ለተመለከተው ሃገራዊ ቀውስ በተዛባ መልኩ በምክንያትነት ሲወሳ የነበረው የፌደራላዊ ስርአቱ ነውና በዚህም ላይ ስራ አስፈጻሚው የደረሰበትን አቋም የተመለከተውን ነጥብ ማሄስ የመግለጫውን እንደምታ ለመገንዘብ ይጠቅማል። ይህን ጉዳይ ስናሄስ የፌደራላዊ ስርአቱን በራሱ የችግር ምንጭ ነው ብለው የሚከራከሩ ሃይሎችን ምልከታ ውድቅ አድርገን ነው። ምክንያቱም በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራላዊ ስርዓት መላ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት ያካሄዱት ትግል ውጤት ሥለሆነ፤ አነዲሁም አዲሲቱ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ህብረብሄራዊ አገር የምትለየው ብዝሃነትን በማወቅና በማክበር በመሆኑ ነው፡፡ ለ26 አመታት የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ እኩልነትን ማረጋገጡ እውነት ስለሆነ፤ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ካልሆነ በቀር በሌላ የማይተዳደሩበት ሁኔታ መፈጠሩም እውነት ስለሆነ፤ የፊዴራላዊ አስተዳደራዊ ስርአቱ ሁሉም በእኩልነትና በመተሳሰብ የሚሳተፍበትን ሁኔታም ስለተመቻቸ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ስርዓቱ ለበላይነትና የበታችነት የማይመች ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ በተግባርም እኩልነት እንጂ የባላይነትም ሆነ የበታችነት የማይፈጠርበት ስርዓት ተገንብቷል፡፡ ይህንን መሰረታዊ መርሆ የሚነካ ማንኛውም ዝንባሌ የበላይነትን በዘላቂነት ሊፈጥር የማይችልና ከመናቆር ውጭ ሌላ ውጤት የማያስገኝ እንደሚሆንም ሥለሚታመን ወዘተ ወዘተ።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከላይ በመነሻ ሂሳችን ላይ የተመለከትነው ሃይል እና የእርሱ ተከታዮች በአንድ ወይም በሌላ ብሔር ህዝብና ድርጅት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማርካት ይህንኑሥርአት በተዛባ መልኩ ትርጉም እየሰጡ በመናቆር ከላይ በመግቢያው ለተመለከተው ኪሳራ ዳርገውናል፡፡ ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ ያሉ ጥገኞችን ያለልዩነትና ማመንታት መታገል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል የሚለው የመግለጫው ነጥብ ከላይ ከውሥጠ ዴሞክራሲ እጦት ጋር ተያይዞ ከውሳኔ በተደረሰበት አግባብ እርምጃውን ለመከወን የሚያስችል የሃሳብና የተግባር አንድነት ተይዟል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ በድርጅቱ በተለይም ደግሞ በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ የታየው የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ችግር አደጋው በድርጅቱ ውስጥ ብቻ ታጥሮ የቀረ አይደለም፡፡ የህዝብ መብትን በማክበርና ተገቢውን ህጋዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታን ባለመወጣት ጭምር መገለጹ እሙን ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ዴሞክራሲያችንን በተለያዩ መንገዶች የማጥበብ አዝማሚያም ተስተውሏል፡፡ ህገ መንግስታዊ ስርአታችን ልዩ ልዩ ጥቅሞችና ፍላጎቶች እንዲሁም በእነዚህ ላይ የተመሰረቱ ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ፣ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ በቂና አስተማማኝ እድል ከፍቶ እያለ አመራሩ ዴሞክራሲውን የማስፋት ግዴታውን ባለመወጣቱ ችግሮችና ልዩነቶች በግጭት መንገድ የሚፈቱበት ሁነታ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ይህም ለሰላማችን መታወክ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረጉን ስራ አስፈጻሚው ተቀበለ ማለት ይህ እንዳይደገም የሃሳብ ስምምነት ላይ ደርሷል ማለት ብቻ ሳይሆን ከላይ በተመለከተው መልኩ የአፈጻጸሙን ሂደት ተከትሎ የተግባር አንድነቱን ያፀናል ማለት ነው።

ሌላውና ከላይ ለተመለከተው መቃወስ ይልቁንም እራሱ ገዥው ፓርቲም የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ለጥልቅ ተሃድሶ አበቁኝ ካላቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የሆነው የመድበለ ፓርቲ ስርአትና ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆነው የፓለቲካ ምህዳር ጉዳይ ነው።ስለሆነም በዚህም ላይ መግለጫውን ከሃሳብና ከተግባር አንድነት አኳያ ማሄስ ተገቢ ይሆናል።

በአገራችን እየተገነባ ያለው ህገመንግስትታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በፍላትና ጥቅሞች ብዝሃነት ላይ የተመሰረት መሆኑ ይታውቃል፡፡ ያም ሆኖ ከቅርብ አመታት ወዲህ የአስተሳሰብ ብዝሃነት በአግባቡ እንዲገለፅ የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ይህንን ችግር በጊዜና በአግባቡ ተገንዝቦ ማስተካከል የሚገባው ድርጅት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ያሳየው ዳተኝነት የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን ችግር እንዲገጥመዉ አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ጉዳይ ምንም እንኳ በአዋጅና በድርጅታችን በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የሚመሰረት ባይሆንም በዚህ ረገድ ድርጅቱ ሊወስደው ይገባ የነበረውን ርምጃ ከመውሰድ አንፃር ሰፊ ክፍተት እንደነበር ሥራ አስፈፃሚው መገንዘቡ እየተደረገ ካለው የፓርታዎች ድርድር ባሻገር ሌሎች እርምጃዎችንም ለመውሰድ የግንባሩ አባል ድርጅቶግ የሃሳብ አንድነት ላይ ደርሰዋል ማለት ነው።

ልክ እንደዴሞክራሲው ሁሉ በአገራችን የህልውና ጥያቄ የሆነውን መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴያችን በአመራር ድክመት ምክንያት ለበረካታ ችግሮች እንደተጋለጠ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዚህ ረገድ የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለማንገስና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳዳር ለመገንባት የሚያስችል የሃሳብም ሆነ የተግባር አንድነት ፈጥረናል ማለት ነው፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በቅን ልቦናና መንግስታዊ መመሪያዎችን በተከተለ አኳኋን ህዝቡን የሚያገለግሉና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡበት እድል ቀንሷል፡፡ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የህዝብ ምሬት ተፈጥሯል፡፡ ስራ አስፈፃሚው ይህ ችግር ከምንም ነገር በላይ በከፍተኛው አመራር ደረጃ በሚታይ ጉድለት ምክንያት የተፈጠረና የተባባሰ እንደሆነ አረርጋግጫለሁ ሲለን፤ የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት በመታየቱ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱና ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ሳይቻል መቆየቱን ሲነግረን፤ ዜገች በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መሆን በሚገባው ደረጃ ሳይፈፀም ቆይቷልም ሲለን፤ በተጨማሪም መንግስት የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጄክቶች ዙሪያ የሚታዩ የአፈፅፀምና የስነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት መታየቱን እና በዚህ የተነሳ አገራችንን በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ፤ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ሊያሰፉ የሚችሉ ፕሮጄክቶች፣ የጊዜ የዋጋ ንረትና የሃብት ብክነት የሚታይባቸው መሆናቸውን ሲነግረን፤ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እነዚህ የመልካም አስተዳዳር ችግሮች ህዝብና አገርን ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ እንደሆኑ በመገንዘብ በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ለማድረግ ጠፍቶበት የነበረው የሃሳብ አንድነት ላይ ደርሷል ማለት ነው። ይህን የሃሳብ አንድነት ወደተግባር አንድነት ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኑን ሲያጠይቅም፤ በዚህ ረገድ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር በተግባር ማቃለል ሲገባ ባጉል ተስፋና በባዶ ቃልኪዳን የመሸንገል ህዝበኛ አዝማሚያዎች በጥብቅ መመከት እንዳለባቸው በመወሰን ነው፡፡ ሌላው ሁሉ በሂደት የሚወገድና የነዚሁ ተቀጥላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተገባው ቃል ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ሲተረጎም የሚፈታ ስለሚሆን መግለጫውን በዚህ ሚዛን ብናሰላው ለሁላችንም ጠቃሚ ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy