Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀቢፀ-ተስፈኛው ፕሬዚዳንት(ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

0 569

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀቢፀ-ተስፈኛው ፕሬዚዳንት

                                                  ዘሩባቤል ማትያስ

(ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ የአቶ ኢሳያስን ሰሞነኛ መግለጫ መነሻ አድርጌ ሰውዬው ስለ ኢትዮጵያ ባሰሙት ዲስኩር ላይ ምላሽ ለመስጠት ሞክሬያለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ወዲ አፎም’ እንኳንስ ለኢትዮጵያዊያን አሳቢ ሊሆኑ ቀርቶ ‘ታግዬ ነፃ አወጣሁት’ ለሚሉት የራሳቸው ዜጋም የሚያስቡ አይደሉም። እንደሚታወቀው የአስመራው አስተዳደር ቀጣናውን በሽብር ተግባር የትርምስ አውድማ ለማድረግ ከሚጎነጉነው ሴራ ባሻገር፤ በሀገሩ ውስጥም “ነፃነት አምጥቼልሃለው” የሚለውን የራሱን ህዝብ እያተራመሰ መውጫና መግቢያ አሳጥቶታል። ኤርትራን እየመራ ያለውና ከስያሜው ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑ የሚታወቀው “ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ” (ህግደፍ) ባለፉት 26 ዓመታት ህዝቡን በጭቆና ሰቆቃና በአፈና ቀንበር ቁም ስቅሉን እያሳየው ይገኛል። ዛሬ የኤርትራ ህዝብ አቶ ኢሳያስን እንደ ጦር በመፍራትና መግቢያ እንጂ መውጫ ቀዳዳ የሌለውን የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገር እየተመመ ነው። አንዳንድ ፀሐፍት ይህን ወደ ጎረቤት ሀገሮችና በባህር ላይ ህይወቱን ሰውቶ እንደ ጎርፍ የሚፈሰውን ወንድም ህዝብ ስደት ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር እያዛመዱ “ዘፀአት” (Exodus) ይሉታል።

ሻዕቢያ በሀገሩ ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግና ከማስፋፋት ይልቅ መሳሪያ ገዝቶ አሊያም ከላኪዎቹ እየተቀበለ አሸባሪዎችን በማስታጠቅ እንደ ምርት ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመላክ ስራ ላይ የተጠመደ አስተዳደር ነው። በመሆኑም የሀገሩን ህዝብ ኑሮ መለወጥ የሚያስብበት ጊዜ የለውም። ይባስ ብሎም በህዝቡ ላይ የቋያ እሳትን በመለኮስና ስርዓቱን አስመልክቶ ትንፍሽ እንዳይል እግር ተወርች አስሮት አበሳውን ማብላት ስራዬ ብሎ ተያይዞታል።

የአስመራው ቡድን በመንግስትነት ራሱን ካደራጀበት ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በዜጎቹ ጉልበትና ዕውቀት እንዲሁም በሀገሩ ተፈጥሮአዊ ፀጋዎች ለማደግ ከማሰብ ይልቅ፤ በሌሎች ሀገራት አንጡራ ሃብት ላይ በጥገኝነት በመንጠላጠል ለመበልፀግ የሚፈልግ የቀቢፀ-ተስፈኞች ስብስብ ነው። ግና ዛሬ ድረስ ቀቢፀ-ተስፋው የሰመረለት አይመስልም።

በዚህም ሳቢያ በቅርቡ ኤርትራ ውስጥ የወጣውን “የቢሻ ወርቅ ማዕድን” የህግደፍ የኢኮኖሚ ጉዳዩች ኃላፊና የአቶ ኢሳያስ የእጅ ቦርሳ ያዥ በሆኑት እንዲሁም በቅፅል ስማቸው “ሓጎስ ኪሻ” እየተባሉ በሚጠሩት ሓጎስ ገ/ህይወት አማካኝነት ሲበዘብዝ ከርሟል። ይህ አልበቃ ብሎት የሀገሪቱን ወደብ በቀጣናው ላይ የራሳቸው ፍላጎት ላላቸው አረቦች ለ30 ዓመታት አከራይቷል። ሆኖም ከገንዘቡ ለህዝቡ ጠብ ያለለት ነገር የለም። የኤርትራ ህዝብ ከተፈጥሮ ፀጋዎቹ ሊጠቀም ቀርቶ በሻዕቢያ ምክንያት ውሎና አዳሩ በሰቀቀን የተሞላ፣ ህይወቱን ሸጦና ከሻዕቢያ ጦር ጥይት አምልጦ የጎረቤቶች ደጅ ጠኝና የባህር አዞዎች ሲሳይ እየሆነ ነው። እናም እንዲህ ዓይነቱ መሪ እንኳንስ ለኢትዮጵያዊያን ሊያስብ ቀርቶ የራሱን ከስደት ተራፊ ዜጋ በአግባቡ ቢመራ እሰየው ነበር። ማን ነበር—“ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” ያለው?…

የህልም ዓለም መንግስት አውራጅ የሆኑት አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ ችግር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ላይ የተቀመጠው አንቀፅ 39 ነው ለማለት እንኳን ትንሽ “ሼም” አልተሰማቸውም። በረሃ በነበሩበት ወቅት ከህወሓት ጋር በአንቀፅ 39 ሳቢያ ሲጨቃጨቁ እንደነበር የተናገሩትም ዓይናቸውን በጨው አጥበው ነው። ታዲያ ይህን እጅግ አስቂኝ ወሬ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ “ቀቢፀ-ተስፋ ሁለት” ብሎ እንደሚመዘግብልኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

ኤርትራ በአንድ ሰው የምትመራና ተቋማቶቿን ሁሉ አቶ ኢሳያስ የሚያዟቸው ሀገር ብቻ አይደለችም። በዚያች ሀገር ውስጥ ስለ ህገ መንግስት፣ ስለ ሰብዓዊ መብቶችና ስለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማሰብ በቅንጦትነት የሚታይ ነው። በአፍሪካ ውስጥ ብቸኛዋ ህገ መንግስት የሌላት ሀገር ኤርትራ ሳትሆን የምትቀር አይመስለኝም። የዚያች ትንሽ ሀገር ህገ መንግስት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው። መብት ሰጪውና ነሺው ርሳቸው ናቸው። በቃ በዚያች ሀገር ውስጥ ሌላ ማንም የለም። ‘ወዲ አፎም’ ራሳቸውን የዕድሜ ልክ ገዥ አድርገው ስለሚቆጥሩ የስልጣን ገደባቸው ህገ መንግስት በሚባል “መዘዘኛ ሰነድ” ውስጥ እንዲጠቀስባቸው አይፈልጉም። በዚህም ሳቢያ ህገ መንግስት የሚባለውን ሰነድ እንደ ተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ ይፈሩታል።

ምን ይህ ብቻ። ኤርትራዊያን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚባል ነገርን የሚሰሙት ከጎረቤቶቻቸው ነው። በሀገረ ኤርትራ ውስጥ ህገ መንግስት እንዲኖር የጠየቀ፣ ዴሞክራሲ እንዲኖር ያስጠየቀ አካል ‘ውርድ ከራሴ’ ነው ማለት ያለበት። መዘዙ የከፋ ነውና። ከዓመታት በፊት ህገ መንግስት እንዲኖር እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሰፍኑ የጠየቁና ራሳቸውን “ጉጅለ-15” (ቡድን-15) እያሉ የሚጠሩ የቀድሞ የህግደፍ ባለስልጣናትና አባላት ዘብጥያ ወርደው የአቶ ኢሳያስ የኮንቴይነር እስር ቤቶች ሲሳይ ሆነዋል። በየቀኑ በመስኮት በኩል አንድ ሻይና አንድ ዳቦ የሚቀርብላቸው እኚህ የነፃነት ታጋዩች፣ አንዳንዶቹም በህይወት እንዳይኖሩ የተደረጉ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ አካላቸው ጎድሎ በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ።

የዛሬ ሶስትና አራት ዓመት ገደማ በብርጋዲየር ጄኔራል ሳልህ ኦስማን የሚመራው የኤርትራ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር 12 ታንኮችን ይዞ ከባሬንቱ ግንባር ተነስቶ ፎርቶ እየተባለ የሚጠራውና የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚገኝበት ቦታን የተቆጣጠረው ኃይል፤ ማስታወቂያ ሚኒስቴሩን ከተቆጣጠረ በኋላ በቴሎቪዥን ለህዝቡ ከገለፃቸው ጉዳዩች ውስጥ የህገ መንግስት መኖር አለበት፣ የህዝቡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊገፈፉ አይገባም፣ በግፍ የታሰሩት የቀድሞ ታጋዮች መፈታት አለባቸው…ወዘተ. የሚሉ ጉዳዩች ተጠቃሽ ናቸው። ምንም እንኳን ይህ የእነ ብ/ጄኔራል ሳልህ ሙከራ በአቶ ኢሳያስ በተመሩ ሌሎች የሻዕቢያ ክፍለ ጦሮች አሻጥር ሳቢያ ቢከሽፍም ቅሉ፤ ክስተቱ ግን አቶ ኢሳያስ ህገ መንግስትን እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዴት እንደሚፈሯቸው የሚያመላክቱ ናቸው።

እናስ እንዲህ ዓይነቱ ህገ መንግስት የሌለውና ህገ መንግስት ጠያቂዎችን የሚገድልና የሚያስር አምባገነን እንደምን ስለ ኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለማውራት ሞራል ይኖረዋል?፣ እንዴት ዓይኑን በጨው አጥቦ ያለ አንዳች ሃፍረት አንቀፅ 39 ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ምክንያት ነው ይላል?…ህገ መንግስት ‘ቀይ ይሁን ጥቁር’ የማያውቅ ሰው እንደምን ስለ ህገ መንግስት ሊያወራ ይችላል?…እናስ አቶ ኢሳያስ የማያውቁት ሀገር እንዴት ይናፍቃቸዋል?…በእኔ እምነት ሰውዬው ስለ ኢትዮጵያ ህገ መንግስት ከማውራት ይልቅ “መጀመሪያ መቀመጫዬን” እንዳለችው እንስሳ ሀገራቸው ውስጥ እየተጠየቁ ያሉትን የህገ መንግስት መኖር ጥያቄ በአግባቡ ቢመልሱ በተገባ ነበር። የሰውዬው ልፈፋ ‘አልሞትኩም አለሁ’ ለማለት የተሰነዘረ ቢሆንም ቅሉ፤ ርሳቸው እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ስላሉበት የሀገራችን ህገ መንግስት ጥቂት ማውሳት ይገባል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙሉ ፈቃድና ይሁንታ የፀደቀው በወርሃ ህዳር 1987 ዓ.ም ነው። ህገ መንግስቱ የመላው የሀገራችን ህዝቦች እንጂ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ አሊያም የደህዴን ወይም የሌላ ሀገራዊ ድርጅት አይደለም። ሊሆንም አይችልም። አንቀፅ 39 የዚህ ህገ መንግስት “ምሶሶ” (Pillar) ነው። ህዝቦች ተወያይተው ያመኑበትም አንቀፅ ነው። ይህ አንቀፅ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች መፍትሔ እንጂ አቶ ኢሳያስ በአላዋቂነት እንዳሉት ከቶም የችግር ምክንያት አይደለም። ርግጥ በአንቀፁ ከተገለፁት ጉዳዮች ውስጥ “የራስን መብት በራስ የመወሰን ዕድል እስከ መገንጠል” የሚለው ለህዝቦች የተሰጠው ዴሞክራሲያዊ መብት አንዱ ነው። ምንም እንኳን አቶ ኢሳያስ ስለ ዴሞክራሲያዊ መብት የተፃፈ ነገር ሁሉ ችግር መስሎ የሚታያቸው ግለሰብ ቢሆኑም፤ ይህ መብት በህገ መንግስቱ ላይ መቀመጡ ህዝቦች በጋራ ፍላጎትና ፈቃድ ላይ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ ነው።

አቶ ኢሳያስ በተጠናወታቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት አስተሳሰብ ምክንያት ‘ለምን ህገ መንግስት ይኖራችኋል?፣ ለምን እንደ እኔ በነሲብ አትመሩም? አሊያም ለምን ስለ ህገ መንግስታችሁ ውስጥ ስለ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ፃፋችሁ?’ ለማለት ካልፈለጉ በስተቀር፤ አንቀፁ የብሔርንና ተጓዳኝ ጭቆናዎችን ለማስወገድ ዋስትና ነው። ይህ መብት በህገ መንግስታችን ውስጥ ከተደነገገ በኋላ፤ ቀደም ሲል የመብቱን ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ኃይሎች በፌዴራል ስርዓቱ ህብረት ውስጥ እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው ነው።  

አቶ ኢሳያስ መብቱ ቢጎመዝዛቸውም የመገንጠል መብት የስነ ልቦና ጫና እና ጥርጣሬን የሚያስወግድ የተሟላ ነፃነትን የሚሰጥ መሆኑን ልነግራቸው እሻለሁ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ለማንነቶች የተሟላ መብት ያጎናፀፈ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ በመሆኑ በዓይነቱ ልዩና የላቀ የማንነት አያያዝ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ እንጂ እንደ ርሳቸው ወረቀትና ህግ አልባ እሳቤ የፀረ ዴሞክራሲያዊነት መገለጫ አይደለም። እናም ሰውዬው ስለ አንቀፅ 39 ከማውራታቸው በፊት ምንነቱን ማወቅና ለሀገራችን ህዝቦች ያስገኛቸውን ጠቀሜታ በተረዱት ነበር—ምንም እንኳን በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ የማያገባቸው ቢሆንም።

ርግጥ አስመራ ቤተ መንግስት ውስጥ የሚገኘው መዝገበ ቃላት እንደሚያዘው ‘ውሸት በመርህ ደረጃ እውነት ነው።’ እናም ሰውዬው የግል ጋዜጠኛቸው ከሚመስሉት እነ ዑስማን ጋር ባደረጉት ቆይታ “ሳዋ ውስጥ የግብፅ ወታደሮች አለ የሚባለው ነገር በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፆረና ውጊያ ወቅት የግብፅ ወታደሮች አሉ በሚል የተነገረውን ውሸት ያስታውሰኛል” ብለዋል። እንግዲህ ይህን የውሸት ክምር አንባቢያን “ቀቢፀ- ተስፋ ሶስት” ብለው ይመዝግቡልኝ።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አንድ ጉዳይ “አለ” ወይም “የለም” የሚል ጥያቄ የቀረበለት ሰው ምላሹን ከሁለቱ አንዱ መርጦ መስጠት እንጂ ዘሎ የጦርነት ታሪክን ማውራት አይገባውም። አቶ ኢሳያስ ግን ከጦርነት ጋር የካቶሊክ ጋብቻ የፈፀሙ ግለሰብ በመሆናቸው አንድን ጉዳይ ለማስረዳት ምሳሌያቸው ጦርነት መሆኑ የሚገርም አይደለም። ለነገሩ የ‘ወዲ አፎም’ ቅብጥርጥሮሽ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ውሸት መርሃቸውና የወቅታዊ ችግር ማብረጃቸው ነው። እዚህ ላይ ግብፅን በተመለከተ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊትና በኋላ ያሉትን እንዲሁም በሰሞኑ መግለጫቸው ላይ የደሰኮሩትን ዋዣቂ ሃሳባቸውን ማንሳት እችላለሁ።

የሻዕቢያው መሪ ከነፃነት በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደለመዱት ከዲያስፖራው ቀረጥ ለመሰብሰብ ወደ ውጭ አምርተው “…የግብፅ ፖለቲከኞች አተያይ ለረጅም ዘመናት የተዛባ ሆኖ መቆየቱ ብዙ የሚያከራክር አይደለም።…ግብፅ ለኤርትራ የምታደርገው ድጋፍ የኢትዮጵያን ሰላም ለማሳጣት ኤርትራን በመሳሪያነት ለመጠቀም እንጂ ኤርትራ ነፃነቷን አግኝታ ሉዓላዊት ሀገር እንድትሆን አልነበረም። ምክንያቱም ከግብፅ ትላልቅ ስትራቴጂካዊ ችግሮች መካከል የዓባይ ውሃ አንዱ ነው። ግብፅ በዓባይ ውሃ ላይ የሚኖራት የመቆጣጠር አቅም ውሃው የሚነሳበት አካባቢ ባሉ ሀገራት ውስጥ አለመረጋጋት ከመፍጠር ውጭ የሚሳካ አይደለም የሚል እምነት አላት።…” በማለት ተናግረው ነበር። ይህም በወቅቱ ሻዕቢያ ምን ያህል ከግብፅ ጋር ሆድና ጀርባ እንደነበር የሚያሳይ ነው።

አክሮባቲስቱ ኢሳያስ ግን በአስመራው ቤተ መንግስት ውሸት ከታሪ መዝገበ ቃላት ተመርተው ይህን ሃሳባቸውን ለመቀየር ጊዜ አልወሰደባቸውም። ያለ ጦርነት ለጥቂት ዓመታት እንኳን መኖር የማይችሉት ‘ወዲ አፎም’ ሀገራችንን ለመውረር ሲያስቡ ሮጠው የተሸጎጡት ግብፅ ጉያ ውስጥ ነው። ወረራቸው በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ድባቅ መሪነት ከተቀለበሰ በኋላም ግብፅን አስመልክተው “…ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት ግብፅ ከቀጣናችን በመውጣቷ ምክንያት በአባይ ተፋሰስና በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ወሳኝ ሚና አልነበራትም። እናም የሽግግር መድረክ ተፈጥሮ ግብፅ ወደ ነበረችበት ኃያልነቷ መመለስ አለባት። ይህ የውጭ ግንኙነታችን መሰረታዊ አቋም ነው።…” ብለው እርፍ አሉት። የሻዕቢያ አዲሱ አቋም ቀደም ሲል ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ርሳቸው በአንደበታቸው እንዳሉት ከግብፅ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ማድረግ መሆኑን የሚያሳይ ነው። አቶ ኢሳያስ ባልተፃፈ የውጭ ግንኙነታቸው ላይ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከግብፅ ጋር ተስማምተዋል ማለት መሆኑንም የሚያረጋግጥ ነው።

ታዲያ ይህን አቋማቸውን ሰሞኑን ለሀገራቸው ጋዜጠኞች “…ከግብፅ ጋር ባለን ሁሉን አቀፍ ትብብር አሁን ባለንበት ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ ወደ ኋላ የምንልበት ጉዳይ አይደለም። በየትኛውም ሁኔታ ወታደራዊና ፀጥታዊ ትብብር ለማድረግ ብንፈልግ እንኳን ወሬና ሐሜትን ፈርተን የምንተወው ጉዳይ አይደለም።” በማለት አጠናክረውታል። በእኔ እምነት ይህ የአቶ ኢሳያስ ከግብፅ ጋር ያላቸው ጊዜያዊ ወዳጅነት ጥገኛው መሪ የግብፆች ተላላኪ ሆነው ለመስራት ምን ያህል ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ይህ የሰውዬው ለከፈላቸው ሁሉ በተላላኪነት የመስራት ፍላጎት በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ የኢፌዴሪ መንግስት በቅርበት ሊከታተለው የሚገባ ይመስለኛል። የሰውዬው ሰሞነኛ ዲስኩር መነሻውና መድረሻው ይኸው የልብ ልብ የሰጣቸው ቀቢፀ-ተስፋ ስለሆነ ነው።

ያም ሆነ ይህ ግን ርሳቸው ‘ግብፆች ሳዋ ውስጥ አሉ ወይስ የሉም?’ ተብለው ለተጠየቁት የፆረናን ውጊያ እንዳስታወሱት፤ እኔም የርሳቸው አባባል የጦጢትና ጅብን አፈ ታሪክን ያስታውሰኛል። ነገሩ እንዲህ ነው።…ጦጢት ዛፍ ላይ ቁጭ ብላለች። አያ ጅቦ ደግሞ ወደ ላይ አንጋጦ ያወራል።…

አያ ጅቦ፦ “ ጦጢት ሁሌም በርቀት እንደተያየን ነው። ለምን ከዛፉ ላይ ወርደሽ በቅርበት

          የሆድ የሆዳችንን አንጨዋወትም”  

ጦጢት፦ “አይ አያ ጅቦ! እዚህም ሆኜ እኮ የምትናገረው ይሰማኛል። ግድ የለህም አንተም

        እዚያው እኔም እዚህ ሆኜ መጨዋወት እንችላለን”

አያ ጅቦ፦ “ጦጢት ሙች አልበላሽም። ውረጂና እንጨዋወት”

ጦጢት ፦”እንዴ አያ ጅቦ፣ አሁን አልበላሽምን ምን አመጣው?” በማለት ምላሽ ሰጥታ ከፈገግታ ጋር አያ ጅቦን ታሰናብተዋለች።

ከዚህ አፈ ታሪክ የምንረዳው ነገር ቢኖር፤ አያ ጅቦ ጦጢትን ለመብላት ሲል ውረጅና እንጨዋወት የሚለው ተራ ብልጠት በጦጢት ብልህ አስተሳሰብ መክሸፉን ነው። አቶ ኢሳያስም ሳዋ ውስጥ ግብፆች መኖርና አለመኖራቸው ተጠይቀው ስለ ፆረና ማውራታቸው ልክ እንደ አያ ጅቦ ጅላጅል መንገድን መከተላቸው ነው። ሆኖም እኛ ኢትዮጵያዊያን ግብፆች ሳዋ ውስጥም ይሁን አስመራው ቤተ መንግስት ውስጥ ቢገኙ የለመድነው ስለሆነ አይገደንም። ምክንያቱም የግብፆች ቅድመ አያቶችና አያቶች ላለፉት ረጅም ዘመናት ዓባይን ለመቆጣጠር ሲሉ ለ14 ጊዜያት ሊወሩን የመጡት በዚያው በኤርትራ በኩል ስለሆነ ነው። ግና ኢትዮጵያዊያን ማን መሆናችንና እንዴት መክተንና አሳፍረን እንደመለስናቸው ቅድመ አያቶቻቸውና አያቶቻቸው በአፈ ታሪክነት ሳይነገሯቸው የቀሩ አይመስለኝም። ምንም እንኳን ‘አያ ጅቦ’ ስለ ግብፆች የሳዋ ወታደራዊ ቤዝ ለማውራት ባይሹም፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በፆረናም ይሁን በሌሎች ግንባሮች የሻዕቢያ ወታደሮች ፈርጥጠው ጥለው የሸሹትን የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችና ፈንጂዎች “በግብፅ የተሰሩ” (Made in Egypt) የሚሉ መሆናቸውን ‘አያ ጅቦ’ም ይሁኑ እኛ ጠንቅቀን እናውቃለን።

ያም ሆነ ይህ አቶ ኢሳያስ ከመሰንበቻው ‘አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም’ ለማለት ያህል የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ትኩሳት ባስገኘላቸው ሽርፍራፊ ዶላሮች የልብ ልብ ሰጥቷቸው ባልተለመደ ሁኔታ በቀቢፀ-ተስፋ በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መሞከራቸው (በተለይም ግብፅ ሄደው ከተመለሱ በኋላ)፤ የሰውዬውን ማንነት የሚያሳይ ብቻ እንጂ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይደለም። ልፈፋቸው ከኤርትራ ቴሌቪዥን ሰሞነኛ ዲስኩር ማሟያ አሊያም ይህን እንዲናገሩ የላካቸው አካል የሰጣቸውን ዳረጎት ያህል እንኳን ሚዛን የሚደፋ አይደለም። በአላዋቂነት የታጀበ ባዶ ትረካ ነው።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሰውዬው “ሲሞቅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ በእጅ” እንደሚባለው አሊያም ፈረንጆች እንደሚሉት “tasting the water” (ውሃው ይሞቃል ወይስ ይቀዘቅዛል) እያሉ እየሞከሩ መሆኑን መናገር ይቻላል። ሙከራቸው ግን የኢትዮጵያን ህዝብና ታሪክን ያላገናዘበ በመሆኑ የሚያስከፍላቸውን ዋጋ እንኳን በቅጡ የተገነዘቡት አይደለም። በእኔ እምነት አንገት የተፈጠረው ዞር ብሎ ለማየት ነውና ሰውዬው የቀቢፀ-ተስፋ ልፈፋቸውን መላልሰው ቢያጤኑት ለርሳቸውም ይሁን ለላኪዎቻቸው ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy