Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቄሮ ማነው?

0 2,193

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቄሮ ማነው?

ኢብሳ ነመራ

ቄሮ የሚለው የኦሮሚኛ ቃል ለብዙዎች እንግዳ ነው። ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ጭምር ዘውትር የሚጠቀሙበት ቃል አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኦሮሚያ ውስጥ የተለመደ ቃል ሆኗል፣ የተቀረውም ህዝብ ዘወትር የሚሰማው ቃል ለመሆን በቅቷል። ቄሮ በጥቅሉ ወጣት ማለት ቢሆንም ወጣት የሚለውን ለመግለጽ ከቄሮ ይልቅ በመደበኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው ደርገጌሳ (dargaggeessa) የሚለው ቃል ነው።

ሰሞኑን በኦሮሚያ ብሮደካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ቴሌቪዥን አባገዳዎች የቄሮ ምንነትን አስመልክተው ባብራሪያ ሰጥተው ነበር። በአባገዳዎቹ ማብራሪያ መሰረት ቄሮ በሚባለው ቃል የሚወከሉት እድሜያቸው ከ24 እስከ 32 የሆኑ ኩሳ (kuusaa) ወይም ቆንዳለ (qondaala) የሚባለው የገዳ የእድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች ሆነው ትዳር ያልመሰረቱት ናቸው። ስለዚህ ከገዳ ስርአት አኳያ ሲታይ ቄሮ ከ24 እስከ 32 ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ ያላገቡ ወጣቶች ማለት ይሆናል።

እንደአባገዳዎቹ ማብራሪያ ቄሮዎች በተለይ በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው። ሳርና ውሃ ፍለጋ ከብቶች ራቅ ወዳለ ቦታ ሲሰማሩ ይህን ተግባር በዋናነት የሚያከናውኑት ቄሮዎች ናቸው። የቄሮዎች እንቅስቃሴና ተግባር የሚወሰነው በአባ ገዳዎችና በሃገር ሽማገሌዎች ነው። ቄሮዎች ከአባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ውሳኔና ትዕዛዝ ውጭ መንቀሳቀስ አይችሉም።

የቄሮ ምንነትና ተግባር ከገዳ ስርአት አኳያ ከላይ የተገለጸውን ቢመስልም፣ ቄሮ በአጠቃላይ ወጣት ማለት ነው የሚሉም አሉ። ያም ሆነ ይህ፣ በገዳ ስርአት በአባገዳዎችና በሃገር ሽማግሌዎች ወሳኔና ትዕዛዝ ብቻ የሚመራው ቄሮ  አዛዥ ነን የሚሉ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ተፈጥረዋል። እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ቄሮ እያሉ ለሚጠሩትና በአካል ለማያወቁት፣ እርሱም ለማያውቃቸው የህብረተሰብ ክፍል ትእዛዝ እያስተላለፉ ህዝቡን ግራ ሲያጋቡት ከርመዋል። ይህ ቄሮ የተሰኘ በማህበራዊ ሚዲያ የሚመራ ቡድን እንቅስቃሴ የተሰማው በተለይ ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ነበር። እርግጥ ከእንቅስቃሴው ባህሪ አኳያ ሲታይ በወጉ የተደራጀም አይደለም። ስሜት ኮርኳሪ ጉዳይ ሲያጋጥም ድንገት ቦግ ብሎ የሚጠፋ አይነት ነው።

በመሰረቱ በገዳ ስርአት ውስጥ ቄሮ የሰላምና የልማት ሃይል ነው። ቤቴ፤ ሚስቴ፤ ልጆቼ ብሎ ሃሳቡ ሳይከፈል የማህበረሰቡን የልማትና የሰላም ማስከበር ሃላፊነት ወስዶ የሚወጣ ሃይል ነው። ቄሮ ከአባገዳዎች ትእዛዝ ውጭ እንደፈለገ የሚፈነጭና በራሱም ማህበረሰብ ውስጥ ሆነ በአጎራባች ማህበረሰብ ውስጥ ሁከትና ግርግር የሚፈጥር ሃይል ማለት አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንመለከተው የቄሮ እንቅስቃሴ የሚባል ግርግር ግን በገዳ ስርአት ካለው ቄሮ በባህሪው የተለየ የስርአተ አልበኞች እንቅስቃሴ ነው። የነጋዴዎች የገቢ ግብር ትመና የተከናወነ ሰሞን የተጀመረው ይህ የማህበራዊ ሚዲያ ቄሮ እንቅስቃሴ ህዝቡ ላይ ስጋት ፈጥሮ ነበር።

የት እንዳሉ የማይታወቁ፣ ማንነቱንና ዓላማውን ከማያውቁት ሰው በማህበራዊ ሚዲያ የሚደርሳቸውን ትዕዛዝ ተከተለው ድንጋይ እየወረወሩ ህዝብ የሚያውኩ ራሳቸውን ቄሮ ብለው የሚጠሩ ለጋ ወጣቶች በወጉ ያልተደራጁ ቢሆኑም፣ በህቡዕ የሚያንቀሳቅሳቸው መሪ ያላቸው መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። ወጣቶቹ በምግባር የልማትና የሰላም ሃይል ከመሆን ይልቅ የግርግር፣ የውድመትና የስጋት መልእክተኞች ናቸው። በዚህ ምግባር የሚገለጹት ወጣቶች ቄሮ የሚለው መጠሪያ አይገልጻቸውም፤ መጠሪያው አይመጥናቸውም። በመሆኑም በይፋ ቄሮ ተብለው ሊጠሩ ወይም በቄሮነት ሊፈረጁ አይገባም። በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ የወንጀል ቡድን አባላት የሚለው መጠሪያ ይበልጥ ይገልጻቸዋል።

የቄሮን ሰያሜ ለብሰው የውድመትና የስጋት ምንጭ የሆኑ ለጋ ወጣቶች እዚህ ውስጥ የገቡት ተደናገረው ነው። እነደሚታወቀው በመላ ሃገሪቱ በኦሮሚያም ጭምር ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ችግር፣ የስራ አጥነት ችግር አለ። ይህ ችግር ተከማችቶ ኮርኳሪ አጋጣሚ ሲያገኝ በህዝባዊ ተቃውሞነት አደባባይ መወጣቱም የታወቃል። በአብዛኛው ወጣቶች የተሳተፉበተና 2008 ዓ/ም መግቢያ ገደማ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ ተጨባጭ ምክንያት ነበርው። ይህን የክልሉና የፌደራል መንግስት ተቀብለው፣ መሰረታዊው የችግር ምንጭ የመንግስት አፈጻጻም ችግር መሆኑን አምነው ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለይ ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው ኦህዴድ ኢህአዴግ ለህዝቡ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄ እንዲሁም የወጣቶች የስራ እድል ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ራሳቸውን ለማደስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በኦሮሚያ ከርዕሰ መሰተዳደርና ከክልሉ ካቢኔ ጀምሮ እስከወረዳ ያሉ የስራ ሃላፊዎችን በአዲስ እንዲተኩ ተደርጓል። ይህ እርምጃ  የመታደስ እንቅስቃሴ ወጤት ነው።

ይህ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። በእነዚህ እርምጃዎች ተጨባጭ መሻሻል ታይቷል። በቀጣይ መሰረታዊ የህዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ ወዘተ ጥያቄዎች በአብዛኛው ምላሽ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ተስፋም ተፈጥሯል። ይሁን እንጂ እነዚህ ተጨባጭ ውጤቶችና ተስፋዎች የሚፈለገውንና መሆን ያለበትን ሰላም አላመጡም። አልፎ አልፎ የተለያዩ ሰበቦች በመፍጠር በሰላማዊ መንገድ ሊቀርቡ የሚችሉና ይህን ማድረግ የሚያስችል መድረክ ሊመቻችላቸው የሚችሉ ጥያቄዎችን ያለወጉ በመጠምዘዝ እዚህም እዚያም ሁከት ሲፈጠር ቆይቷል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄዱ ህዝባዊ በዓላትን ኢሬቻን ጨምሮ የሁከት አውድማ ለማድረግ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

እነዚህ ሁከቶች የሚጠነሰሱት ውጭ ሃገር ነው። ወደሃገር ቤት የሚተላለፉት ማንም ሃላፊነት በማይወስድባቸውና ተጠያቂነት በሌለባቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ነው። ይህን በማህበራዊ ሚዲያ የደረሰ መልዕክት የሚቀበሉ የሁከት አስፈጻሚዎች መኖራቸው ባይካድም በሁከቱና ግርግር ውስጥ የሚሳተፉት ግን ከሁከቱ ጀርባ ያለውን እኩይ ዓላማ የማያውቁ ወጣቶች ናቸው። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቄሮ የሚል ስያሜ የተለጠፈባቸው በአብዛኛው እነዚህ ከሁከቱ ጀርባ ያለውን እኩይ ዓላማ የማያውቁ ለጋ ወጣቶች ናቸው። የሁከቱን ዓላማና የሚያስከትለውን አደገኛ ውጤት አውቀው ለጋ ወጣቶቹን የሚመሩ ግለሰቦች ግን አሉ።

በሌላ በኩል፤ ምንም የማያውቁ ወጣቶች የሚያካሂዱትን ሁከት በመከላከል ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ በገዳ ስርአት መሰረት የሚንቀሳቀሱ ፎሌ የተሰኙ ወጣቶችንም አይተናል። በገዳ መዋቅር ውስጥ ፎሌ የሚባሉት እድሜያቸው ከ16 እስከ 24 ዓመት የሆኑ ጉብሎች ናቸው። እነዚህ በገዳ መዋቅር ውስጥ ቄሮዎችንም ወደሚያካተተው ኩሳ ወይም ቆንዳለ ለመሸጋጋር የታጩ ወጣቶች በተለይ ዘንድሮ የተከበረው የኢሬቻ በአል ላይ የሁከት መልዕክተኞቹን እንቅስቃሴ ደፍቀው ሰላምን በማስከበር በገዳ ስርአት መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ተወጥተዋል። ይህ የፎሌዎች እንቅስቃሴ እንዳይጠለፍ አባገዳዎች ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

እንግዲህ፣ በአሁኑ ወቅት የገዳ መዋቅር ተረስቶ በነበረባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች በሙሉ እንዲያሰራራ እየተደረገ ነው። እናም ነገ አባገዳዎች የሚሆኑ ፎሌዎችን በማደራጀት የሰላምና የልማት ሃላፊነትን መወጣት በሚያስችላቸው ስነምግባር ታንጸው የሚያድጉበት ሁኔታ ይመቻቻል። ይህ ደግሞ በፎሌም ይሁን በቄሮ ሽፋን የሚካሄዱ የውድመትና የስጋት ልዑካን እንቅስቃሴዎችን መከላከል፣ ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ ማደላደል የሚያስችል እድል ይፈጥራል። በአጠቃላይ ቄሮ የልማትና የሰላም ሃይል እንጂ የውድመትና የስጋት ልዑክ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy