Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

            በደም የተሳሰረው ግንኙነት

0 636

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

            በደም የተሳሰረው ግንኙነት

                                                              ይልቃል ፍርዱ  

የኢፌድሪ ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባለፈው ሳምንት የኩባ ሪፐብሊክን ጎብኝተዋል፤ የኩባው ፕሬዚደንት ራውል ካስትሮም ኦፊሴላዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ኢትዮጰያና ኩባ በደም የተሳሰረ፤ በመስዋእትነት የደመቀ ታሪክ ያላቸው ወዳጅ አገራት ናቸው፡፡ ኩባ ለኢትዮጰያ የክፉና የቁርጥ ቀን ወዳጅ ነች፡፡

የፕሬዚደንቱ ጉብኝት ኩባና ኢትዮጵያ ዳግም በብዙ መስክ ያላቸውን የወዳጅነት ትስስር እንዲጎለብት ያደርገዋል፡፡ በሳይንስና ምርምር፣ በተለይ በሕክምናው፣ በግብርናው፣ በመድሀኒትና በትምሕርት ዘርፎች የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ያለው ውጤት ሊያስመዘግብ የሚችል ነው፡፡ የኩባና የኢትዮጵያ ግንኙነት የበለጠ መጠናከር መጎልበትም ይገባዋል፡፡ አሜሪካን ኢትዮጵያን ስትከዳ ኩባ ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት የቆመች የሕይወት መስዋእትነት የከፈለች ወዳጅ አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያውያንና ኩባውያን በሶማሊያው ጦርነት ወቅት በአንድ ጦር ሜዳ ተዋግተው በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል፡፡ ለዚህም  የክፉ ቀን ወዳጅነታቸው ኢትዮጵያ በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ለኩባውያን ጀግኖች መታሰቢያ ኃውልት አቁማለች፡፡ ዛሬም የያን ጊዜው አዲስ ግንኙነት የበለጠ ያድግ ዘንድ ይጠበቃል፡፡

እብሪተኛው የሶማሊያ ፕሬዚደንት ዚያድ ባሬ ከግብጽ መንግስትና ከአንዳንድ የአረብ መንግስታት ባገኘው ወታደራዊ እርዳታ በወቅቱ ከሶቭየት ሕብረትም ጋር በነበረው ወዳጅነት እጅግ ዘመናዊ የጦር ጀቶችን፣ ታንኮችን፣ ሚሳኤሎችን . . . ታጥቆ በርካታ ሜካናይዝድና እግረኛ ክፍለጦሮችን አደራጅቶ እና አቀናጅቶ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር፡፡

በግብጽ የጦር ጀነራሎች የቅርብ አማካሪነትና የጦር እቅድ አውጪነት በኢትዮጵያ ላይ በአየር ጥቃትና በምድር የተቀናጀ ማጥቃት በመሰንዘር ግዛቴ አዋሽ ድረስ ነው የሚለው ዚያድ ባሬ 700 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ የኢትዮጵያን ግዛት ጥሶ ገባ፡፡ በአጭሩ ሐረርና ድሬድዋን በመድፍ ርቀት ውስጥ አስገብቶ መደብደብ ጀመረ፡፡ በኢትዮጰያ በኩል በወቅቱ ንጉሡ ከስልጣን የወረዱበት ግዜ ስለነበር ኢትዮጵያን ተረክቦ እየመራት የነበረው ወታደራዊ ደርግ ሊመክተኝ አይችልም፤ በቂ የሰው ኃይልና መሳሪያ የለውም፤ ስለዚህም ተመራጩ ግዜ አሁን ነው፤ እስከ አዋሽ ድረስም የኢትዮጵያን ግዛት መቆጣጠር እችላለሁ በሚል የተሳሳተ ስሌት ነበር ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ የማጥቃት ጦርነት ከፍቶ ሰተት ብሎ የገባው፡፡

ዚያድባሬ በአነስተኛ ከተሞች የነበሩትን የኢትዮጵያ የፖሊስና የፈጥኖ ደራሽ ኬላዎችን እየደመሰሰ እየገደለ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እያደረገ ሠራዊት ባለበትና መከላከል በገጠመው አካባቢ በማለፍ በርካታ ቦታዎችን በመያዝ ተቆጣጠረ፡፡ በግብርናና ከብት እርባታ የሚተዳደሩ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውንን ያለርህራሄ ገደለ፤ ሕጻናትና ሴቶች አልቀሩትም፤ ደፈረ፤ በምርኮም አጋዘ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የታጠቀው አሜሪካ ሰራሽ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ግዜ የነበሩ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣ ታንኮችና መድፎችን የነበረ ቢሆንም በአለው አቅም የኋላ ረዳት እስኪደርስለት ድረስ ታላቅ ተጋድሎ አድርጎአል፡፡

በቀጠናው ኢትዮጵያ አንድ  ክፍለጦር ከተደራቢ አነስተኛ ኃይሎች የፖሊስና የፈጥኖ ደራሽ ውስን ኃይል ብቻ የነበራት ሲሆን ሶማሊያ ወረራ የፈጸመችብን የሰማይና መሬት ያህል ልዩነት ባለው መልኩ 25 ክፍለጦሮችን በሚግ ጀቶች በሜካናይዝድ በመድፈኛና በቢኤም በርካታ ምድቦች በማጀብ ነበር፡፡ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአሜሪካን ሰራሽ ኤፍ 5 ተዋጊ ጀቶች የሚግተለተለውን የሶማሊያ ሠራዊት ኮንቮይ በማጋየትና የአየር በአየር ውጊያ በመግጠም የሶማሊያን ሚግ ጀቶች መቶ በመጣል ታላቅና ድንቅ የተባለለትን የጀግንነት ስራ ሰራ፡፡

ነፍሱን ለገነት ይበለውና አምና ሕይወቱ ያለፈው በሶማሊያ እስር ቤት አስራአንድ አመታትን ያሳለፈው፤ የያኔው ሻለቃ በኋላ ብርጋድየር ጀነራል ለገሰ ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር ባደረገው የአየር በአየር ውጊያ በተለያዩ ግዜያት በኤፍ 5 ተዋጊ ጀት በመብረር ስድስት የሶማሊያ ጀቶችን መቶ የጣለ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡

ከሶማሊያው ወራሪ ሠራዊት ሌላ ከጀርባ ሁነው የሚረዱት የግብጽ መንግስትና የመከላከያ ጀነራሎች ሲሆኑ በወታደራዊ መረጃና ደሕንነትም ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ የግብጽ ጉዳይ ያው ከአባይ ወንዝ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በየትኛውም ዘመን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በጦርነት እንድትመታ ቢቻላቸውም ከካርታ ላይ እንድትጠፋ ዘመን የማይሽረው የከፋ ጠላትነት ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎች እንደሚያስቡት የግብጽ ጉዳይ ዛሬ ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ ስላለ የመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡ ብዙ መቶ አመታትን ያስቆጠረ ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ሲመሩና ሲያደራጁ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲያደራጁ፣ ወታደራዊ ስልጣና ሲሰጡ፣ ሬድዮ ጣቢያ ሲከፍቱና መጠጊያ ሲሰጡ የኖሩና ዛሬም በዚሁ ስራ ተጠምደው ያሉ ናቸው፡፡

በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት በነበሩት ቀደም ባሉ አመታት የኢትዮጵያ ወታደራዊ መረጃና ሲቪል ደሕንነቱ በስፋት ባደረገውና በተጨባጭ በደረሰበት መረጃ መሰረት ሶማሊያ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የተደራጀና የታጠቀ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለመፈጸም እየተዘጋጀ ያለ ሠራዊት እያደራጀች በመሆኑ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን መግዛት አለባት ብለው ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት ንጉሠ ነገሥቱ ከአሜሪካን መንግስት ጋር በመዋዋል ገንዘብ ተከፍሎ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች  ለኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲገባ እየተጠበቀ ሳለ ነው ንጉሱ ከስልጣን የወረዱት፡፤

ደርግ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ እንደፈጸመች ንጉሱ በከፈሉት ክፍያ መሰረት መሣሪያው ወደኢትዮጵያ እንዲላክለት የአሜሪካንን መንግስት ጠየቀ፡፡ በወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዚደንት የነበረው ጂሚ ካርተር የኢትዮጵያን በሶማሊያ መወረር የመደገፍ ያህል የጦር መሣሪያዎቹ ለኢትዮጵያ እንዳይሰጡ ከለከለ፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ላይ ታላቅ የታሪክ ክሕደት ፈጸመ፤ ደርግን መጥላትና ኢትዮጵያ እንድትወረር መፍቀድ በእጅጉ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸውና፡፡

ይህ የአሜሪካን መንግስት የፈጸመው ጥቁር ነጥብ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የማይሽር ጠባሳ ሆኖ ለዘለአለም ይኖራል፡፡ ብዙ ሺህ ዜጎቻችን ያለምሕረት ተጨፍጭፈዋል፡ ታርደዋል፡፡ ይህ ጥቃትና በደል አጥንቱን ሰርስሮ የገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ከሰሜን፣ ደቡብ፣ ምእራብ፣ ምስራቅ ያለው በፈቃደኝነት ወደ ውትድርናው ተቀላቅሎ በ3 ወር ስልጠና ዘመተ፡፡ ሌላ አማራጭ ያልነበረው ደርግ ፊቱን ወደሶቭየት ሕብረትና ኩባ አዞረ፡፡ ራሽያ፣ ኩባና የመን (የዛሬን አያድርገውና) የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጆች ሁነው ከጎናችን ተሰለፉ፡፡ ራሽያ ዘመናዊ ታንኮች፣ መድፎች፣ ቢኤሞች፣ ሚግ ጀቶችና ተዋጊ ሔሊኮፕተሮችን በስፋት በብድር ግዥ ለኢትዮጵያ በመስጠት አሰልጣኞችና ኤክስፐርቶችን ላከች፡፡ የመን የተወሰኑ መድፈኞችዋን ለኢትዮጵያ እርዳታ እንዲያደርጉ ላከች፡፡ ኩባ ደግሞ በቀጥታ በውጊያው ወረዳ የሚገባና ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ የሚዋጋ ታንከኛና መድፈኞችን ልካ በቀጥታ የሶማሊያን ወራሪ ሠራዊትን ለመደምሰስ ወደ ውጊያ ገባች፡፡

ኩባ ውጊያውን እንዲያግዙ ወደ ኢትዮጵያ የላከቻቸው ምርጥ ጀነራሎችዋን ሞት አይፈሬ ተዋጊዎችዋን ነበር፡፡ እነዚህ ጀነራሎች ጀግና፣ ደፋርና ተዋጊዎች እንዲሁም የወታደራዊ ሳይንስ ጠበብቶችም ነበሩ፡፡ ኩባውያን የኢትዮጵያን ድንበር ከወራሪዎች ለማስለቀቅ በተደረገው ከባድ ውጊያ ታላቅ የሕይወት መስዋእትነት ለእኛ ሲሉ ከፍለዋል፤ የእኛንም ሞት ሞተዋል፡፡ በሶማሊያ ጦርነት አባቶቻቸውን ያጡ የወታደር ልጆችን ኩባ ድረስ ወስደው አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡

ከወታደር ልጆች ሌላም ለከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ስኮላርሽፕ በመስጠት በርካታ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው በኩባ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለበርካታ አመታት በመማር ተመርቀው ዛሬ በብዙ ዘርፍ ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ኩባ በተባበሩት መንግስታት የትምሕርትና የሳይንስ ምርምር ማእከል በትምህርት ብቃትና ጥራት በአለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡ ኩባ በሕክምናው መስክ የካንሰር እንዲሁም የለምጽ መድሀኒት በምርምር ያገኘት ሀገር ነች፡፡ እነዚህ ግኝቶችዋ ለሀገራችን በብዙ መልኩ ይጠቅማሉ፡፡

በሕክምና፣ በግብርና ልማትና በእንስሳት ሕክምና፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በወታደራዊ ሳይንስ እና በሌሎችም መስኮች በአለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረላት፤ ብቃት ያላት ሀገር ነች፡፡ ኩባ ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ተቀብላ አስተምራ አስመርቃ ሀገራቸውን በየተማሩበት መስክ እንዲያገለግሉ ያደረገች ለኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የሆነች ሀገር ነች፡፡ ዛሬም የሀገራቱ ግንኙነት ከነበረውም በላይ እንደሚያድግ ይጠበቃል፤ ግንኙነቱ በደም የተሳሰረው ነውና፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy